Monday, 12 December 2016 11:52

መድረክ፤ዶ/ር መረራ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል

  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል በሚል በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱና መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይትና ድርድር ለማካሄድ ቃል በገባው መሰረት ጊዜ ሳይባክን ወደ ተግባር እንዲገባ መድረክ ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ ዶ/ር መረራ ጉዲና የሃገሪቱን ህግ አክብረው በሠላማዊ መንገድ የሚንቀሣቀሱ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ያለ አግባብ መታሠራቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመድረኩን አባላትና ደጋፊዎች አሳስቧል ብሏል። መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይትና ድርድር ለማካሄድ የገባውን ቃል እውን ያደርጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት የዶ/ር መረራ መታሠር፣ የመድረኩን ተሣትፎ አቅም እንዳያሳጣው ስጋት መፈጠሩን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
ባለፉት አመታት ከኢህአዴግ ጋር በተደረጉ ድርድሮች ላይ መንግስት ሽብርተኛ ከሚላቸው ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ ማለት፤ ‹‹ስምምነት ተፈራርሞ ድርጅታዊ ቁርጠኝነት መፍጠር ማለት ነው” የሚል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን የጠቀሰው መድረክ፤ ይህን ስምምነት እስካሁንም አክብሮ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቋል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው እስካሁን ድረስ ከገዥው ፓርቲ ምንም አይነት ቅሬታ ቀርቦበት አያውቅም ያለው መድረክ፤ የዶ/ር መረራ እስራት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ ውጪና መድረክ ከገዥው ፓርቲ ጋር ከደረሰበት የጋራ መግባባት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ እስራቱ ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡
‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንድ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በሃገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ገለፃ ማድረግን አይከለክልም ያለው መግለጫው፤ “ዶ/ር መረራ ከሽብርተኞች ጋር ተገናኙ ለተባለውም፣ አንድ አለም አቀፍ ስብሰባ ቀርቶ በሰንበቴ ማህበር ስብሰባዎች እንኳን መቀመጫ ለእንግዳ የሚሰጠው አዘጋጁ ነው፤ የተጠራው እንግዳ በመረጠው ስፍራ አይቀመጥም፤ ከዚህ አንፃር ከሽብርተኛ ጎን ተቀምጠህ ተገኝተሃል ማለት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረስ ነው” ብሏል፡፡
በሌላ በኩል፤ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት ላነሳቸው ብሶቶችና ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመሻት፣ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የሚያስችል ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲመቻች መድረክ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የመድረክ ምክትል ሊ/መንበርና የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እንዲሁም የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገውንና ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር መገናኘትን የሚከለክለውን አንቀፅ ጥሠው በመገኘታቸው፣ ህግ ለማስከበር ሲባል መታሰራቸውን ባለፈው ሳምንት) መንግስት መግለፁ ይታወሳል፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሣለኝ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መደበኛ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው ችግር እንደሌለ ገልፀው፤ ህጉን ጥሠው ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት ‹‹የሽግግር መንግስት ስለማቋቋም የሚመክሩን የተቃዋሚ አመራሮች እንዳሉ መጥቀሳቸው አይዘነጋም፡፡

Read 3949 times