Print this page
Saturday, 10 March 2012 12:12

ቼልሲ አሰልጣኝ ለማግኘት ይቸገራል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከሳምንት በፊት አንድሬስ ቪአስ ቦአስን ያሰናበተው ቼልሲ ለክለቡ የሚመጥን ብቁ አሰልጣኝ ለማግኘት እንደሚቸገር የተለያዩ መረጃዎች ገለፁ፡፡ የፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች ማህበር የቼልሲ አሰልጣኞችን የማባረር አባዜ አሳፋሪ ብሎታል፡፡ ከፖርቱጋሉ ክለብ ፖርቶ ጋር በአንድ የውድድር ዘመን የአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫን ጀምሮ 3 የዋንጫ ክብሮችን ካገኙ በኋላ በቼልሲ የተቀጠሩት አንድሬስ ቪላስ ቦአስ በስታምፎርድ ብሪጅ ለ10 ወራት ሲሰሩ ባደረጉአቸው 38 ጨዋታዎች 19አሸንፈው፣ በ10 አቻ በመለያየትና በ9 ተሸንፈው ባልረባ ውጤት ድንገት ተባርረዋል፡፡ በ34 ዓመታቸው ቼልሲን ሲይዙ ሃላፊነቱ ይከብዳቸዋል በሚል ከጅምሩ የተሟረተባቸው አሰልጣኙ ከሊጉ የዋንጫ ፉክክር መውጣታቸው፤ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸው አርኪ አለመሆኑና በእድሜ እኩያ ከሚሆኗቸው የቼልሲ ተጨዋቾች ጋር ሊስማሙ አለመቻላቸው የመባረራቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡

ቦአስ ከ256 ቀናት የስራ ቆይታ በኋላ ከስታምፎርድ ብሪጅ  በመሰናበትም አጭሩን ቆይታ በክለቡ ያደረጉ ሲሆኑ ባለፉት 9 የአብራሞቪች ባለቤትነት ዓመታት ከቼልሲ የተባረሩ 6ኛው አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡ በ3 የውድድር ዘመናት በክለቡ የሰሩት ሞውሪንሆ ስኬታማነት ለማሻሻል መክበዱ ሌሎች አሰልጣኞች ተረጋግተው እንዳይሰሩ ምክንያት መሆኑም ይነገራል፡፡ ጆሴ ሞውሪንሆ ሁለት የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ አከታትለው በመውሰድና ሁለት የኤፍኤ ካፕና የሊግ ዋንጫ ድሎችን አስመዝገበው በ5 የዋንጫ ክብሮች መሰናበታቸው ይታወቃል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ቼልሲ በቀጠራቸው እና ባባረራቸው አሰልጣኞች 64 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭ አድርጓል ያለው የዴይሊ ሜል ዘገባ ቼልሲ ከዋንጫ ፉክክር በመራቁ የፋይናንስ ቀውስ መግባቱን በማመልከት ዘንድሮ 67.7 ሚሊዮን ፓውንድ መክሰሩን ገልጿል፡፡ ለተጨዋቾችና አሰልጣኞች የሚከፍለው 69 ሚሊዮን ፓውንድ ከታላቅ ክለቦች ተርታ የሚያሰልፈው ቢሆንም ወጪው የተፈለገውን ስኬት አለማስገኘቱና በተለይም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አብራሞቪች የሚያልሙትን ክብር አለማምጣቱ ለአሰልጣኞቹ የስራ ዋስትና አደጋ ሆኖ ቀጥሏል፡፡  ቼልሲ ከአንድሬስ ቪያስ ቦአስ ስንብት በኋላ ምትክ አሰልጣኙን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቢመስልም በአፋጣኝ እንደማይሳካለት እየተነገረ ነው፡፡ በተለይ ለክለቡ ስኬት ዳግም የተፈለጉትን ሞውሪንሆን ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ለመመለስ  ቢያንስ 12 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ መክፈል እንደሚጠበቅ የዘገበው ዴይሊ ሜል አብራሞቪች ይህን ውድ ደሞዝ የመክፈል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅምም ያላቸው አይመስልም ብሏል፡፡

 

ሞውሪንሆ በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ የላሊጋውን ክለብ ሪያል ማድሪድ በመልቀቅ በተለይ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መመለሳቸው እንደማይቀር በርካታ ዘገባዎች እየገለፁ ናቸው፡፡ ባለፈው ሰሞን አሰልጣኙ በለንደን ከተማ የመኖርያ ቤት ሲያፈላልጉ መታየታቸው ደግሞ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

አብራሞቪች በቀጣይ ክረምት በባርሴሎና ያለውን ኮንትራት የሚጨርሰውን ፔፔ ጋርዲዮላ ለመቅጠር ፍላጎት ነበራቸው፡፡ በአንፃሩ የክለቡ ደጋፊዎች በሞውሪንሆ መመለስ ከፍተኛ ዘመቻ ማድረግ መጀመራቸው ከቢሊየነሩ ጋር ያለ ግንኙነታቸውን እያወሳሰበው መጥቷል፡፡ የ41 ዓመቱ ፔፔ ጋርዲዮላ ለተጨማሪ አንድ የውድድር ዘመን በባርሴሎና ይቀጥላል መባሉ አብራሞቪች ቀዳሚ ምርጫቸው የሆነውን አሰልጣኝ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል፡፡ አብራሞቪች ከጋርዲዮላ ቀጥሎ የጀርመን የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ጆአኪም ሎውም ለመቅጠር ሞክረዋል፡፡ በጄኔቫ ሆቴል ለቅጥር እንዳነጋገሩት የተናገረው አሰልጣኙ በጀርመን ስራው እስከ 2014 መቆየቱ ጥያቄውን ላለመቀበል ምክንያት እንደሆነበት አስታውቋል፡፡ ቼልሱ ምትክ አሰልጣኙን ለማግኘት በስፋት ጥረት እያደረገ ሲሆን ከሞውሪንሆና ጋርዲዮላ ውጭ በሌሎች 5 አሰልጣኞች ላይ አተኩሯል፡፡ የምእራብ ለንደኑ ክለብ ከቀድሞ አሰልጣኞቹ መመለስ ጋር በተያያዘ ሞውሪንሆን ብቻ ሳይሆን ክላውደዮ ራንዬሪንና ስኮላሪን የመመለስ ፍላጎት እንዳለው የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

ብራዚላዊው ፊሊፕ ስኮላሪ ወደ ቼልሲ መንበራቸው መመለስ እንደማይፈልጉና ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ በስታምፎርድ ብሪጅ ለመስራት ከደፈረ ገሃነም እንደገባ እቆጥረዋለሁ በማለት ተናግረው ጥሪ እንዳይቀርብላቸው ተከላክለዋል፡፡ የቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ራፋ ቤኒቴዝና የቀድሞው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጎራን ኤሪክሰን ግን ቼልሲን በሃላፊነት ለመረከብ  ፍላጎታቸውን በይፋ የገለፁ አሰልጣኞች ናቸው፡፡

ከሮማን አብራሞቪች ጋር አብረን ባንሰራም በተገናኘንባቸው 15 አጋጣሚዎች ሰውዬው እግር ኳስን የሚወዱ ታላቅ ስፖርተ አፍቃሪ ናቸው የሚሉት ስዊድናዊው ኤሪክሰን ቼልሲን እንዳሰለጥን  ጥያቄ ካቀረቡ ሃላፊነቱን ለመረከብ አላመነታም ብለዋል፡፡ ስፓንያርዱ ራፋ ቤኒቴዝ በበኩላቸው ስራ በማፈላለግ ላይ መሆናቸውን ሲናገሩ በሻምፒዮንስ ሊግ፤ እንዲሁም በስፔን በእንግሊዝና ጣሊያን የሊግ ውድድሮች ያለኝ ልምድ ለቼልሲ ሃላፊነት ብቁ ስለሚያደርገኝ ለሚቀርብልኝ የቅጥር ጥያቄ በሬ ክፍት ነው ብለዋል፡፡

 

 

 

Read 3700 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:17