Monday, 12 December 2016 12:01

አቶ ሙሼ ሰሙ ስለ ግምገማ፣ ተሃድሶና የምሁራን ካቢኔ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ በሚል በጀመረው ዘመቻ፣ በየክልሎቹ ግምገማና የካቢኔ ለውጦች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ህዝብን
በበደሉ የስራ ኃላፊዎችም ላይ በቁርጠኝነት እርምጃ እንደሚወስድ በይፋ እየገለፀ ነው፡፡ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ
ሙሼ ሰሙ መንግስት እየተከተለ ባለው አቅጣጫ ላይ ጥያቄና ጥርጣሬ ያነሳሉ፡፡ አቶ ሙሼ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግምገማውን፣ ተሃድሶውንና የስልጣን ሹም ሽሩን ከህዝብ ጥያቄዎች አንጻር
በመተንተን የራሳቸውን የመፍትሄ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡

መንግስት በፌደራልም ሆነ በክልል በተዋቀሩ አዳዲስ ካቢኔዎች ውስጥ ባልተለመደ መልኩ ምሁራንን በብዛት ማካተቱ የለውጥ ተስፋ የሚያጭር ነው ይላሉ?
በመጀመሪያ መንግስት ካቢኔውን እንደገና ለማዋቀር መፈለጉ ህብረተሰቡ ካደረገው ጫና የመጣ ይመስላል፡፡ ግን ዋናው ቁም ነገር አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየቀረበ ያለው ጥያቄ በቅርፁም ሆነ  በይዘቱ ላለፉት 10 እና 15 ዓመታት ሲቀርቡ ከነበሩት የተለየ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ላለፉት ዓመታት ለውጥን፣ መሻሻልን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ፍትህን፣ የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ሲጠይቅ ነው የኖረው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ጥያቄዎች በመንግስት በኩል እንደ ትልቅ ቁም ነገር ተቆጥረው አያውቁም፡፡ እንዲያውም ኢህአዴግ የበለጠ ስልጣንን የማጠናከር እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነው የተመለከትነው፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት የነበሩ የምርጫ ውጤቶችን፣ የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴንና በሚዲያዎች ላይ የተደረጉ ዘመቻዎች ስናይ፣ ስልጣንን የበለጠ የማጠናከር ነገር እንደነበር እንገነዘባለን፡፡ በነዚህ ዓመታት ስልጣንን አላልቶ፤ ምህዳርን ከፍቶ እንቅስቃሴ ሲደረግ አላየንም፡፡
አሁን እየተደረገ ያለውን ነገር ስንመለከት ደግሞ በመጀመሪያ “ምንድን ነው የማህበረሰቡ ጥያቄና ፍላጎት?” የሚለውን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ካቢኔ ተለውጧል ግን በትክክል ሰው የሚማረርባቸውን ጉዳዮች ለይቶ በማወቅ የተሰራ ነው ወይ? ስንል አንደኛ፣ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር ቁጭ ብሎ ጋር አልተወያየም፤ ስለዚህ አሁንም ትክክለኛውን የህዝብ ጥያቄ ያወቀ አይመስለኝም። ለራሱ የፈጠረውን ጥያቄ ነው እየመለሰ ያለው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ካልገመገመ ከራስ የመነጨ ውሳኔ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ጥያቄውን ሳይረዳ የራሱን ጥያቄ አዘጋጅቶ፣ ለዚያ ጥያቄ መልስ እየሰጠ ነው ያለው፡፡
ሌላው ከስልጣን የተነሱት ሰዎች፤ ”በምንድን ነው የተገመገሙት?” የሚለውን አናውቅም፡፡ የሰሩት ስህተት ምንድን ነው? ይሄ አይታወቅም፡፡ እነዚህ ሰዎች ሲነሱ ግምገማው ምን ነበር? በግምገማው ምን ጉዳዮች ነበር የታዩት? የተገመገሙበትና ሊያሟሉት ያልቻሉት ጉዳይ ምን ነበር? እነዚህ አይታወቁም፡፡ ጉዳዩ የመንግስት ሳይሆን የፓርቲ ግምገማ ቢሆን ኖሮ የፓርቲ የውስጥ ጉዳይ አይመለከተንም ልንል እንችል ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን አሁን የመንግስት ሹመኞች ናቸው፡፡ በህዝብ ሀብትና ሀገር ላይ ነው የሚወስኑት፤ ስለዚህ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ይሄ የፓርቲ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ነገሮችን አድበስብሶ፣ እነዚህን ሰዎች አንስቶ በሌላ ተክቶ እንደገና ደግሞ የተነሱትን ራቅ አድርጎ ወደ ሌላ ቦታ እየመደበ ነው ያለው፡፡ ኃላፊነትን በአግባቡና በብቃት አለመወጣት እንኳ ከሆነ፣ የነበረባቸው የብቃትና ኃላፊነት ያለመወጣት ችግር ምን ነበር? ለምንድን ነው ኃላፊነታቸውን ያልተወጡት? ይሄን ማወቅ ነበረብን፡፡ አስተዳደራዊ በደል ከተባለም፣ ምንድን ነው በደሉ? ይሄንንም ማወቅ ነበረብን፡፡ ማህበረሰቡ’ኮ እየደረሰበት ያለው ችግር ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሌላው የአስተዳደራዊ ብቃት ማነስ ነው፡፡ ይሄ ሲባል ግን የትምህርታዊ ብቃት ችግር ማለት አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ልምድና በቢሮክራሲ ያለፉበት መንገድም ሊታይ ይችላል፡፡
ምሁራኑ የማህበረሰቡን ጥያቄ መመለስ የሚችሉ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው ናቸው ወይ? ብለን ስንጠይቅ፣ አይደሉም፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም እጩዎች ናቸው፡፡ ይሄን ስል ዩኒቨርሲቲውን እየተቃወምኩ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ተቋም የራሱ ባህሪ አለው፡፡ ለምሳሌ በህግ ረጅም ዓመት የማስተማር ልምድ ያላቸው ሰዎች በዳኝነት ቢቀመጡ ስራውን ሊሰሩ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ፍትህንና ፍትሃዊ ርትዕን በመስጠት ሳይሆን በማስተማር ነው ጊዜያቸውን ያሳለፉት፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፡፡ ምሁርነትን ብቻ መስፈርት ማድረግ የሚያመጣው አንዱ ችግር ይሄ ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን ምናልባት በማስተማርና በምርምር ስራቸው ምንም የብቃት ጥያቄ ላይነሳባቸው ይችል ይሆናል፤ ግን አሁን ለተመደቡበት ቦታ ብቁ ናቸው ወይ? ይሄ አጠያያቂ ነው፡፡ ብቁ ካልሆነ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ሌላው እነዚህ ሰዎች ከሙስና የፀዱ ናቸው ወይ? በዘመድ አዝማድ ባለመስራት የነበራቸው የኋላ ታሪክ ምንድን ነው? የሚለውም መታየት አለበት። በዚህ የአመራሮች ለውጥ ላይ “ኢህአዴግ ቁርጠኛ ነው” እንዳንል የሚያደርገን፣ ከስልጣን የተነሱት ሰዎች በምን ምክንያት እንደተነሱ አለመታወቁና ምን ተጠያቂነት እንደነበረባቸው አለመገለጹ ነው። በሙስና ነው የተነሱት ከተባለ፣ ለምን ፍ/ቤት አልቀረቡም? ህዝብ በድለዋል ከተባለ፣ ለምን አስተዳደራዊ እርምጃ ሲወሰድባቸው አናይም? ማንኛውም የመንግስት ተሿሚ፤ ከፓርቲ መሃልም ይምጣ፣ ከህዝብ በቀጥታ ተመርጦ፣ በህዝብ ፊት ቃለ መኃላ ከፈፀመ፣ ያንን ቃለ መሃላ አለማፍረሱን ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩን ቆርጦ ለመጣልና ለወደፊት የሚመጡትንም አመራሮች በሚያስተምር መልኩ አይደለም ሁሉም ነገር እየተካሄደ ያለው፡፡ ይሄ የተለሳለሰ ሽግግር ነው ማለት እንችላለን፡፡ ሹም ሽረቱ ከአንዱ የተደላደለ መሬት ወደ ሌላ የተደላደለ መሬት እንደመሄድ ነው የሆነው፡፡
ይህ በምሁራን የተዋቀረ ካቢኔ ምን አይነት ለውጦች ያመጣል ብለው ይጠብቃሉ?
የህዝቡ ጥያቄ ምንድን ነው ተብሎ ካልተነሳ፣በራስ ጥያቄ ተነስቶ ምላሽ ለመስጠት መሞከር ብዙም ውጤታማ አያደርግም፡፡ ኢህአዴግም ከራሱ ጥያቄ ነው የተነሳው፡፡ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረበትን ምስቅልቅል ነው እንጂ የሚያስበው፣ ይሄ ምስቅልቅል ማህበረሰቡ ምን አይነት ጥያቄ እንዲያነሳ እንዳደረገው ለማሰብ አይፈልግም፡፡ አሁን ህዝቡ ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል መኖር አለበት ብሎ ሲጠይቅ፣ የፖሊሲ አቅጣጫን ነው መመርመር የሚያስፈልገው እንጂ ግለሰቦችን አይደለም ተጠያቂ ማድረግ የሚያስፈልገው። ግለሰቦቹ በብቃት ማነስ ወይም በሌላ የፈጠሩት ችግር ካለ፣ ፖሊሲው ወይም የፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው ነው ያንን ያደረጉት። ስለዚህ እንደኔ አሁን ጥያቄው የተነሳው፣ በፖሊሲ አቅጣጫ ላይ ነው፤ እንጂ ግለሰቦች በድለውናል የሚል አይደለም፡፡ ውሃ ልማት ወይም መብራት ኃይል በድሎናል የሚል ጥያቄ ሲነሳ አላየንም፡፡ ፖሊሲው እንደ ፖሊሲ በየአካባቢው የማንነትና የመሬት ጥያቄን አስነስቷል፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ ሲነሳ እዚህ ውስጥ ያለው አንዱ ስራ አጥነት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ለመቅረፍ የሚያስችል የፖሊሲ አቅጣጫ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለፈው ፖሊሲ በቂ የስራ እድል ለመፍጠር አላስቻለም ማለት ነው፡፡ ይሄ በምንም መመዘኛ የግለሰብ ችግር ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ መልስ እየተሰጠ ያለው ግን የግለሰብ ችግር ተደርጎ ነው፡፡
ብዙዎች እንደ “የዋህነት” ሊቆጥሩት የሚችሉትን ጥያቄ ላንሳ፡፡ አዳዲሶቹ የምሁራን ሹመኞች ከፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ የመወሰን አቅም ሊኖራቸው የሚችልበት ዕድል ይኖራል?
የተሾመው ሰው ከሰማይም ይምጣ ከምድር ሊሰራ የሚችለው ሲስተሙ ወይም ፖሊሲው በፈቀደለት ልክ ነው፡፡ ይሄን ሲስተም ለማሻሻልና አዲስ አሰራር ለማምጣት አቅም ያለው ሰው ቢሆን እንኳ እድሉ ካልተሰጠው በነበረው ሲስተም ወይም ፖሊሲ ከመስራት ውጭ ምርጫ የለውም፡፡ እኔ እነዚህን ሰዎች ባላውቃቸውም ገለልተኛ ናቸው የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ፖሊሲ የሚያስፈፅሙ ሰዎች ሲመጡ፣ በፖሊሲው አምነውና ተጠምቀው የመጡ ካልሆነ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ሊያስፈፅሙ አይችሉም። ስለዚህ ገለልተኛ ናቸው የሚለው አያስኬድም። ሰዎቹ በፖሊሲው አምነው ለማስፈፀም የመጡ እንደ መሆናቸው ስለ ገለልተኝነታቸው ማንሳት ተገቢ አይሆንም፡፡ ከፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ የመወሰን አቅምም ሊኖራቸው አይችልም፡፡
መንግስት/ኢህአዴግ “በ1993 የተደረገው ተሃድሶ ያመጣቸው ለውጦች በግልፅ ታይተዋል፤ አሁንም የሚደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል” በሚል ይሞግታል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? ሁለቱ ተሃድሶዎች ምንና ምን ናቸው?
በኔ እምነት በ1993 የተካሄደው ተሃድሶ፣ የፖሊሲም ለውጥ የታየበት እንዲሁም የግለሠቦችንም ሚና ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮ እስከ 1993 ይህቺን ሃገር ወዴት አቅጣጫ ይዞ እንደሚሄድ እንኳ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ ስራው ዝም ብሎ ሃገር የሚጠብቅ የፖሊስ ስራ ዓይነት ነበር፡፡ ህግና ፍትህን የሚያስከብር እንጂ ሃገሪቱ በኢኮኖሚና ልማት ወዴት መሄድ እንዳለባት በፖሊሲና ስትራቴጂ ያስቀመጠው ነገር አልነበረውም፡፡  በወቅቱ የተፈጠረው የተሃድሶ አጋጣሚ ግን የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በግልፅ እንዲቀይስ አድርጎታል፡፡ ጠቃሚና ጠቃሚ ያልሆኑ ግለሠቦችንም መዝኖ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከሲስተሙ ለማስወጣት ችሏል፡፡ ዛሬም ያስፈልግ የነበረው የዚያ ዓይነት ተሃድሶ ነው፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡
አንድ ፖሊሲ ለ15 ዓመት ተሠርቶበት የሚፈለገውን ያህል የስራ እድል ካልፈጠረ፣ ዲሞክራሲውን ካላሳለጠ፣ ፍትህን ማስፈን ካልቻለ፤በቅጡ መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ይሄ እንደውም በየ5 ዓመቱ ከሚቀመጠው የእድገት እቅድ ጋር እየተመረመረ መሄድ የነበረበት ነው። አሁንም ይሄን ፖሊሲ ይዞ ሰው መለወጥ ብቻ ያዋጣል በሚል መጓዝ ለሃገሪቱ ችግሮች ትርጉም ያለው መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ህዝቡ ለጥያቄው ተገቢ መልስ ብቻ ሳይሆን ጥያቄውንም በሚገባ ሊያዳምጠው የሚችል አካል ማግኘት አለበት፡፡
በፊት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለምንም ማቅማማት በምርጫ ውስጥ ይሳተፉ ነበር። ግን በሂደት ትርጉም አጣ፡፡ ትርጉም ሲያጣ ደግሞ ተቃዋሚዎችም ህዝቡም ተስፋ ቆረጡ። ሆኖም ኢህአዴግ ቅሬታዎችን ሰምቶ፣ ለለውጥ አልተነሳሳም፤ ከማጥላላት በስተቀር፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት በብዙ ጉዳዮች ስናይ፣ ተስፋዎች ተጓድለዋል። ማህበረሰቡ ውስጥ ተስፋ ማጣት ብቻ ሳይሆን አቅጣጫ ማጣትም ይስተዋላል፡፡ ተስፋ ማጣቱ ሃገሪቱን በሚጎዳ የተሣሣተ አቅጣጫ እንዲጓዝ ነው እያደረገው ያለው፡፡ ከዚህ ለመዳን ዋናው መሆን ያለበት ከማህበረሰቡ ከራሱ ጥያቄ ተነስቶ መንግስት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን በሚገባ ማሣየት ነው፡፡ አሁን ግን እየተደረገ ያለው የኢህአዴግን የውስጥ በሽታ ማከም ነው፡፡ ከስልጣን ያወረዳቸውን እንኳን ያወረደበትን ምክንያት ገልፆ ለመቅጣት ድፍረቱን አጥቷል፡፡ ስለዚህ ለኔ ይሄ ተሃድሶ  ለ3ኛ ጊዜ የተደረገ ቢሆንም ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ከ1993 ተሃድሶ በስተቀር በ1998 ሆነ አሁን እየተደረገ ያለው ተሃድሶ የተለየ ነገር የላቸውም፡፡
የተሃድሶው አንዱ አካል ግምገማ ነው፡፡ በግምገማው ላይስ አስተያየትዎ ምንድን ነው?
አካሄዱ ትክክል አይደለም፡፡ መጀመሪያ ጥያቄ ያቀረበውን ማህበረሰብ ነበር ማወያየት የሚገባው። ጥያቄ ያቀረበውን ማህበረሰብ ትቶ፣ በራስ ጥያቄ መነሻነት መልስ ሰጥቶ ከወሰኑ በኋላ ህዝብ አወያያለሁ ማለት ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። ምክንያቱም አሁን ሁሉም ነገር ተጠናቋል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ህዝቡን ምንድን ነው የሚጠይቁት? ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌያለሁ ከተባለ በኋላ እንዴት ነው በድጋሚ ማህበረሰቡን እናወያያለን የሚባለው? ትክክለኛው አካሄድ መጀመሪያ ህዝቡን አወያይቶ፣ በሙሉ ነፃነትና ድፍረት የሚሰማውን እንዲናገር አድርጎ፣ ከዚያ በኋላ ወደ ፓርቲ ውይይት፣በመቀጠል ወደ መንግስት መዋቅር ማሻሻያ መሄድ ነበር፡፡ ግን----አልሆነም፡፡
መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ በፓርላማ በዓመት ሦስቴ እየገቡ የሚሳተፉበት አሰራር ለመቅረጽም ማንዋል እየተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ ይሄ ተስፋ ሰጪ ዜና ሆኖ ሳለ በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚው ጎራ አመራሮችና አባላት እየታሰሩ ነው የሚል አቤቱታ ከፓርቲዎች እየቀረበ ነው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?
ማስታረቅ ከተፈለገ ሆደ ሰፊነት ያስፈልጋል። በሆደ ሰፊነት ነገሮች መታየት አለባቸው። ልዩነትና ቅራኔዎች ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ፣ በዚያ ዙሪያ ላይ ብቻ መንቀሳቀስ የሚፈለገውን ለውጥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ያሰናክለዋል። ተቃዋሚዎች በተናገርን ቁጥር እንታሰራለን፣ በጠየቅን ቁጥር ህልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል እምነት የሚያሳድሩ ከሆነ፣ ኢህአዴግ በአንድ እጅ ለማጨብጨብ ይገደዳል፡፡ በህዝቡ ውስጥ ተቃዋሚዎች ትልቅ መሰረት እንዳላቸው መታመን አለበት፡፡ እነሱን አግልሎና በውጥረት ውስጥ ከትቶ፣ ከህዝብ ጋር ብቻ ተነጋግሬ ችግሮችን እፈታለሁ ማለት፣ተቃዋሚዎችም የህዝብ አካል መሆናቸውን መርሳት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ኃላፊነት እንዳለባቸው አምኖ፣ የህዝብ ጥያቄን ሲያነሱ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ተቃዋሚዎች በገዥው ፓርቲና በህዝብ መካከል ድልድይም ናቸው፡፡
ማህበረሰቡ ሀሳቤን መግለፅ ያሳስረኛል የሚል ስጋት እንዲያድርበት ማድረግ ብዙም አይጠቅምም፡፡ ይሄ ወቅት የትዕግስት፣ የጥሞና፣ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የመቻቻል ወቅት ነው፡፡ ማንኛውም የሚያስከፋ ሀሳብ ሲፈጠር፣በፍጥነት ወደ መድረክ መጥቶ፣ አድምቶ ተወያይቶ ወደፊት ለመሄድ መሞከር እንጂ ቆርጦ የመጣል መሆን የለበትም፡፡ ለእያንዳንዱ ጥያቄ ቆርጦ የሚጥል መልስ የሚመጣ ከሆነ፣ ሰው አሁንም ሀሳቡን ከመግለፅ ያፈገፍጋል፡፡ ሀሳቡን አምቆ መቀመጡ ደግሞ አንድ ቀን ገንፍሎ ሲወጣ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፡፡ በምክንያት የሚመራ ቁጣ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ትዕግስቱና መቻሉ በመንግስት በኩል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በእጁ አለ፤ ማሰርና መቅጣት የመጨረሻው መፍትሄ ነው መሆን ያለበት፡፡
በመጨረሻ ----- የአገሪቱ መጻኢ ዕድል ምን ይሆናል ብለው ይገምታሉ?
ይሄ አዲስ ስርአት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ጀምሮ ህዝቡ በትልቅ ተስፋ ነው የኖረው፡፡ በሚፈልገው ፍጥነት ሀገሪቱ አድጋ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተፈተው፣ ሀሳቡን በነፃነት እየገለፀ፣ አማራጮች በስፋት እየቀረቡ አይደለም እስከ ዛሬ የመጣነው፡፡ ብዙዎቹ ነገሮች ጭላንጭሎች ናቸው፤እየጎለበቱና እያደጉ መሄድ ነበረባቸው፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ አናወራም ነበር፡፡ ከ97 በፊት በዲሞክራሲና በምርጫ ረገድ የተሻሉ ተስፋዎች ነበሩ፡፡ በኋላ ግን እነዚህ ነገሮች ደብዝዘዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ስር የሰደደ ድህነትና የፍትህ እጦት አንፃር በጣም ብዙ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ለነዚህ ፍላጎቶች የበለጡ ተስፋዎች እንዲፈነጥቁ አለመደረጉ ወደ አመፅና ግርግር ይወስዳል፡፡ ይሄ ደግሞ ሀገር ነው የሚያፈርሰው፡፡ በምንም መልኩ የሚደገፍ አይደለም፡፡
አሁንም ኢህአዴግ ተሃድሶ አይደለም የሚያስፈልገው፤ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ተረድቶ፣ ተስፋ ሰጪ በሆነ መንገድ መልስ መስጠት ነው ያለበት፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም የተጠራቀሙ ችግሮች በአንድ ጀንበር ሊፈታ አይችልም፡፡ ግን ህዝቡ እምነት ሊያድርበትና ብሩህ ተስፋ ሊያይ ይገባል፡፡ ነገሮች ይለወጣሉ፣ ይሻሻላሉ የሚል ተስፋ እንዲሰንቅ መደረግ አለበት፡፡
ሌላው የፕሬሱና የተቃዋሚዎች መዳከም የፌስ ቡክ መጫወቻ ነው ያደረገን፡፡ የፅንፈኛ ኃይል በሀገራችን ጉዳይ የሚፈተፍትበት እድል ነው የፈጠረው፡፡ ይሄ ደግሞ አቅጣጫ መሳትን ያመጣል። ማህበረሰቡ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ወጥ አቋም እንዳይዝ አድርጎታል፡፡ ጋዜጦች መዳከማቸው ተስፋ የሚያጨልም ነው፡፡ እነዚህ ተስፋዎች መፍካት አለባቸው፡፡ ዲሞክራሲ ይሄው ነው፣ ሌላ ምስጢር የለውም፡፡  

Read 2617 times