Monday, 05 December 2016 09:55

“የምርኮ አገር እውነት”

Written by  ዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(3 votes)

 (ነብስ ወለድ የሀበሻ ቅኔ)
                        

     “የወፍ ማስፈራሪያን” እና “ሚስጥረኛው ባለቅኔ”ን ያስነበበን ሚካኤል ሽፈራው፤ በ2008 መገባደጂያ ላይ “የምርኮ አገር እውነት፡
    ነብስ ወለድ የሀበሻ ቅኔ” የተሰኘ ልብወለድ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ደራሲውን ባገኘሁት ወቅትም አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቼለት
  በሰጠኝ ምላሽ ተደምሜአለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚም ብዕረኛ ብቻ ሳይሆን አንደበተ ርቱዕም እንደሆነ ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ እኔና ደራሲው
  በመጽሐፉ መነሻነት ያደረግነውን ጥበባዊ ወግ እንደወረደ ለአዲስ አድማስ አንባቢያን ላቀርበው ወደድኩ፡፡

        “ነብስ ወለድ የሀበሻ ቅኔ” ያልክበት ምክንያት ምንድን ነው?
“ነብስ ወለድ ያበሻ ቅኔ” ያልኩበት ምክንያት ከዚህ ቀደም ከምናውቃቸው ልቦለዶች የሚለይበት ጥቂት ነገሮች ስላሉ ነው፡፡ ልብ ወለድ ድርሰት ማለት በደራሲው ህይወት ላይ ከፍተኛ የሰብዕና መናጋትና የአዕምሮ መናጋት ሳይፈጥር፣ በሰከነና በረጋ መንፈስ ደራሲው አውቆና መርጦ የሚጽፈው የፈጠራ ስነ-ጽሑፍ ነው፡፡ ይህ “የምርኮ አገር እውነት” ያልኩት መጽሐፍ ግን በሰብዕናዬና በዘመን መካከል በተፈጠረ ግጭት በህይወቴ ውስጥ ተነስቶ የነበረ ታላቅ የህልውና ማዕበል ውጤት በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ ልብ ወለዶች ሁሉ ከምናባዊ ፈጠራ የተለየ የፈጠራ ውጤትን አልፎ የመጣ የነብስ የፈጠራ ውጤት ነው ብዬ ስላመንኩ “ነብስ ወለድ” የሚል እንግዳ የሆነ ስያሜ ሰጠሁት፡፡
“የሀበሻ ቅኔ” ማለትህስ?
ድርሰቱ እንደ ማንኛውም ወጥ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ሁሉ ፍፁም ኢትዮጵያዊ የሆነ የሀገራችን ምስልና የተፃፈውም በጥንታዊው የሀበሻ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ቅኔም ነው፣ ልቦለድም ነው፡፡ ያም ማለት ልብ ወለድ ሆኖ ሳለም ቅኔ ነው፡፡ እንደ ሀገራችን ሰምና ወርቅ ቅኔ ሀሳቦችን አነባብሮ የያዘ፣ ባለ ሁለት ወይም ደግሞ እንደ ተደራሲው ምናባዊ ተራክቦ መጠን በውስጡ ሰውሮ የያዘው ትርጉም እያደር እየተገለጠ የሚፈታ፣ ከዚያም በላይ የሆኑ ትርጉሞችን ያመቀ የጥበብ አነባበሮ ነው፡፡ ያም ሆኖ ላዩን ብቻ ለሚረዱ ወይም ደግሞ ጥልቅ ትርጉሙን ለመረዳት መድከም ለማይፈልጉ ተደራሲያን፣ የታሪኩን ፍሰት ተከትለው በተረቱ ብቻ ይጫወቱ ዘንድ ይፈቅዳል፡፡ ይሁንና ላዩን ሲያነቡት እንደሚመስለው የጊዜ ማሳለፊያ፣ የልጆች ተረት ግን ከቶም አይደለም። በሀገራችን ስነ-ጽሁፍ ታሪክ ሰምና ወርቅ ቅኔያችን በጥቂት መስመሮች ብዙ ምስጢር የሚነገርበት ቢሆንም በጥቂት መስመሮች የተወሰነ ሆኖ ኖሯል፡፡
በዚህ ጽሁፍ የሞከርኩት ይህን በጥቂት መስመሮች ተወስኖ የኖረውን የሀገራችንን የስነ-ጽሁፍ ዘዬ ወደ ልብ ወለድ ደረጃ ከፍ አድርጌ፣ ታሪኩ ተጀምሮ እስከሚደመደምበት ምዕራፍ ድረስ የህይወታችንን ምስል በቅኔ ልብ ወለድ መተረክ ነው፡፡ ምን ያህል እንደተሳካልኝ የሚመሰክረው እኔ ሳልሆን ተደራሲው ነው፡፡ የኔ ድርሻ ከገዛ ህይወቴ የቀዳሁትን ያገር ምስል ጠንስሼ ጠምቄ፣ተጋበዙልኝ ብዬ በአክብሮትና በልባዊነት ለተደራሲው ማቅረብ ነው፡፡ ጣዕሙን የማጣጣሙ አቅምና ደረጃ እንደተደራሲው ቅኔ የመተርጎም አቅም ይለያይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ድርሰቱ ለተለያየ ተደራሲ የተለያየ ጣዕም ቢኖረው ችግሩ ከወይን ጠጁ ብቻ ሳይሆን ከተጋባዡም ጭምር ሊሆን ይችላል። እናም ድርሰቱ በኔ እምነት አንድ ጊዜ ብቻ ተነብቦ “አንብቤዋለሁ” ተብሎ የሚዘጋ ሳይሆን ምን አልባት እንደገና ተመልሰን እንድናነብበው ያስገድደን ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ነው ይህን ጽሁፍ ቅኔ ልቦለድ ማለቴ፡፡
 ድርሰቱ ከየትኛው ዘውግ ይመደባል? ወይም አንተ ከየትኛው ዘውግ ትመድበዋለህ?
በእንግሊዝኛው “ፋንታሲ” (ምናባዊ ዕርገት) ከሚባለው የስነ-ጽሑፍ ምዳቤ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ይህ ዘውግ ለደራሲው ገደብ የለሽ ምናባዊ ጉዞን የሚፈቅድና ፍፁም ነፃነትን የሚሰጥ የአፃፃፍ መንገድ ነው፡፡ ሌላው በምዕራባዊያን የስነ-ጽሁፍ ባህል ይህን ጽሁፍ ልንመድበው የምንችለው Allegory (አሊጎሪ) ከሚባለው የኪነ-ጥበብ ዘዬ ነው፡፡ አሊጎሪ ያንድን ማህበረሰብ ህይወት በሌላ ምሳሌያዊ ዓለም ውስጥ ስሎ እንደማሳየት ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የግሪኩ ፕሌቶ The Allegory of the Cave (የዋሻው አሊጎሪ) ዘወትር ሲጠቀስ የሚኖር ነው፡፡ ፕሌቶ ሪፐብሊክ በተባለው ብቸኛ መጽሐፉ ለዘመኑ ሰዎች የሚኖሩበትን የድንቁርና እስር ቤት በምሳሌ ሊያሳያቸው ይሞክራል፡፡
የፕሌቶ የምሳሌ ማህበረ-ሰብ ሰዎች በተዘጋ ዋሻ ውስጥ በጨለማ፣ በሰንሰለት ታስረው ይኖራሉ፡፡ ከጀርባቸው የሚነድ እሳት አለ፡፡ ከእሳቱ ፊት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ። ከፊታቸው ደግሞ የዋሻው ግድግዳ አለ። በዚህ ግድግዳ ላይ የሚንቀሳቀሱት ሰዎች ምስል ጥላ ፈጥሮ፣ ጥላቸው ሲንቀሳቀስ ይታያል፡፡ ይህን የጥላ ምስል እንደ እውነተኛ የህይወት ምስልና ትርጉም አድርገው ወስደው በተሳሳተ የህይወት ትርጉም ውስጥ ይኖራሉ። ከነርሱ መሃል አንዱ እንደምንም አምልጦ ከዋሻው ይወጣና የእውነተኛውን ዓለም ምስል ይመለከታል፡፡ ይህንንም ሲመሰክርላቸው፣ ከሚኖሩበትም የሀሰት ዓለም ነፃ ሊያወጣቸው ይሞክራል። እነሱ ግን የራሳቸውን የጥላ ምስል እውነት አድርገው ስለኖሩና ስለሚኖሩ ሌላ እውነት ለመስማት ፈቃደኞች አይሆኑም፡፡ ስለዚህም እርሱም በብቸኝነት ከዋሻው ውጪ፣ እነርሱም በለመዱት የጨለማ ዓለም ይቀጥላሉ፡፡ ከዋሻው አምልጦ የወጣው፣ ከዘልማድ የአስተሳሰብ እስር ያመለጠው የፈላስፋው ፕሌቶ ምሳሌ ነው፡፡ በዋሻው ተዘግቶ የሚኖረው የእርሱ ዘመን ትውልድ ነው፡፡ ይሁንና ፕሌቶ ይህን የዋሻ ምሳሌ ከተረከላቸው በኋላ ዘመኑንና ትውልዱን ከዋሻው ለማውጣት አልቻለም፡፡
በሌላ በኩል ይህ ጽሑፍ በእንስሳት ታሪክ እንደተፃፈው እንደ ጆርጅ ኦርዌል አኒማልፋርም ያለ በእንስሳት ምስል የተፃፈ፣ በጥሞና ለሚያነቡ ልባብ ተደራሲያን የተፃፈ የዐዋቂዎች ተረት ነው፡፡ የሰው ልጅ የገዛ ራሱን ምስል በእንስሳት ምስል በተሳሉ ተረቶች ውስጥ ማየት የጀመረው የኢትዮጵያ የዘር ግንድ እንዳለው ከሚነገርለት ጥንታዊ የተረት ሰው ከግሪኩ ኤዞፕ ዘመን ጀምሮ ምናልባትም ከዚያን ዘመን አስቀድሞ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኤዞፕ አገር፣ በየባህሉና በየጎሳው እጅግ ውብና ጥልቅ የሆነ የተረትና የምሳሌ ሀብት ያላት የወረት ሳይሆን የባህል፣ የውበትና የታሪክ ባለፀጋ የሆነች ሀገር ናት፡፡
 “ታሪክና ተረት ምን ይፈይድልናል? ታሪክና ተረት ኪስ አይገባም፣ ዳቦ አይገዛም፡፡ ሀበሻ ደህይቶ የቀረው ለሶስት ሺ ዘመን እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ተረት ሲተርት ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ቁጭ ብሎ መተረት ሳይሆን ተነስቶ፣ ወገብን ጠበቅ አድርጎ መስራት ብቻ ነው” የሚሉ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ይሁንና የሰው ልጅ እንጀራ ብቻ አይበቃውም፤ እንስሳ አይደለምና፡፡ እንጀራ የጠገቡ ህዝቦች ራሳቸው ዛሬ እንጀራ ብቻውን የሰውን ልጅ ሙሉ እንደማያደርገው ተረድተዋል፡፡ ስለዚህም እንዲህ የሚያስቡ የዋሃን ይልቁንም ተረትና ታሪክ የሚመነዘሩ፣ ተመንዝረውም የትናንት መነሻችንን፣ የዛሬ መርገጫችንን፣ የነገ መዳረሻ ዕድል - ፈንታችንን ጭምር አሻግረን እንመለከታቸው ዘንድ የተሰጡን ረቂቅ ጥበባዊ መስተዋቶቻችን መሆናቸውን ተረድተው፣ ለጥበብና ለባህል አክብሮት ይሰጡ ዘንድ ፋይዳቸውን ለማሳየት የተሞከረም ሙከራ ነው፡፡
ተረቶቻችንና ስነ - ቃሎቻችን መቼና እንዴት ተፈጠሩ? የሚታወቅና የተመዘገበ ነገር ስለመኖሩ በትክክል ባላውቅም እኔ ያለፍኩበት ዘመን ግን እንዲህ ያሉት ውብ የፈጠራ ውጤቶች ቀስ በቀስ እየነጠፉና እየመከኑ መሄዳቸውን በሀዘን እናስተውላለን፡፡ ምክንያቱም የትውልድ ሁሉ ህልም ወረትና ሸቀጥ በሆነበት በዚህ ዘመን፣ ማሰብና መፍጠር የሚችሉ አዕምሮዎች ሁሉ በዚህ የማይበጨጥ ተስፋ ተማርከው ወረትን ሳይሆን ትውልድና አገርን፣ እውነትና ጥበብን ከሚያፈቅር ንፁህ ልብ የሚመነጭ ጥበብና ፈጠራ ከቶውንም ሊታሰብ የማይችል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡
አንዳንዴ የልጅነት ዘመናችንን መለስ ብዬ ሳስበው፣ እንደነ “አሌሆይ አላሌ ሆይ” ያሉትን ውብ የልጆች ጨዋታ የፈጠረ ዘመን ምንኛ ለዛ ያለው ዘመን ነበር እላለሁ። ያ ዘመን የኢኮኖሚ ድቀትና ድህነት የተጫነው ነበር ተብሎ በዚህኛው ዘመን አልሚ ትውልድ ወይም ለሙ በሚባሉቱ በሚቀናው ትውልድ ቢወቀስም፣ የለዛና የውበት ድህነት ግን፣ የመንፈስ ድርቀት ግን፣ እንዲህ እንዳለንበት ዘመን የበረታበት እንዳልነበር፣ ዘመንና ትውልድ ተሻግረው አለንበት  ዘመን የደረሱ የጥበብና የፈጠራ ውጤቶቹ የሚመሰክሩት እውነታ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ውብ ፈጠራ የሚመነጨው ደግሞ ለህፃናት ልጆቹ፣ ለውበት፣ ለጥበብ ፍቅር ካለው ማህበረሰብ ይመስለኛል። ስለዚህ ፈጠራ በፍቅር የወዛች ነፍስ ይፈልጋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለው ፈጠራ በዕለት ተዕለት ሩጫና በወረት እሽቅድምድም ያልተተበተበ፣ ለእሳት ዳር ጨዋታ የሚተርፍ ጊዜ ያለው ባህልና ማህበረሰብ ይፈልጋል። እንዲህ ያለው ባህልና ማህበረሰብ ደግሞ ዛሬ ራሱ ተረት ሆኖ ከሚቀርብበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡   
ይልቁንም እንዲህ ያሉ ውብ የጥበብ ፈጠራዎች ይቀዱበት የነበረው የባህል ምንጭ ጥልቀቱ እጅግ እየራቀን በመሄዱ ከምንጩ ደርሰን፤ ከውበቱና ከጥበቡ ለመቅዳት ሳይቻለን እነሆ በመሰላቸትና በመንፈስ ድርቀት ብዛት ነፍሳችንን ንቃቃት ይዟት ተሰነጣጥቃና ገርጥታ ትታያኛለች፡፡ ስነ ጥበብ እንዲህ እንደ ዛሬው የጊዜ ማሳለፊያ የኢንተርቴይመንት ኢንዱስትሪ ወይም ገልፍጦ ማስገልፈጫ፤ ሸንግሎ መነገጃ ሸቀጥ ብቻ ሳይሆን በፊት የዘመን ድልድይ ነበር፡፡ የዘመን ድልድይ ማለት ወደ ኋላ ተዘርግቶ ካለፈው ዘመን የእውነት፣ የውበትና የቅርስ ውርስ ጋር የሚያገናኝ፣ ወደፊት ተዘርግቶ ወረትና ሸቀጥ ብቻ ሳይሆን  ሰብዓዊ ክብርና የተቀደሰ መንፈስ ከሰፈነበት፣ሰው መሆን ልብ ከሚሞላበት ለራስና ለሌሎች አክብሮትና ፍቅርን ከሚያሳድርባት ከተስፋይቱ ምድር አሻግሮ የሚያደራርስ የዘመን ድልድይ ነበር፡፡ ስለዚህ በስነ ጽሁፍ ድልድይነት ያልነበርንበትን ዘመን ነብስ እንዘራበት ዘንድ እንችል ነበር፡፡ ያልደረስንበትን ዘመን አቅርበን፣ ዛሬን ትናንትና ነገን ባንድ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እናገኛቸው ዘንድ ስልጣን ሰጥቶ ከጊዜና ከስፍራ ወሰን በላይ ከፍ ያደርገን ነበር፡፡ በተለይ ባለ ብዙ ፍቺው፣ ባለ ንብርብር ምስጢሩ ቅኔና የምሳሌ ቋንቋ ለዚህ የተመቸ ነበር፡፡ ስለዚህ ስነጥበብን ወደ ቀደመ ክብሯ ተመልሳ ማየት የዘወትር ጉጉቴ ነው፡፡
ያም ሆኖ ይህ ሁሉ ሲሆን ‹‹ቆይ እስቲ በልቦለድ ቅኔ ልቀኝ›› ወይም ደግሞ በቅኔ ልቦለድ ልፃፍ ብዬ ወይም ከጥንታዊው የባህል ምንጫችን ቀድቼ፣የተደራሲዎቼን የጥበብ ጥም ልቁረጥ ብዬ ሆን ብዬ ያደረኩት ሥራ ከቶም አይደለም፡፡ ማንኛውም የስነ ጥበብ ውጤት የገዛ ራሱን ቅርፅ ይመርጣል እንጂ ደራሲው ‹‹እየመረጥኩ ላስጊጠው›› ቢል ውጤቱ ቅርጽና ይዘቱ የማይተዋወቅ ይልቁንም እርስ በእርሱ የሚጋጭ የስነ ጥበብ ዲሪቶ ይሆናል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለውን የስነ-ጽሁፍ ዘዬ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፤ ትክክልም ቢሆን የኔ መንገድ አይደለም፡፡
ግሩምና ማራኪ ማብራሪያ ነው፡፡ በስነ-ጽሁፍ የቅርጽና ይዘት ግንኙነት እንዴት ይገለጣል?
በስነ- ጽሁፍ የቅርጽና ይዘትን ግንኙነት ለኔ በገባኝ መጠን በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፡፡ በኔ እምነት እውነተኛ ድርሰት ስነ ጽሁፋዊ ቅርፁን የሚመርጠው ራሱ ሥራው እንጂ ደራሲው አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የድርሰት ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ሁሉ እውነት ነው። ለምሳሌ የሰውን ልጅ እንደ አንድ መለኮታዊ ድርሰት ልንወስደው እንችላለን፡፡ የሰው ልጅ ማየት ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዐይን ወይም ዐይኖች ያስፈልጉታል፡፡ በዚህ የተነሳ ዓይኖቹ ከብለል ከብለል ይበሉም ጭል ጭል፣ በዚያ ስፍራ የተቀመጡት ለማየት እንጂ ሰውዬውን ወይም ሴቲቱን ለማስጌጥ ብቻ አይደለም፡፡ ማሽተትም እንዲሁ ለሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪው ነው፡፡ እንግዲህ አፍንጫው ስንደዶም ይሁን ዳምጦ ደራሲው አፍንጫውን በዚያ ሥፍራ ያኖረለት ለጌጥነት ሳይሆን ለሰውየው መረጃ ያቀብለው ዘንድ ነው። ጆሮ እጅግም ከውበት ጋር ተዛምዶ  የሌለው ቢመስልም በልጅነት ‹‹ጆሮ ጋሻ›› እንደምንላቸው ልጆች ከመጠን በላይ ሰፍቶ ግራና ቀኝ እንደ ዘመናችን ዲሽ በተዘረጋ ጊዜ በትክክል መረጃ ሰብሳቢነቱን ራሱ ይመሰክራል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ አሁን የምናውቀውን የመሰለው ወይም ይህን ቅርጽ የያዘው የፈጠራ ባለቤቱ ገና ሲፈጥረው ሰው ሆኖ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ጠቃሚ ክፍሎች በሥፍራ በሥፍራቸው ባስቀመጣቸው ጊዜ ነው፡፡ አንድም ነገር ለጌጥ ሲባል ያለ አገልግሎትና ጥቅም የተቀመጠ ትርፍ ነገር የለበትም፡፡
ይሁንና ደግሞ እነዚህን ክፍሎች ለመደርደር ብቸኛው አቀማመጥ አሁን የምናውቀው የሰው ልጅ ምስል ብቻም ነው ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል እንደ ሆሊውድ ጭራቆች ዐይኑን ግንባሩ ላይ፤ ጆሮውን አናቱ መሀል፣ ያፍንጫውን ቀዳዳ ከአፍ ዝቅ ብሎ፤ አፍን ከአፍንጫው በላይ አድርጎ ቢያኖራቸው ኖሮ የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ሊሰጡ ይችሉ ይሆናል። ይሁንና ሰው የተባለው ፍጡር ደራሲ አገልግሎትን ብቻ ሳይሆን የውበትም ባለቤት ነውና ዛሬ በምናውቀው መንገድ የሚፈለግባቸውን አገልግሎት እየሰጡም ሳለ፣ ለዓይን በሚማርኩበትና ድርሰቱ ተደራሲዎችን ሊስብ በሚችልበት መንገድ አሳምሮ ደረደራቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ የሚገርመን የጥርስ አቀማመጥና የተመረጠለት ብሩህ ማራኪ ቀለም ነው፡፡ በተለይም በፈገግታ ብሩህ የሆነ የሕይወት ሙቀትን የማስተላለፍ ሀይሉን ስናይ፣ እነዚህን የወፍጮ ድንጋዮች ከከናፍሮቻችን ጀርባ የደረደራቸው ደራሲ፣ የይዘትና ቅርፅን አገልግሎትና ውበት እንዴት ባለ ውብ መንገድ አዋህዶ እንዳኖራቸው በመገረም እናስተውላለን፡፡ ስለዚህ ነው እንደ ዳቬንቺ ያሉት የዓለማችን ድንቅ ቀራጽያን፣ በሰው ልጅ ቁመናና ተፈጥሮ ዕድሜ ዘመናቸውን ሙሉ እየተመሰጡ፣ በድርሰቱ ውስጥ የደራሲውን ማንነት መርምረው ለመረዳት ሲጥሩ የኖሩት፡፡
ይህን ሁሉ ያልኩት የዚህን ጽሁፍ ቅርጽ የመረጠለት ደራሲው ሳይሆን የልጆቻችንን ዓይኖች፣ አፍንጫና ከናፍር ቅርጽ፣ ወላጆቻቸው እንመርጣላቸው ዘንድ ሥልጣን እንደሌለን ሁሉ፣ ይልቁንም በገዛ ራሳቸው የገዛ ራሳቸውን መልክና ቁመና ይዘው እንደሚወለዱ ሁሉ፣ የዚህም ጽሁፍ ቅርጽ ጉዳይ እንዲሁ ገና ሲፀነስ ድርሰቱ ራሱ የመረጠው ቅርጽ ነው ለማለት ነው፡፡ የወላጅ ተግባር ፀንሶ ወይም አስፀንሶ፣ አርግዞ ወይም አስረግዞ መውለድ እንደሆነ ሁሉ፣ የደራሲም ተግባር እንዲሁ ነው፡፡ ይሁንና ልጅ የወላጆቹ ደም ቅጂ እንደመሆኑ ሁሉ ድርሰቱም ያው የደራሲው ደም ቅጂ ነውና እጅግም አያስገርምም፡፡ በሌላ በኩል ደራሲው ደግሞ ማንነቱን፣ አስተሳሰቡን፣ሕይወቱን----ይህን ሁሉ የሚጋራው ከማህበረሰቡ ጋር ነውና የደራሲው ደም ቅጂ ያገርና የማህበረሰቡ ደም ቅጂም ጭምር ነው፡፡
ይህ ድርሰት በተፀነሰ ዘመን የሰው ልጅ ህልውና ዝም ብዬ ሳስተውለው፣ የሰው ልጅ የተፈጠረለት ታላቅ ምክንያት ያለ ሆኖ ይሰማኝ ነበር፡፡ ይሁንና የሰው ልጅ የተፈጠረለትን ታላቅ ምክንያት ዘንግቶ፣ ወይም ሕይወቱን ሙሉ ላንዲት ቅጽበትም ቢሆን እንዲህ ያለ ነገር መኖሩን ሳይጠረጥር በዕለት ውሎ ሩጫው እየተጣደፈ፣ እየመሸ ሲነጋ የዕድሜው ድምበር ማዘቅዘቅ ትጀምራለች፡፡ ይህም ሲሆን አሁንም ቆም ብሎ ‹‹የመፈጠሬ ትርጉም በቃ ይኸ ነው?›› ብሎ ለመጠየቅ ፋታ ሳያገኝ፣ ከዕለት አዙሪቱ ሳይወጣ ያዘቀዘቀቺው የዕድሜ ጀንበሩ ትጠልቃለች፡፡
እስኪ ስለ ድርሰቱ መቼት አስፋፍተህ ንገረን?
ድርሰቱ የተፀነሰው በአገራችን ዛሬም ድረስ ሂደቱ ባልተቋረጠው ታላቅ የሆነ የሥርዓት ለውጥ በተካሄደባቸው በአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ዓመታት ነበር፡፡ ይህ ለውጥ በቀናና በተስፋ ለሚመለከቱትም፣ በቅሬታና በምሬት ለሚፃረሩትም፣ ለሁላችንም ይዞ የመጣው ታላቅ ዕድልና ፈተና ነበር። ቀድሞ የነበረው የህይወትና የአስተሳሰብ መንገዳችንን ፈተና ላይ ጥሎታል፡፡ በዚህ ምክንያት በዚህ አስተሳሰብን፣ አኗኗርን በሚፈትን ዘመን ውስጥ የራስን ትክክለኛ ሥፍራ አግኝቶ ለመዝለቅ ሲባል፣ ራስን በራስ መፈተንን የሚያስገደድ ዘመን ነበር፡፡ እናም ይህ ድርሰት የዚህ የራስን በራስ የመፈተን ሂደት ውጤት ነው ማለት እችላለሁ፡፡
የድርሰቱ ሃሳብ መቼ ተጠነሰሰ (ተጸነሰ)? ለመጻፍ ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?
ድርሰቱ በትክክል በዚህ ጊዜ መፃፍ ተጀምሮ፣በዚህ ጊዜ ተጠናቀቀ ብዬ ለመናገር ያስቸግረኛል፡፡ ያም ሆኖ በአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ የመጨረሻ ዓመታት ሃሳቡ በውስጤ ተፀነሰ፡፡ ተፀንሶም ሲያበቃ ሽል በእናቱ ማህፀን እየተገላበጠ፣ እናቱ አንዳንዴ እያጥወለወላት ቆይቶ ጤና እየነሳት፣ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ አዲስ ሕይወት በውስጧ መፈጠሩን ማወቋ ብቻ የሚፈጥርባት ተስፋና ደስታ እያረካትና እያስኮራት፣ ዘጠኝ ወራትን ዘልቆ ቅርፁን ይዞ እንደሚፈጠር፣ ቆይቶም እንደሚወለድ እስከ አስራ ዘጠኝ ዘጠናዎቹ መጀመሪያ ድረስ በውስጤ ሲገላበጥ ቆይቶ፣ በአስራ ዘጠኝ ዘጠና ሁለት ግድም የመጀመሪያውን ቅጂ ቅርጽ ሰጥቼ ፃፍኩት፡፡
 ይሁንና ይህን የመጀመሪያውን ቅጂ እኔ ራሴ መልሼ ስመለከተው፣ ለማለት የፈለኩትንና እኔን ለረጅም ዓመታት ሲንጠኝ የኖረውን፣ ለጓደኞቼ እየተረኩላቸው ሲመሰጡበትና ሲሰክሩበት የነበረው ያ ታሪክ፣ ይህ አሁን ከፊቴ ከምመለከተው ህይወት የለሽ በድን ጋር አንድ ሆኖ አልታይ አለኝ፤ ስለዚህ ጠላሁት እናም ለሚቀጥሉት ከአስር በላይ ዓመታት አስቀምጬ ረሳሁት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ታሪኩን የተረኩላቸው ጓደኞቼ እንዳሳትመው ይወተውቱኝ ነበር፡፡ በመጨረሻ በሚሊኒየሙ ማግስት፣ ያን ፅሁፍ እንደገና አንስቼ፣ እንደገና ተነባቢ በሆነና ቀለል ባለ መንገድ ልጽፈው ወስኜ ገባሁበት እናም እነሆ ከሃያ ዓመታት በላይ ፈጅቶ አሁን በታተመበት ቅርጽ ለሕትመት ተዘጋጀ፡፡
ስለዚህ ይህን ድርሰት የሚያነብ ልባም ተደራሲ፣ በንባቡ ውስጥ ሳለ የዓለማችን ታላላቅ ጠያቂዎች ያነሱትን ታላቅ የህልውና ጥያቄ ለማንሳት ይገደዳል፡፡ ስለዚህ ለጥቂት የንባብ ሰዓታት ቢሆንም እንኳ ፈላስፋ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በዚህ ድርሰት ውስጥ የሞከርኩት ሙከራ ይህ ነው፡፡ ሙከራው ግቡን ባልመታ ጊዜ ‹‹ያልተሳካ ሙከራ›› ተብሎ ይቅርታ ይደረግለኝ ዘንድ እለምናለሁ፡፡ ግቡን በመታ ጊዜ ደግሞ ደራሲና ተደራሲ በጽሁፍ ውስጥ ተገናኙ ማለት ነው፡፡

Read 2951 times