Monday, 05 December 2016 09:50

የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

 ምዕራፍ አንድ

ይህ የጉዞ ማስታወሻዬ ነው፡፡ ጉዞው አምስት የሥራ ባልደረቦቼን ያካተተ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የሰሜን በር ወጥተን በምዕራብ በር ተመለስን፡፡ ጥድፊያ የበዛበት ቢሆንም በፀደይ ወር የተደረገ አስደሳች ጉዞ ነበር፡፡ በከተማ የድግግሞሽ ህይወት የደነዘዘውና በአዲስ አበባ የጩኸት ኑሮ የደነቆረው መንፈሴ፤ ገና ድል በርን አለፍ ብለን በደኖች መካከል በእንጦጦ ተራራ ጠመዝማዛ ጎዳና ሽቅብ መውጣት እንደ ጀመርኩ ትንሳዔ አገኘ፡፡ የጸደይ ወራት ጉዞ ይመቻል፡፡ የሰላሌ ሜዳ ውብት በጸደይ ማለዳ ይደምቃል፡፡ ‹‹ዕድለኛ ሰው በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ በጸደይ ወራት የሰላሌን ሜዳ አቋርጦ የሚጓዝ ሰው ነው›› አልኩ፤ በለሆሳስ፡፡
ሆኖም ከላይ የተጠቀምኩበት ገለጻ የተውሶ ነው፡፡ ግሪካዊው ደራሲ ኒኮስ ካዛንትዛኪስ በአንድ ልቦለዱ፤ ‹‹የደስታ ምንጭ ሊሆን የሚችለው ነገር ብዙ ነው፡፡ ………ሆኖም እንደኔ ሐሳብ የሰውን ልብ አንከብክቦ ወደ ገነት የሚያስገባ ደስታ ሊገኝ የሚችለው፤ የኤጂያ ባህር ደሴቶችን ስም በለሆሳስ እየጠሩ፤ በተስማሚው የጸደይ ወራት ባህሩን ሰንጥቆ በመጓዝ ነው›› የሚል ገለጻ አለው። እሱን ተከትዬ ‹‹ዕድለኛ ሰው፤ በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ በጸደይ ወራት የሰላሌን ሜዳ አቋርጦ፤ ደብረ ሊባኖስ ጎራ ብሎ፤ የአባይን በረሃ ሰንጥቆ፤ የጎጃምና የአገው ምድርን አየር ለአንድ ሰዓትም ቢሆን ተንፍሶ …. የመጓዝ አጋጣሚ ያገኘ ሰው ነው›› አልኩ፡፡
ደብረ ሊባኖስ ከአፋፉ ቆሜ፤ ቁልቁል የቆላውን ምድር ስመለከት የተለየ ስሜት ይሰማኛል፡፡ ከአፋፉ ሆኜ ወደ በረሃው ስመለከት፤ እንደ ሽመላ ድምጹ ያማረ፤ ባልገመትኩት ሥፍራ ተደብቆ፤ ውብ ዜማን የሚያንቆረቁርና ማንነቱን የማላውቀው፤ ዓይኑን ለማየት ጉጉት የሚያሳድርብኝ አንድ ልሳነ ወርቅ ድምጻዊ፤ ለዝምታ በቀረበ ድምጽ የሚያዜምልኝ ይመስለኛል፡፡ በዜማው ነፍሴን ይበዘብዛታል፡፡ አንድ የማላውቀው የናፍቆት ስሜት ያድርብኛል። በተመስጦ ማርኮ ይይዘኛል፡፡ የደብረ ሊባኖስ አፋፍ ትዕይንት፤ ከራሴ ጋር ያቀራርበኛል፡፡ የፍቅር በር የተከፈተለት የ‹‹ኤክስታቲክ ፖይት›› ስሜት ያሳድርብኛል፡፡
ትዕይንቱን ሰበብ አድርጎ፤ እንደ ልጆች ህብር ዜማ ገርና ድሱት የሆነ ዕንቁ ስሜት የሚያሳድር ዜማ ይነሳል፡፡ ውብ እና ቀላል የህጻናት ዜማ ነው፡፡ በቃለ አንክሮ ምስጢር ያረቅቃል፡፡ ንባብን ያጎላል። ከህሊና እና ከልብ ሰልቶ የተራቀቀ ቅኔ ይሆናል። ዝርውነት እና ረቂቅነት ጋብቻ ይፈጽማሉ፡፡ ክስተቱ ልዩ ነው፡፡
በረቂቅነቱ ኃይል የገረረው ነገር፤ በዝርውነቱ እና በግልጽነቱ ይለዝባል፡፡ በረቂቅነቱ ያርቀኝና በዝርውነቱ ያቀርበኛል፡፡ በእውነት ይህ ትዕይንት፤ እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ባለ ኢዩር ገጣሚ ሊስተናገድ የሚገባው ትዕይንት ነው፡፡ የስበቱ ኃይል ግዙፍ ነው፡፡ በእኔ የምናብ ጉልበት መመጠን የማይችል የስሜት ጓዝ ያለው ባለጸጋ ትዕይንት ነው፡፡
የፋልማው እና የዘብጡ ትዕይንቶች የሚፈጥሩብኝ ስሜት፤ የአዲስ ቋንቋ ጀማሪ ተማሪ ሆኜ ሳለ፤ አንደበቱ ከተባ ፈጣን ተናጋሪ ፊት ቆሜ፤ በአዲሱ ቋንቋ የሚነግረኝን ምስጢር ለመረዳት የመሞከር ዓይነት አስቸጋሪ ስሜት ነው፡፡ አሁን የምገኝበት ሥፍራ የፈጠረብኝ ስሜት፤ እንደኔ ያለ መዋቲ እና ድኩም ምናብ ያለው ሰው ሊሸከመው እና ሊገልጸው የማይችለው ነው፡፡ ግንፊት ሰጥቶ በስሜት ያነጋግረኛል፡፡ ከኃይለኛ የስሜት ፈረስ ያስቀምጠኛል፡፡ ይህ ኃይለኛ የስሜት ፈረስ ልሂድ - ልሂድ ይለኛል፡፡ ዛቡ፣ ርካቡ እና ልጓሙ ተደናግሮኛል፡፡ የዚህን ኃይለኛ የስሜት ፈረስ መጋለብም ሆነ ልጓም ስቦ ማቆም ያቅተኛል። እናም ለደራጎን መስዋዕት ልትሆን የተሰጠች ብሩክታዊት እንደታሰረች፤ አቅም አጥቶ የታሰረ ምናብ እና ሐሳቤ፤ የአምላክ እንደ ሰማዕቱ የልዳው ጊዮርጊስ ያለ ታዳጊን ይፈልጋል፡፡ ማህሌት የቆመ ካህን በቅኔ ምስጢር የስሜቱ ግድብ እንደሚፈርስ፤ በማይገደብ ማዕበል የሚናጠው ስሜቴ ሞልቶ ይፈስሳል፡፡
ከኮረብታው ሆኜ ቁልቁል ወደ በረሃው እመለከታለሁ፡፡ ትዕይንቱ በእውን እና በህልም ዓለም መካከል የቆመውን ድንበር አፍርሶ ኩነት ይቀላቅላል፡፡ ተቃራኒ ነገሮች ድር እና ማግ ሆነው አዲስ ኩነት ያቀናብራሉ፡፡ ዓይኔ በሸለቆው እና በወንዙ መፍሰሻ መደብ ይመላለሳል፡፡ ወዲያ ማዶ በገመገሙ የሚታየው መልክዐ ምድር በስስ የቀለም ቅብ የተሳለ ይመስላል፡፡ ወዲህ እኔ የቆምኩበት የአብራጃው ምድር እና ወዲያ ከሸለቆ ያለው የሞቃታማው ምድር የተለያዩ ትዕይንቶች ህብር ዜማ ያዜማሉ፡፡ ከአብራጃው ምድር ሆኖ፤ የቆላውን ምድር ትዕይንት ማየት ለስ ባለ ውሃ ገላን እንደ መታጠብ ያዝናናል፡፡ በበረሃው የሚፈጠረው የኦና ስሜት ቀለም፤ ከደጋው የልምላሜ ደማቅ ስሜት ጋር ይቀላቀላል፡፡ በረሃውን ሳተኩር በዓይኔ የሚገባው የሐሩር ስሜት፤ በደጋው ቁር ቀዝቅዞ ይለዝባል፡፡ ከሁለቱ የተዳቀለ አዲስ ዓለም ይፈጠራል፡፡
የርቀት ትዕይንት በግዝፈት ሚዛን አግኝቶ ጉልህ ይሆናል፡፡ ከአፋፍ እስከ ቆላው በእግር ለሚጓዝ ሰው የውሎ መንገድ ይሆናል፡፡ ሆኖም በግዝፈት ድጋፍ የማዶው ተራራ ቅርብ መስሎ ይታያል፡፡ ርቀት እየሰሰተ በስሱ የሚያሳየንን ነገር፤ ግዝፈት ተደራድሮ አጉልቶ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡
በደብረ ሊባኖስ፤በአቡነ ተክለሃይማኖት የተቆረቆረ ገዳም አለ፡፡ ተክልዬ ሲያርፉ፤ ጻድቁ አቡነ ሐብተ ማርያም ተተክተዋል፡፡ ወደ ገዳሙ የሚወስድ የአስፋልት መንገድ አለ፡፡ የዠማ በረሃን አሻግሮ እየተመለከተ በመኪና ወደ ገዳሙ የሚጓዝ ሰው፤ ጥቂት ተጉዞ፤ ከአንዲት ኮረብታ ደርሶ እጥፍ ሲል ቤተክርስቲያኑ ድንገት ከዓይኑ ድቅን ይላል፡፡ በተራራ እና በገጠር ትዕይንት ከረመ ዓይን፤ ኮረብታዋን እጥፍ ሲል ድንገት ከእይታው በሚገባው ድንቅ ኪነት ይደናበራል፡፡
በዚህ ክስተት ውስጥ አስማታዊ ኃይል ፈጥሮ ውበት የሚቀምረው ድንገቴነቱ ተጨማሪ ውበት ይሰራል፡፡ የርቀት እይታ ነፍጎን የቆየው ቤተክርስቲያን፤ከአንድ የኮረብታ ደረት ሥር ብቅ ሲል፤ በጨርቅ ተሸፍኖ ቆይቶ ድንገት እንደተገለጠ ሐውልት የሰውን ስሜት ይተኩሳል፡፡ በኪነቱና ድንገቴነቱ ትብብር ተመልካችን ያንበረክካል፡፡
ኮረብታዋን እጥፍ ስንል በመጀመሪያ ከዓይን የሚገባው፤ ወተት የተሞላ ትልቅ አንገተ ረዥም ብርሌ የሚመስለው የቤተክስቲያኑ ጉተና ነው፡፡ ከብርሌው አንገት ጫፍ ጌጠኛ መስቀል ይታያል። የቤተክርስቲያን ጣሪያ ‹‹ዶሜ›› የሚባለው ዓይነት ጣሪያ ነው፡፡ ያ የብርሌ አንገት መስሎ ወደ ላይ የተመዘዘው ጉተና መሳይ ነገር ከ‹‹ዶሜው›› አናት የሚነሳ ነው፡፡ ዶሜው በከፊል ብቅ ሲል፤ የቤተክርስቲያኑ ቀሪ አካል አይታይም፡፡ ስለዚህ ዶሜው በቤተክርስቲያኑ በዙሪያው ከሚታየው አረንጓዴ ደን ላይ የተቀመጠ መስሎ ያታያል፡፡ የብርሌ አንገት የሚመስለው ነገር፤ከጀርባ ዳራ ሆኖ በሚታይ አረንጓዴ የለበሰ ተራራ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ የብርሌ አንገቱ በአረንጓዴ ማህቶት ላይ የተቀመጠ መስሎ ይታያል፡፡
ግዝፈቱ ውበት ሆኖታል፡፡ በአረንጓዴ ሸራ ላይ የተሳለ ስዕል እንጂ ህንጻ ቤተክርስቲያን አይመስልም፡፡ በአናቱ የመስቀል ሥራ ካለው ‹‹ዶሜ››፤ አንድ ስንዝር ብቻ ራቅ ያለ መስሎ የሚታይ እና ከተራራው ቁልቁል የሚፈስስ የነጭ ፈረስ ጭራ የመሰለ ፏፏቴ አለ፡፡ ለወዲያው የፈረስ ጭራ መስሎ የሚታየው ፏፏቴ፤ ጭራ አለመሆኑ የሚታወቀው ከጥቂት መደናገር በኋላ ነው። በእውነቱ ስዕል እንጂ እውን አይመስልም። ምትሃት እንጂ እሙን ነገር ለማለት አይቻልም፡፡
ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ ባሉ ኮረብታዎች መሐል ሆኖ መኪናው ሲጠመዘዝ ከአይናችሁ በድንገት ድቅን የሚለው ጉልላት፤ ከሰው እይታ መደበቅ የፈለገ እና ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ ኪነጥበብ መስሎ ይታያችኋል፡፡ ይህ ‹‹ሰማያዊ ኪነጥበብ›› ድንገት ታይቶ፤ መልሶ ከእይታ እንዳይጠፋ በመሥጋት ዓይናችሁ ይስገበገባል፡፡ በስዕል አይቶት የሄደ ሰው፤ በድንገቴ ትዕይንቱ መደንገጡ አይቀርም፡፡ በዙሪያው የሚታዩት ተራሮች የቤተ ክርስቲያኑን ግዙፍነት የማጉላት እንጂ የወደረኛነት አመል አይታይባቸውም፡፡ ህንፃ ቤተክርስቲያኑ፤ በዙሪያው ካሉት ተራሮች ጋር ተመጣጥኖ፤ ውበቱ እጥፍ ገንኖ ስሜትን ይተኩሳል፡፡ እንዲያው በጥቅሉ የአካባቢው ተራሮች ቤተክርስቲያኑ ተሰርቶ ካለቀ በኋላ በልዩ ጥንቃቄ የተቀመጡ ይመስላል፡፡ ቤተክርሰቲያኑ ሳይታሰብ ከዓይኑ ድቅን የሚልበት ሰው፤ በኢትዮጵያ ምድር የነበረውን ጉዞ አብቅቶ፤ በአንድ የአውሮፓ የገጠር ክፍል ጉዞ የጀመረ ሊመስለው ይችላል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ገዳሙ በመጣ ሰው ሆነ፤ ደጋግሞ በጎበኘው ሰው ዘንድ የሚፈጠረው ስሜት ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም እና የአካባቢው ትዕይንት ‹‹በጥንቃቄ የተሰደረ፤ ስክን ያለ እና ጌጣጌጥ ያልበዛበት፤ ኃይለኝነትን ከገራምነት አስተባብሮ የያያዘ ማለፊያ ድርሰት ይመስላል፡፡ ይህ ድርሰት መባል የሚገባውን ነገር ሁሉ በታላቅ ቁጥብነት ብሎ ይዞ፤ ከደንታ ቢስ ዝርክርክነት እና ከከንቱ ድግግሞሽ ርቆ፤ ከከንቱ ማሽሞንሞን ተጠብቆ፤ የተንዛዛ የነገር ድግስ የሌለው ቆፍጣና ድርሰት ነው፡፡ ተገቢው ነገር ሁሉ ስትር ብሎ የተገለጸበት ልዩ ድርሰት ሲሆን፤ ኃይለኛ እና ቁጡ በሆኑ ዐ. ነገሮች መሐል፤ ፍፁም ገርነት እና ስሱነት መኖሩ ያስታውቃል፡፡››
በደብረ ሊባኖስ ገዳም፤ የምኒልክ የጦር ጀነራል ራስ ጎበና ዳጨው መቃብር ይገኛል። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የጥበብ ደብር ሆኖ ነበር፡፡ ደብረ ሊባኖስ ብዙ የትርጉም ሥራዎች የተደጎሱበት ገዳም ነው፡፡ ስማቸውን የዘነጋሁት የመናዊው መነኩሴ በዚሁ ሥፍራ ኖረው ጥበብ አዝምረዋል። በዚህ ሥፍራ በቂ ቆይተናል፡፡ አሁን ጉዞው ይቀጥላል፡፡
የምንጓዝባት መኪና ምቹና ዘመናዊ ነች፡፡ እንደ ጥንግ እየተወረወረች ትጓዛለች፡፡ መንገዱ እንደ ጨርቅ ይጠቀለልላታል፡፡ ከአዲስ አበባ ረፋዱ ላይ ተነስተን፣ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ግድም ሲሆን ጎሐጽዮን ደርሰናል፡፡ አዳራችን ፍኖተ ሰላም ነው፡፡

Read 2220 times