Monday, 05 December 2016 10:07

አቢሲኒያ ባንክ፤ ለ7 በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍአደረገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  አቢሲኒያ ባንክ በቅርቡ ባደረገው የባለአክሲዮኖች 20ኛ መደበኛና 11ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ ለግብረሰናይ ድርጅቶች እንዲለገስ የተወሰነውን የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለተመረጡ 7 ግብረሰናይ ድርጅቶች ሰጠ፡፡
ባንኩ ባለፈው ሳምንት በቅርቡ ለተቀዳሚ ደንበኞች ማስተናገጃ በከፈተው ልዩ ሐበሻ ቅርንጫፍ በተደረገው የርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ ባደረጉት ንግግር፣ ባንካችን ከምስረታው ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት ከበርካታ የግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት ማኅበራዊ ግዴታውን ሲወጣ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዕለቱ ድጋፍ የተደረገላቸው 7 ግብረሰናይ ድርጅቶች፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የ200 ሺህ ብር፣ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የ100 ሺህ ብር፣ ለዓለም የሕፃናት ዕርዳታ ድርጅት 60 ሺህ ብር፣ ርዕይ ለትውልድ የ50 ሺህ ብር፣ ነህምያ ኦቲዝም ማዕከል የ40 ሺህ ብር፣ የጎንደር መልሶ ማቋቋምና ልማት ማኅበር የ25 ሺህ ብር፣ ፍሬገነት ኪዳን ለህፃናት የ25ሺ ብር ቼክ ከባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ከአቶ መሰረት ታዬ እጅ ተቀብለዋል፡፡
“ከተመሰረትን አጭር ጊዜ ቢሆንም ይዘን የተነሳነው ራዕይ ትልቅ ነው፡፡ በ2020 ዓ.ም (ከ11 ዓመት በኋላ ማለት ነው) 10 ሺህ ህፃናት ራዕይ ኖሯቸው አገር የሚቀይሩ ትልቅ ቦታ የሚደርሱ ዜጎችን መፍጠር ነው” ያሉት የርዕይ ለትውልድ ፕሬዚዳንት፤ የድርጅቱ ዓላማ፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ በመጠየቅ የድሃ ቤተሰብ ልጆች ምግብ እንዲበሉ ማድረግ፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችና ዩኒፎርምም ማቅረብ ነው ብለዋል፡፡

Read 1821 times