Monday, 05 December 2016 09:44

ይደገማል!

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(12 votes)

 … ኖህ በድጋሚ ካርታውን ዘርግቶ ተመለከተው። ካርታው ማፕ አይደለም፡፡ የምድርንም ሆነ የሰማይን መልክአ ምድር አያሳይም፡፡ ዝም ብሎ ልሙጥ ቁርበት ላይ አንድ ቃል ተደጋግሞ ተፅፏል፡፡ ተደጋግሞ የተፃፈው ቃል … “ይደገማል” የሚል ነው።
ምድር በድጋሚ ጠፍታለች፡፡ ኖህም በድጋሚ መርከቡን ሰርቷል፡፡ በድጋሚ ዘመዶቹን ሰብስቧል። … በድጋሚ ውሀው ሞልቷል፡፡ … ስለዚህ በድጋሚ መርከቧን እየሾፈረ ይተርፋል፡፡ ማድረግ ያለበት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ኖሆች ያደረጉትን ሳያዛንፍ መድገም፡፡
በድጋሚ መርከቡ ውስጥ እንስሳቶቹ እየተንጫጩ ነው፡፡ የኦርዌልን ድርሰት የመሰለ የእንስሳት አመፅ እያካሄዱ ነው፡፡ እሱን ከነቤተሰቡ አባረው መርከቧን እነሱ ወደሚፈልጉበት ለመንዳት ነው ፍላጎታቸው። ኖህ ያውቃል፤ አመፃቸው የትም እንደማያደርስ፡፡ ምክኒያቱም፤ ሁሉም ነገር እንደከዚህ ቀደሙ የሚደገም በመሆኑ ነው፡፡ … ያውቃል፤ የእንስሳቱን አመፅ የቀሰቀሱት አሳማዎቹ እንደሆኑ፤ … ግን በድጋሚ የትም አይደርሱም፡፡ … እሱም ለእንስሳቶቹና ለቤተሰቦቹ ወደ አዲስ አለም አደርሳችኋለሁ ያላቸው በድጋሚ ውሸቱን ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በተለያየ የዓለም ጥፋት ላይ ቀደምቶቹ ኖሆች ላተረፏቸው ቃል የገቡት ውሸት እንደነበር አይቷል፡፡ ውሸት ሲደገም አዲስ ተስፋ ይፈጥራል፡፡ 30ኛውን ኖህ እንደመሆኑ፤ ወደ ሰላሳ አንደኛው አለም ህይወት እንዲተላለፍ ማድረግ ነው እግዜር የሰጠው ኃላፊነት፡፡ ከሱ በፊት ሰላሳዎቹ የምድር ጥፋቶች ላይ የተደረገውን በመድገም ነው ኃላፊነቱን የሚወጣው፡፡
ምድር እንደ አዲስ መወለድ አለባት … ከመወለዷ በፊት ግን መጥፋት ያስፈልጋት ነበር፡፡ ….
*   *   *
የተጣለበት ኃላፊነት ከባድ እንደሆነ ያውቃል። በመርከቡ ውስጥ ያሉትን የእግዜር ፍጡሮች … ንፁሆቹን መርጦ ጥንድ ጥንድ እያደረገ እንደጫናቸው … ሳይጎድሉ እንደ አገባባቸው ማውረድ አለበት። ይህንን ማድረግ ከባድ ነው፡፡ … አዳም ለእንስሳቱ ስም ሰይሞላቸው በቀላል ኃላፊነት እንደተገላገለው አይደለም፡፡ የኖህ ሸክም ከባድ ነው፡፡ ግን የፈለገ ቢከብድም ይወጣዋል፡፡ ምክንያቱም፤ ከሱ በፊት የነበሩት ሰላሳዎቹ ተወጥተውታል፡፡ እነሱ እንዴት እንደተወጡት የሚገልፅ “ማኑዋል” ለአሁነኛው ኖህ ባይተውለትም … እንደሚወጣው ግን ያለ አንዳች ጥርጥር ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር ይደገማልና ነው፡፡
ግን እንዲደገም ለማድረግ 30ኛው ኖህ ትንሽ ብልጠት ያስፈልገው ነበር፡፡ ዋናው ራስ ምታት፡- እንስሳቱ እርስ በራስ ሳይበላሉ የጥፋት ውሀው ጠፈፍ እስኪል እንዴት ይቆያሉ? የሚለው ጥያቄ ስለነበር እዚያ ላይ አተኮረ፡፡ መርከቡን ወደ የትም አቅጣጫ እየሾፈረ፡፡
የውሃውን ብዛትና ቁጣ እያስተዋለ በድጋሚ በፈጣሪው ተገረመ፡፡ “አሁን ይሄ ውሃ በሀይላንድ ጠርሙስ ታሽጎ ሲሸጥ የነበረው ነው?... ውሀ እኮ ዘመዳችን ነበር የሚመስለን … በቁጥጥራችን ስር ያደረግነው፤ … በግድብ አቁመን ለማዳ ስናደርገው ከርመናል … ግን የፈለገ ለማዳ ቢሆን፣ አውሬ በመሰረቱ አውሬ ነው፤ … ምን ሆኖ እንደሚቆጣም አይታወቅም፤ … ሊያውቅ የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ሊያባብለውም የሚችል እሱ ብቻ ነው … ያባብልና ለቅሶውን ያስቁምልን …” እያለ ሀሳቡን ከፀሎቱ ጋር ቀየጠው፡፡
የእሱ ስራ ግን እንስሳቱ ሳይበላሉ የሚቆዩበትን ብልሀት ማዋለድ ነበር፡፡ በአዕምሮው የጆርጅ ኦርዌል መፅሐፍ ይመላለስበታል፡፡ … አንዳች መፍትሄ እዛ ታሪክ ላይ እንዳለ አውቋል። … በድጋሚ ወይን ጠጁን ተጎነጨ። አሰበ፡፡ እግዚአብሔር ላይ እንዳለ አውቋል፡፡ …. በድጋሚ ወይን ጠጁን ተጎነጨ። አሰበ፡፡ እግዚአብሔር ለምን ፍጡሮቹን እንድመራ መረጠኝ? … ብሎ ሊያማርር ትንሽ ሲቀረው … መፍትሄ ሰማይ ላይ ከሚታየው መብረቅ ጋር ብልጭ አለበት፡፡ … ሚስቱን ጠርቶ አዘዛት፡፡ ያዘዛትን ተቀብላ የበኩር ልጇን አስጠርታ አዘዘችው፡፡ የበኩሩ የመሀከለኛውን .. የመሀከለኛው የመጨረሻውን ልጅ በተዋረድ አዘዘው … ትዕዛዙ ተፈፀመ፡፡
ትዕዛዙ ሁለቱን ጥንድ አሳሞች ይዘውለት እንዲመጡ ነበር፡፡ አሳሞቹ መጡ፡፡
ለአዳም የስም ማውጣቱን ቀላል ስራ የሰጠው የመጀመሪያ ፍጡሩ ስለሆነ ነው ወይንስ ስለሚወደው? … ግን ቢወደው ምን ያደርጋል፤ በመጨረሻ ላይ ረግሞ ከገነት አባረረው … እኔንስ ምን ያደርገኝ ይሆን----እያለ እያሰበ አሳሞቹን አስተዋላቸው፡፡ “አዳም የስም ማውጣቱ ነገር ቀላል የሆነለት የእንስሳ ቋንቋ መናገር ይችል ስለነበር ነው። … ምናልባትም “አሳማ” ማለት በአዳም ወቅት በነበረው ቋንቋ “መሰሪ” ማለት ሊሆን ይችላል … ትርጉሙ፡፡ … በወደፊቱ አለም ላይ ግን አብዮተኛ የሚል ትርጉም እንዲኖራችሁ እሻለሁ” አላቸው ኖህ፤ አሳሞቹን፡፡ ጆሮአቸውን ቀስረው አዳመጡት፡፡ ለካ ኖህም የእንስሳት ቋንቋ ይችላል ብለው ተገረሙ፡፡ ተንትኖ አስረዳቸው… ስለ እንስሳ እኩልነት፣ ከሰው የጭቆና ቀንበር ስለ መላቀቅ… ስለ ነፃነት … ስለ እንስሳት ወንድማማችነት …፡፡
በአንዴ ሀሳቡ በደምስራቸው ሰረፀ፡፡ አይናቸው እንባ አቆረዘዘ፡፡ የተበደሉት ሁሉ ታወሳቸው። … ቀጣይዋ ምድር የእነሱ እንጂ በድጋሚ በሰው ልጆች እጅ እንዳትወድቅ መታገል እንዳለባቸው አሳመናቸውና አመኑ፡፡ ከኖህ ተሰናብተው ወደ መሰሎቻቸው ሲመለሱ “ኮሙኒስት” ሆነዋል፡፡
እንስሳቱ ዘንድ ገቡ፤ ስብሰባ ጠሩ፡፡ የተነገራቸውን መልዕክት ከራሳቸው ግኝት እንደመነጨ አድርገው አጣፍጠው ሰበኩ፡፡ በመርከቢቷ ዳር እስከ ዳር አመፅ ተቀጣጠለ፡፡ የኖህ አላማ ለሰላሳኛ ጊዜ በድጋሚ ተሳካ፡፡ እንስሳቶቹ “ሰው” የሚባል አዲስ ጠላት ያገኙ ሲመስላቸው እርስ በራስ የነበራቸውን የተፈጥሮ ቅራኔ አስወገዱ፡፡ ሀሳብ ከተፈጥሮ በላይ ኃይል አለው፡፡ እርስ በራስ እንዳይበላሉ አዲሱ እምነታቸው አበረታቸው፡፡ ሆዳቸውን አሰረው፡፡
ሰዎች በእንስሳት እንዲሸነፉ ምን መደረግ እንዳለበት ኖህን ሲያማክሩ፣ አሳሞቹ ኖህ ሰው ስለመሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ “ሰውን ለማሸነፍ የሰው ምክር እንደሚያሻን በመረዳታችን ምክንያት ነው” … አሉት ለኖህ፡፡ ኖህም በተመሳሳይ መንገድ እንስሳትን ለማስተዳደር እንስሳ ሆኖ ከሰው ጋር መስራት የሚፈልግ ፍጡር ማስቀመጥ እንደሚሻ ገለፀላቸው፡፡ እግዚአብሔርም የምድር ውክልናውን በእሱ በኩል እንዲያከናውን ስልጣን እንደሰጠው ገለፀ፡፡
 ያሻውን አደረገ፡፡ ያደረገው ሁሉ የተደገመ ነው። ከድሮው ዓለም የጆርጅ ኦርዌል መፅሐፍ ተጠቅሞ … ለወደፊቱ ዓለም የሚሆን ፖለቲካ በመርከቢቷ ውስጥ አሰፈነ፡፡ … አስፍኖ እንስሳቱን በጠኔ አስሮ የሙላት ውሀው ጠፈፍ እስኪል በርሀብ አኖራቸው፡፡ በርሀብ እንደማይሞቱ እርግጠኛ ነበር፡፡ ምክንያቱም፤ … ከዚህ ቀደም በነበሩት ኖሆች ጊዜ የሞተ እንስሳ ስላልነበር ብቻ ነው፡፡ ደግሞም አልሞቱም፡፡ ሁሉም ነገር ይደገማል፡፡
*   *   *
እንዲያውም ጠኔ እየበረታባቸው ሲመጣ ያረቀቁት የእንስሳት አለም ህገ መንግስትን እየተጠራጠሩ ግራ መጋባት ጀመሩ፡፡ “እኩልነት የሚያስርበን ከሆነ  … የቀድሞው አንባገነንነት ምን አለን” አሉ - እነ ሚዳቋ ሁሉ፡፡ መከባበርና እኩልነት በጠኔ ከሚገድለን አንበሳ በቀድሞው ስርዓተ ወግ ቢበላን ይሻላል ብለው ማመፅ ጀመሩ፡፡ በዚህ መሀል ማህበሩ ለሁለት ተሰነጠቀ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ … ኖህ መርከቡን ሾፍሮ ሲና ተራራ በድጋሚ ደርሷል። እንስሳቱ ለሁለት ተከፋፍለው ሁለት ድርጅት አቋቋሙ፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ልዩነቶቻቸውን አስወግደው ሊዋሀዱ ሲሞክሩ ሶስት ቦታ ተከፋፈሉ።  
አንደኛው ድርጅት፡- እንስሳዎች በህገ አራዊት ይተዳደሩ፤ የሚል ነው፡፡
ሁለተኛው ድርጅት፡- እንስሳት በሰው ህግ ይተዳደሩ፤ ይላል፡፡
ሦስተኛው ድርጅት፡- እንስሳት በህገ አራዊትም ይተዳደሩ በሰው ህግ …. ችግር የለውም፤ ለረሀብና ጠኔ እስካልዳረጋቸው ድረስ የሚል አቋም ይዟል። ይህንን የሶስት ድርጅቶች ፍትጊያ አምጥተው ሲነግሩት ኖህ ሳቀ፡፡ ያሳቁት በሰው ህግ እንተዳደር ያሉት ናቸው፡፡ ሰው እንስሳ መሆኑን ፈፅሞ መርሳታቸው ነበር፡፡
እንግዲህ እዚህ ነጥብ ላይ ነው … እነ ውሻና ድመት … የተሰጣ የሚበሉ አእዋፋት … ወደ ሁለተኛው ድርጅት የተጠቀለሉት፡፡ ከዚህ ድርጅት የተሰጣትን ተልዕኮ በመወጣት ከፍ ያለ ክብር በኖህና በሰው ልጆች ዘንድ የተቸራት እርግብ ትጠቀሳለች፡፡
የሦስተኛው ድርጅት አባላት… እህል እስካመነዠጉ ድረስ አንበሳ ቢዘነጥላቸው ወይንም ሰው አጋድሞ ቢያርዳቸው ግድ የማይሰጣቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ድርጅት ለጅቦችና ደም ለሚጠጡት መሰብሰቢያ ሆነ፡፡
*   *   *
የሚገርመው ግን፤ ለሦስቱም ድርጅት መፈጠር ቁልፉን ሚና የተጫወቱት አሳሞቹ ቢሆኑም… በአቋም ደረጃ ግን ከአንዱም ድርጅት ጋር ለመቆም ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ፍላጎታቸው ከእንስሳቱም ከሰውም አይገጥምም፤ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ከፍተኛ ነበር፡፡
ኖህ ተልዕኮውን ለማጠናቀቅ ሲቀርብ… ቁራን በመርከቡ መስኮት አውጥቶ ለቀቀው፡፡ የውሃ ሙላቱ መጉደሉንና የብስ ብቅ ማለቱን አረጋግጦ እንዲነግረው ነው የላከው፡፡… ሳይመለስ ሲቀር ኖህ ረገመው፡፡ ለካ በተደጋጋሚ ከዚህ በፊት በቀድሞዎቹ ኖሆች ጊዜም ቁራ ተልኮ ያውቅ ነበር። በተደጋጋሚም ሳይመለስ ቀርቷል። ተረግሟልም፡፡ እርግብ ስትላክም የመጀመሪያዋ አልነበረም፡፡ ተልዕኮዋን ፈፅማ ስትመጣም ኖህ ሲባርካት ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ተልኮ መታዘዝ … የመጀመሪዋም ስላልሆነ የመጨረሻም አይሆንም፡፡ ምድርም መልሳ ትጠፋለች፡፡ … እርግቧም ቅጠል በጥሳ ትመለሳለች፡፡
ኖህ ስራውን አጠናቀቀ፡፡ ወደ መርከቡ ጥንድ ጥንድ አድርጎ ያስገባቸው እንስሳት፤ ተራራው ላይ ደርሰው ሲወርዱ ጥንድ ሆነው አልነበረም፤በማህበር ሆነው ነው፡፡ ግን፤ በፖለቲካ ናላቸው ዞሮ… እንደ አገባባቸው አወጣጣቸው በእንስሳዊ እርግጠኝነት የተሞላ አልነበረም፡፡
ኖህ ምንም ማድረግ እንደማይችል ያውቃል፤ ማድረግ ከነበረበት በስተቀር፡፡ ምድር ከደረሰባት ጥፋት በአልጋ ተኝታ እንደምታገግመው፣ እንስሳቶቹም ከደረሰባቸው ግራ መጋባት አገግመው ወደ እንስሳት የዋህነታቸው ይመለሳሉ፡፡ … ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በነበሩት ኖሆች ዘመንም ምድርም ከጠፋችበት ተመልሳ ነፍስ ዘርታለች፡፡ እንስሳቱም ተመልሰው የዋህ ሆነዋል፡፡ “የዋህ ቢሆኑ ነው … የጆርጅ ኦርዌል መፅሀፍ በሰላሳ ኖሆችና የኖህ ልጅ ልጆች ላይም እየተደጋገመ ሲፃፍባቸው ምንም የመንቃት ምልክት የማያሳዩት…” ሲል ኖህ አሰበ - ለ30ኛ ጊዜ፡፡

Read 3192 times