Monday, 12 December 2016 11:54

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በግጭቶች የደረሰውን ጉዳት እየመረመርኩ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በአማራና ኦሮምያ ክልሎች የምርመራ ቡድን ልኳል

     የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተቀሰቀሱ ተቃውሞና ግጭቶችን ተከትሎ የደረሱ ጉዳቶችን 10 ቡድኖች አዋቅሮ እየመረመረ መሆኑን ገለፀ፡፡
ኮሚሽኑ በክልሎቹ ምርመራ ሲያካሂድ የአሁኑ ሁለተኛው ዙር መሆኑን ጠቅሶ በኦሮሚያ ክልል እያንዳንዳቸው ከ3 እስከ 4 አባላት ያሏቸው 6 ቡድኖችን፣ በአማራ 4 የምርመራ ቡድኖችን ማሰማራቱን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ወደ አማራ ክልል የተላከው የምርመራ ቡድን፤ በምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎንደርና ደቡብ ጎንደር ላይ የተሰማራ ሲሆን የኮሚሽኑ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አባዲ ገልፀው፤ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተላከው ቡድን ደግሞ በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ አርሲና ምስራቅ አርሲ፣ ባሌ  ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋና ወደ ጉጂ ዞን መላኩን አስታውቋል፡፡
ቡድኖቹ ምርመራቸውን ለማጠናቀቅ ከ20-25 ቀናት ይፈጅባቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ በአሁን ወቅት ምርመራቸውን እያገባደዱ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል፡፡ ምርመራው ሲጠናቀቅ ሪፖርቱ ተጠናቅሮ፤ ከዚህ በፊት እንደተደረገው፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የእሳት ቃጠሎ ምርመራ ተጠናቆ ሪፖርቱ ለፓርላማ እንደሚቀርብ መገለፁ የሚታወስ ሲሆን አቶ ብርሃኑ መቼ ይቀርባል ተብለው ለተጠየቁት፤ ‹‹በቅርቡ ይቀርባል›› ብለዋል፡፡

Read 2538 times