Monday, 05 December 2016 09:53

ጠርጥር!!

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

  “--- የእኛው አፈር ያበቀለውን ታላቁ ፈላስፋ ዘርዐያዕቆብ
       ፍልስፍናዊ ምልከታውን ስንመረምር፣ ከዴካርት ጋር በአንድ ማሕጠን
       መተኛታቸውን ልቦናችን ይጠረጥራል፡፡ በሁለቱ ጠቢባን እዝነ ኅሊና
       ላይ የሚመላለሰው የጥርጣሬ ጅረት በአንድነት መግጠሙ ከሁሉም
        በላይ ይደንቃል፡፡---”
                        

       ታላቁ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሬኒ ዴካርት የንቃተ ኅሊናውን ጎኽ ለመቅደድ እንደ ችቦ የለኮሰው ጥርጣሬን ነበር። የጠቢቡ ዘመን ተሻጋሪ እሳቤ የታነጸው በጥርጣሬ ጡብ ነው። ጠርጥሮ ከእውነተኛው ኅልውናው ጋር ይወዳጃል፡፡ ጠርጥሮ ለፈጣሪው እውቅና ይሰጣል። የመጠርጠሩ ሒደት በስኬት ይሞላ ዘንድ ከብዙኃኑ ጋር በማይገጥም ሐዲድ ላይ በባይተዋርነት መንጎድ ነበረበት። በእርግጥም ጉዞው መናኛ አልነበረም፡፡ የሰብአዊ ፍጡርን ክብር ወደ ላቀ ሥፍራ የሚያሸጋግሩ ዓይነ ግቡ ዕውነታዎችን ለፍሬ በማብቃት ነው የተደመደመው። ይህም ግብር ጠቢቡን የዘመናዊ ፍልስፍና ፋና ዋጊ ሊያደርገው  ችሏል፡፡
ዴካርት ለግሪክ ፈላስፎች ያሳየው ክብር እንደ ዘመን አቻዎቹ የተጋነነ አይደለም፡፡ እስከ መካከለኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ቀኖና የነበሩ የፍልስፍና ጭብጦችን በማፈራረሱ ረገድ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ታላላቅ የግሪክ ፈላስፎችን ድክመት በመሄስ በየዘርፉ አዳዲስ የፍልስፍና ግንዛቤዎችን ለማስተዋወቅ በብርቱ ተግቷል፡፡
በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ዕውቀትን በተመለከተ የናኘው ጭብጥ በአርስቶትል አስተምህሮት የተቀየደ ነበር፡፡ ይህ አረዳድ በአናቱ ይገለበጥ ዘንድ የዴካርት ከፍልስፍናው ዓለም መቀየጥ በብርቱ ተጠበቀ፡፡ ዴካርት  ዕውቀትን የሚመስለው በዋርካ ነው ፡፡ዋርካውን ከምድር ማሕጸን ጋር ያስተሳሰረው ዲበአካል /Metaphysics/ ሲሆን ከመሬት ብቅ የሚልበት ቁመናው ደግሞ በፊዚክስ ይመሰላል ይላል፡፡ እላዩ ላይ የበቀሉት ቅርንጫፎች የሳይንስ ንዑስ ዘርፎች ናቸው፡፡ የሚታየው ከማይታየው ይመጣል እንደ ማለት ነው፡፡ ዋርካው ፍሬ ያፈራ ዘንድ የማይታዩ ጭብጦች ላይ መምከር መዘከር ተቀዳሚ ሥራ ነው፡፡ ይህ ተምሳሌት ከአርስቶትል የዕውቀት አረዳድ ጋር ፈጽሞ አይገጥምም፡፡ አርስቶትል ሁሉም ዕውቀት በተናጥል የቆመ ነው ይላል፡፡
ዴካርት በቀመረው የፍልስፍና ጭብጥ ብቻ አይደለም ከግሪክ ፋላስፎች ጋር ሆድና ጀርባ የነበረው። በምግባሩም ጭምር እንጂ፡፡ እንደ ሶቅራጠስ ፊት ለፊት ተጋፍጦ ጭዳ ከመሆን ይልቅ ገሽሽ ብሎ ደግ ጊዜ መጠበቅን መርጧል፡፡ በአንድ ወቅት ልክ እንደ ሶቅራጠስ ሀገሩን ከሚያስተዳድረው አገዛዝ ሥርዓት ጋር ፊት ለፊት የመላተም አደጋ አንዣቦበት እንደነበረ ስለ ሕይወት ታሪኩ የሚያወሱ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ የስነከዋክብት ተመራማሪው ጋለሊዮ ጋለሊዪ፣ ምድርን ከተቆናጠጠችበት ዙፋን ላይ በማውረዱ የተነሳ በካቶሊክ እምነት የደረሰበት አበሳ፣ እርሱም ላይ እንዳይደገም በመፍራት Treatise on the Universe የሚል ሥራውን ከኅትመት ብርሃን ነፍጎ በግል ማኅደር ላይ ብቻ እንዲቀር ወስኗል፡፡ ምንአልባትም ይህንን ተገቢ ፍርሃት ባይፈራ ኖሮ ለጥቆ ያበረከታቸውን ጥልቅ እሳቤዎች የፍልስፍናውን ዓለም ለማግኘት ባልታደሉ ነበር።
የጥርጣሬው አባዜ
ዴካርት የጥርጣሬ ችቦን ሲለኩስ እንዲህ ብሎ ነው የሚፈታተነን፡- ‘It is nccessary ,’once in lifetime’ to ‘demolish everything and start again, right from the foundations’’ ራሳችንን ከንቃት ማማ ላይ ለመስቀል መጀመሪያ በእጃችን ላይ የጨበጥነውን በሙሉ ጉም እንደሆነ ማመን ይኖርብናል፡፡ ይህ አሁን ያለንበት ዓለም በሕልም ይሁን በእውን ምን ማረጋገጫ አለን? በገሃዱ ዓለም ላይ እንዳለን ማስረጃ የሚሆኑን ምልክቶች በሕልም ዓለም ላይ አሉ። በገሃዱ ዓለም የምናየው እሳትና በሕልም ዓለም ላይ ያለው እሳት መንትያ ነው፡፡ ስለዚህ በሕውስታ/sense organ/ የምንቃርማቸው ቁምነገሮች እንዴት እኛነታችንን ሊወስኑ ይችላሉ?
ይህንን መላምቱን ይበልጥ የሚያጠናክረው ደግሞ በምናብ በፈጠረው ሐሳዊ መንፈስ /evil genius/ነው፡፡ የእዚህ መንፈስ ዋንኛው ሚና በቁምና በቅዥት መካከል ያለውን ዓለም ማፋለስ ይሆናል፡፡ ይህ መላምታዊ መንፈስ በሕውስታ ግንዛቤያችን ላይ መሰልጠን ይችላል። በቁምና በቅዥት መካከል ያለውን ድልድይ አፍርሶ፣ ሁለመናችንን የማጥበርበር ስልጣንም ተክኗል። ስለዚህ መላምታዊው መንፈስ ቢሆንስ የምናየውን የምናደስሰውን ዓለም የሚያበጃጅልን? ምን ማረጋገጫ ይኖረናል? በእርግጥም ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ጠቢቡ እንዲህ የቁምና የቅዥቱ ዓለም ደንግሮብን አውላላ ሜዳ ላይ ግን ጥሎን አይሰወርም፡፡ ከእዚህ ውዥንብር ነፃ የምንወጣበትን መላ ያቀብለናል፡፡ ፈሩን ሲያመላክተን ማወጠንጠኛ አእምሯችንን ዞር ብለን እንድንመለከት በመቀስቀስ ነው፡፡ መላምታዊው መንፈስ አቅሙ የሚከዳው ኹነኛ ሥፍራ አራቱን የሒሳብ መደብ ስሌት የምናወጣበት የምናወርድበት ማሰቢያችን ላይ ነው። ሁለት ሲደመር ሁለት አራት ብዬ ለመመለስ የግድ ማሰብ ይኖርብኛል፡፡ ይህን ማሰቤን ባወቅኩ ጊዜ ነው መኖሬን የማረጋግጠው፡፡ የሰው ሰውነቱ ማሰቡን ማወቁ ላይ ነው። “I think therefore  I am” (‘Cogito ergo sum’). ብሎ ያስረገጠው ለእዚሁም ነው፡፡  ሞደርን ፊሎሶፊ ገጽ 28 ይህንን ያስነብበናል፤
‘There are beliefs which are not shaken by the argument from dreaming—beliefs about what is most general, such as we encounter in mathematics. ‘Whether I am awake or asleep,’ ‘two and three added together are five, and a square has no more than four sides.’
የዴካርት ማሰብን ማወቅ ከሶቅራጠስ አለማወቅን ከማወቅ ጋር የሚዛመድበት ወሽመጥ አለ፡፡ ወሽመጡ የንቃት ዓለም ነው፡፡ ማሰብን ለማወቅም ሆነ ለዕውቀት የመራብ ንቃት ካሸለበ ውሃ ይበለዋል፡፡ ሁለቱ አባባሎች በዲያሌክቲካል ጭውውት የሚፈበረኩት ሰብዕና ብልጽግና ይሆናል፡፡ ማሰብን ከማወቅ ወደ አለማወቅን ማወቅ ሽግግሩ ዕውን ሲሆን የዑደቱ ማገባዳጃ ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን በዘመን ስሌት ሁለቱ ፈላስፎች ፊትና ኋላ በሲለፉም እሳቤያቸው አንዱ ከአንዱ ጋር ተጣማጅ ነው።
ዴካርት ጥርጣሬን ለሁሉ ነገር መነሻ ቢያደርግም ከጥርጣሬ ፍልፍስና ጎራ የሚመደብ ፈላስፋ ግን አልነበረም፡፡ ጥርጣሬን እንደ ማዝገሚያ ጎዳና ይቁጠረው እንጂ ማሳረጊያው ከእዚህ ፈጽሞ ይርቃል፡፡ የጥርጣሬ ፍልስፍና /skepticism/ አቀንቃኞች መነሻቸውም መድረሻቸውም መጠርጠር ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ወደ ኢ-ታዋቂነት ጽንፍ ይወስዱታል፡፡ የእርሱ ግን በተቃራኒው መነሻው /premises/ ኢ-ታዋቂነት ይሆንና ማሰሪያው /conclusion/ በታዋቂነት ይደመደማል። ዴካርት ከጥርጣሬ ውስጥ መዞ የሚያወጣው እርግጠኛነትን ነው፡፡ ከደመነፍስ፣ከቁም ቅዥት ዓለም ነፃ መውጪያው መንገድ ጥርጣሬ ብቻ ነው፡፡ ጥርጣሬ ሲነጥፍ የቁም ቅዠቱ ዓለም ይሰለጥብናል፡፡ መላምታዊው መንፈስ በላያችን ላይ አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ይሾማል፡፡ ለመኖራችን ዋስትና ከሆነው ዓለም እንመነጠራለን። ይህ ምንጣሮው ማሰብ በማቆማችን የተነሳ የመጣብን ጦስ ነው፡፡ ከምንጣሮው ዳፋ ለመትረፍ መጠርጠሩን ጠበቅ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡
 ያልጠረጠረ ተመነጠረ
የእኛው አፈር ያበቀለውን ታላቁ ፈላስፋ  ዘርዐያዕቆብ ፍልስፍናዊ ምልከታውን ስንመረምር፣ ከዴካርት ጋር በአንድ ማሕጠን መተኛታቸውን ልቦናችን ይጠረጥራል፡፡ በሁለቱ ጠቢባን እዝነ ኅሊና ላይ የሚመላለሰው የጥርጣሬ ጅረት በአንድነት መግጠሙ ከሁሉም በላይ ይደንቃል። ቅድሚያ የምናብ ሰጋርን ኮርኩሮ መጋለብ፣ሲለጥቅ ጋልበው የሚወዳጁትን ፍሬ ነገር በጥሬው ከመውሰድ ይልቅ ሁለመናውን መሰለል፣ መጠርጠር፡፡ ይህ ነው ከጠቢባኑ ልቦና ላይ የታተመው ፍልስፍናዊ ቀኖና ፡፡፡
ዘርዐያዕቆብ የጥርጣሬ ወጋገንን ለማፍካት ቅድሚያ የመረጠው በዙሪያ ገባው ላይ ገጽታውን ማደመንን  ነው። በአለቃ ያሬድ ፋንታ ሐተታ ዘርዐያዕቆብ በሚል ድርሳን ላይ ግሩም ሆኖ ከተሰናዳው በጥቂቱ እነሆ፡-
በኋላም በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈው ሁሉ እውነት ይሆንን? ብዬ አሰብሁ፡፡ ብዙውንም አስቤ ምንም አላስተዋልሁም፡፡ እኔም ኽጄ ምሁራንና ተመራማሪዎችን እጠይቃለሁ፡፡ እነሱም እውነትን ይነግሩኛል ብዬ አሰብሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች ምን ይመልሱልኛል? ከልባቸው ውስጥ ካለው በቀር ብዬ አሰብሁ፡፡ ሰው ሁሉ “ሃይማኖቴ የቀናች ናት፤በሌላ ኃይማኖት የሚያምኑ ግን በሐሰት ያምናሉ፡፡ እነሱ የእግዚሐብሔር ጠላቶች ናቸው” ይላልና። ዛሬ ግን ፈረንጅ  “ሃይማኖታችን መልካም ናት፤ ሃይማኖታችሁ ግን ክፉ ናት” ይሉናል፡፡ እኛም እንዲህ አይደለም ብለን እንመልስላቸዋለን፡፡ “ሃይማኖታችን ደግ ናት፤ ሃይማኖታችሁ ክፉ ናት” እንላቸዋለን፡፡
ይህን አይነት አውጫጭኝ እንኳን በዘመነ ዘርዐያዕቆብ በቆምንበት ዘመን ላይም ፈተናን ያበዛል፡፡ እርግጥ ነው፣ ይህን መሰሉን ደቃቅ ትዝብት ከልቦናችን ስንጥፍ፣ የንቃት አድባርን ለመለማመን  ሸብረክ ማለት እንጀምራለን። የመንፍስን ከፍታ ወደ የሚያበረታው ንቃታዊ ዓለም ለመሰደድ ጓዛችንን እንሸክፋለን፡፡ በበረከት ዋጅተን ከመርገም እንጠበቃለን፡፡
የጠቢባኑ ጥርጣሬን የመቆስቆስ ትጋት በዓላማ ነው የተከወነው፡፡ ጥልቅ እሳቤያቸው ያፈራውን ሲሳይ ያለ ስስት ሊያቋድሱን ላይ ታች ባጅተዋል፡፡ እዚህ ጋ “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” የሚለውን  የአበው ተረት ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

Read 1839 times