Monday, 12 December 2016 11:43

የሆላንድ ካር ባለቤት ለጠ/ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     የሆላንድ ካር ኩባንያ ግማሽ ባለሀብት የሆኑት ኢ/ር ታደሰ ተሰማ፤ በኩባንያቸው ላይ እየተደረገ ያለውን ምርመራ በተመለከተ ለጠ/ሚኒስትሩና ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቤቱታ አቀረቡ፡፡
ባለሀብቱ ህዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም ለዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፅሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ፤ “በፍ/ቤት የኪሳራ ውሳኔ የተላለፈበትን ሆላንድ ካር ኩባንያ በተመለከተ የኪሳራውን ሂደት እንዲያከናውኑ በተሾሙት መርማሪ ዳኛ ላይ እምነት አጥቻለሁ›› ብለዋል፡፡
ባለሀብቱ እየተፈፀመ ነው ያሉት በስልጣን አለአግባብ መጠቀምና ሙስና እንዲጣራላቸው ጠይቀዋል - በአቤቱታቸው፡፡
በዘጠኝ ነጥቦች ዘርዝረው እየተፈፀሙ ናቸው ያሏቸውን ስህተቶች ያቀረቡት ባለሀብቱ፤ ኪሳራ አጋጥሞታል የተባለው ኩባንያቸው በአንድ ወቅት በሀገሪቱ ካሉ ኩባንያዎች ከፍተኛ ግብር ከፋይ የነበረና ታማኝ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተብሎ የተሰየመ ድርጅት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  ሆላንድ ካር፤ ዶክ፣ አባይ፣ አዋሽ፣ ተከዜና ናኦሚ የተሰኙ አውቶሞቢሎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ይታወቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡

Read 1823 times