Monday, 12 December 2016 11:47

‹‹ጣዕም ያላቸው ምግቦች ለአንድ ሺህ ቀናት›› መጽሐፍ ተመረቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

    የቪታባይት ኑትሪሽን መሰራችና ስራ አስኪያጅ በሆነችው ወ/ሮ ሙላት ዮሴፍና በወ/ሮ ህሊና በየነ የተዘጋጀው “ጣዕም ያላቸው ምግቦች ለአንድ ሺህ ቀናት” መጽሐፍ ተመረቀ፡፡
መጽሐፉ ባለፈው ሳምንት በ17/19 ቀበሌ መናፈሻ በተመረቀበት ወቅት ወ/ሮ ሜላት እንዳለችው፣ 1000 ቀናት ከእርግዝና እስከ ሁለት ዓመት ያለው ጊዜ (270 የእርግዝና ጊዜ፣ 365 + 365 = 1000) እንደሆነ ገልጻ፣ እነዚህ ቀናት በህፃናት አዕምሮና አካላዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ሚና አላቸው ብላለች፡፡
‹‹ልጆች በዚህ ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድጉበት ወቅት ነው ያለችው ወ/ሮ ሙላት፤ ያንን የሚያደርገው ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ነው። ይህ መጽሐፍ ለእናቶች በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህን ምግቦች እንዴት እንደሚያዘጋጁ፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ የንፅህና አያያዝ፣ የመመገቢያ ቁሳቁሶች፣ ህፃናት እንዴት ምግብ ደረጃ በደረጃ ማስጀመር እንደሚቻል የሚያስረዳ ነው›› ስትል አስረድታለች፡፡
እናት በእርግዝናና በምታጠባበት ወቅት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለባት ያለችው ወ/ሮ ሜላት፣ አንድ ህፃን እስከ 6 ወር የእናት ጡት መጥባት አለበት፡፡ 6 ወር ሲሞላው ፍራፍሬ ወይም በካሮት ወይም በድንች ድልህ ምግብ መጀመር አለበት። እንዲሁም ከሩዝና ከወተት በሚዘጋጁ ምግቦች እንዲጀምሩ ይመከራል፡፡
ሩዝ የሚመከረው በህፃናት ላይ አለርጂ ስለማይፈጥር ነው፡፡ በአትክልትና በፍራፍሬ ድልሆችም መጀመር ይቻላል፡፡ ሰባት ወር ሲሞላቸው ስጋ ዕንቁላል፣ ዓሣ፣… ከሌሎች ምግቦች ጋር አደባልቆ በማዘጋጀት መመገብ እንደሚቻል አስረድታለች፡፡ 150 ገጾች ያሉት “ጣዕም ያላቸው ምግቦች ለአንድ ሺህ ቀናት” መጽሐፍ ለማዘጋጀት አንድ ዓመት ተኩል የፈጀ ሲሆን ዋጋው 150 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 1734 times