Monday, 05 December 2016 10:11

የአዋሽ ባንክን የሎተሪ አውቶሞቢል የጅማ ነዋሪ አሸነፉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

 አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ “ከአዋሽ ይቀበሉ! ያሸንፉ” በሚል  ያዘጋጀውን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የቤት አውቶሞቢል የሎተሪ ዕጣ የጅማ ከተማ ነዋሪዋ አሸነፉ፡፡
ባንኩ፤ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ከሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም በተዘጋጀው የሎተሪ መርሐ ግብር የተሳተፉ ባለዕድለኞች ባለፈው ማክሰኞ በዋናው መ/ቤት በተከናወነው ሥነ-ስርዓት፣ ዕድላቸው ያስገኘላቸውን ሽልማት ከባንኩ ኃላፊዎች ተቀብለዋል፡፡
ጥቅምት 14 ቀን 2009 ዓ.ም በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ በሕዝብ ፊት በወጣው ዕጣ 1ኛ ደረጃ የሆነውን ቶዮታ ያሪስ የቤት አውቶሞቢል ከጅማ የአዋሽ ቅርንጫፍ በወሰዱት 137697 የኩፖን ቁጥር ያሸነፉት የጅማ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ዝናሽ አግደው ኦዴሎ ናቸው፡፡ ከመኪናው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሽልማቶች የወጡ ሲሆን 15 ዕጣዎች 295 ሊትር የሚይዙ ማቀዝቀዣዎች፣ 25 ዕጣዎች ባለ 32 ኢንች ሶኒ ኤል ዲ ቴሌቪዥኖች፣ 20 ዕጣዎች ዋሪት የውሃ ማጣሪያዎች፣ 80 ዕጣዎች ሳምሰንግ ስማርት የሞባይል ቀፎዎችና 30 ዕጣዎች በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የሶላር ፓኔሎች ለባለ ዕድለኞች ተሰጥተዋል፡፡
በባንኩ ቅርንጫፎች ከተሰራጩትና የተለያዩ ሽልማቶች ከሚያስገኙት ዕጣዎች መካከል 101 ኩፖኖች በአዲስ አበባና ዙሪያዋ፣ 71 ኩፖኖች በክልል ከተሞች የተሰራጩ ሲሆን በዕለቱ ዕድላቸው ያስገኘላቸውን ሽልማት የወሰዱት የአቶሞቢሏ ዕድለኛ እንዲሁም የአዲስ አበባና አካባቢዋ አሸናፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ በመቀጠልም ብዙ ተሸላሚዎች በሚገኙባቸው በጅማና በአዳማ ከተሞች ዕድለኞች ሽልማታቸውን እንደሚወስዱ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡
ከብሔራዊ ሎተሪ በተገኘ ፈቃድ ለዕጣ የቀረቡት ኩፖኖች 72ሺህ ሲሆኑ በቀጣይም ሌሎች ተመሳሳይ መርሐ ግብሮች ለማካሄድ ባንኩ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ አዳዲስ ሆኑ ነባር ደንበኞች በተሳትፎአቸው እንዲያደምቁት ጠይቀዋል፡፡
ከ22 ዓመት በፊት በ486 ባለአክሲዮኖችና በ24.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ስራ የጀመረው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ፤ በአሁኑ አቅት ከ3,600 በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ በብድር የተሰጠ ገንዘብ ከ17.6 ቢ. ብር በላይ፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከ34.8 ቢ. ብር በላይ መድረሱን፣ በ2015/16 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግል ባንኮች በተከፈለ ካፒታል፣ በጠቅላላ ሀብት፣ በተቀማጭ ገንዘብና ብድር መጠን፣ በትርፍና በቅርንጫፎች ብዛት በቀዳሚነት ማጠናቀቁን አቶ ፀሐይ አስታውቀዋል፡፡

Read 2373 times