Monday, 12 December 2016 12:06

በገዛ ዳቦዬ…

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(1 Vote)

     ዛሬ በሌላ ሰበብ በጨረፍታም ቢሆን ለማየትና ለማሳየት የምሞክረው አሜሪካ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በንግዱ ዘርፍ ተሳታፊነት ነው። ዲያስፖራ አላልኩም! ቃሉን ስለማልወደው ነው! ሌላ ቀን እንወያይበታለን!
ገና አሜሪካ እንደመጣሁ 1984 (1992)፣ በፊት የሚያውቁኝና አዲስ ያወቁኝም አሜሪካኖች ዋሺንግቶን ዲሲ፤ ጆርጅ ታዎን(Goergetown) በሚባለው የሀብታሞች መንደር፤ አበሻ ምግብ ቤት ምሳ ጋበዙኝ። በጫወታችን መካከል በእንግድነቴ በዞርኩበት ስለ ኢትዮጵያውያን የታዘብኩትንና ያለኝን አስተያየት ሰጠሁ። ወረዱብኝ! በተለይም ዲን ጀምስ ፖል (James Paul) ወረዱብኝ። “አንደኛ እንደ ህግ ባለሙያ አልተናገርክም! በቂ ማስረጃ ሳትይዝ ወደ ድምዳሜ ተሸጋገርክ! ሁለተኛም እዚህ ያሉትን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ባህርይ ልብ አላልክም። ኢትዮጵያዊው በተፈጥሮ ልታይ ልታይ የማይል (Low Profile) ሕዝብ ነው። እንጅ ለመሆኑ ከአፍሪቃ የትኛው አገር ነው ቤተክርስቲያናት፤ መስጊዶች፤ የባህል ማእከሎች (Community Centers)፤ የምግብና ሌሎች አገራቸውን ነክ የሆነ ነገር ያዘጋጀና ያደራጀ በከፍተኛ ሥልጣንና በዩኒቨርስቲዎቹ …” ይቅርታ ብጤ ጠይቄ ተለያየን። ከዚያ ወዲህ የበለጠ ልብ እንድል ረድቶኛል፡፡
*   *   *
የዛሬ ወር ገደማ ይመስለኛል የትራምፕን የአሜሪካንን ፕሬዚደንት ምርጫ ማሸነፍ ሰበብ ሆኖ “በማግስቱ!” የሚል ጽፌ ነበር። አዲሳባ አዲስ አድማስም ላይ ወጥቷል። እንዳሉኝ ከሆነ በሶሻል ሚዲያ ቁጥር ስፍር የሌለው ሰው ማንበብ፣ አስተያየት መስጠት ብቻ ሳይሆን አዳርሰውታልም (Share)። ደስ አለኝ! “የወለዱትን ሲስሙለት የደገሱትን ሲበሉለት!” እንደሚባለው መሆኑ ነው። “በማግስቱ!” መዝጊያው ላይ አንዳንድ ስለ አሜሪካን የምታዘባቸውን አልፎ አልፎ ማቅረብ እሞክራለሁ ብዬ ነበር። ይኸ ያ መሆኑ ነው! የትራምፕን መመረጥ ጥቁር አሜሪካውያን (Afirican Americans) እንዴት እንዳዩት በጨረፍታ ለማየትና ለማሳየት ሙከራ መሆኑ ነው።
የዛሬ አመት ይሁን እንዲያ ሌላ የጻፍኩትም ነበረኝ። ሙሉ ለሙሉ አላስታውሰውም። የማስታውሰውን ያክል፣ ካለሁበት ከዳላስ ወደ ዋሽንግቶን ዲ.ሲ ለመብረር ዳላስ Love Field Airport  ሄድኩ። ፈታሹ የያዝኩትን ቡና “ድፋው!” አለኝና ደፋሁት። የሚጠጣ ነገር የታሸገም ቢሆን አውሮፕላን ላይ ይዞ መውጣት ከተከለከለ ቆይቷል። ለወዳጆቼ ይሆናል ብዬ የገዛሁትን ዊስኪና የወይን ጠጅ “ወይ ጠጣው ወይ ድፋው!”አለኝ። ሰጠሁት እንጅ አልደፋሁትም! (የጸጥታው ጉዳይ ነው።) በዛሬው ዘመን ፈንጂ ምን፣ ማን መስሎ እንደሚመጣ አይታወቅምና! “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!” የሚሉት አይነት መሆኑ ነው።
እኔ አውሮፕላን መብረር ይሰለቸኛል! ረዥም ሰአታት ቁጭ የሚያሰኝም በረራ አውቃለሁ። ከዳላስ ዋሽንግቶን ዲ.ሲ 3 ሰአት ከሩብ ነው። ቢሆንም ይሰለቸኛልና ጋዜጦች፤ መጽሐፍት ቡና ይዤ ተሳፍሬ አባብለዋለሁ። አውሮፕላኑ ላይ የሚሰጠውን ነጻ ቡናና ቁራሳ- ቁርስ (Snack) አልወደውም። የለበጣና የይስሙላ ይመስለኛልና! የአሁኑን አላውቅም እንጅ ለአለም አቀፍ በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የጀርመን አየር መንገድን የመሰለ የለም። የአገር ውስጥ በረራ ሁሌም፤ የትም የማስተናገዱ ደረጃው ዝቅ ይላል። ስለዚህም ቡናና ቁርሳ- ቁርስ (Snack) ለመግዛት አውሮፕላን ማረፊያ አዳራሽ(Terminal) ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስል ብዙ ኢትዮጵያዊያንን አየሁ። አሁን አቡነ ባርናባስ የሆኑት አባ ወልደትንሳኤ አንዴ ሎስ አንጀለስ (Los Angeles) ጫዋታ ላይ “አቶ አሰፋ እባክዎ ይተውኝ! አበሻን እንኳንስ ፊቱን አይቼ ከማጅራቱም ቢሆን እለየዋለሁ!” ያሉኝን አስታወሰኝ። እንግሊዝኛውን በቅጡ የማይችሉ፣ በአማርኛ ሲያናግሯቸው በእንግሊዝኛ የሚመልሱትን አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አንስተን ስንጫወት ነበር። አሁን ይህንን ያነሳሁት ኢትዮጵያዊውንና ብዛቱን ለመለየት ችግር አልነበረብኝም ለማለት ነው።
ቡና ፍለጋ የገባሁበት አንዲት ወደ ወጣትነት የምታደላ ልጅ አገኘሁና፤ “አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ!” አልኳት። ይህንን እዚህ አሜሪካኖቹ “ትንሽ ጫዋታ”(Small Talk) ብለው የሚጠሩት አይነት መሆኑ ነው። በአብዛኛው ፈረንጆቹ ዘው ብለው ወደ ፍሬ ሐሳብና ወደሚያከራክርና የሚያወያይ ጉዳይ አይገቡም። ገራ ገሩና የማያሻማው ላይ ያተኩራሉ። ብዙ ጊዜ የአየር ጠባይ ተዘውትሮ፣ የዚህ ደንበኛና መደበኛ ርእስ ወይም ስፖርት ነው። አየሩ ባለቤት የሌለው የሁሉም ንብረት ነውና!
ኢትዮጵያዊው፤ በአብዛኛው፤ ከሰላምታ በኋላ፣”  ምን የአገራችን ነገርኮ…!” ብሎ ይጀምራል። ቢያውቅህም! በቅጡ ባያውቅህም! ዛሬ ጥዋት ተገናኝታችሁ ከሆነም! “የአገር ፍቅር!” መሆኑ መሰለኝ። ቢሆንም ይህን የመሰለ ጉዳይ ቦታና ወቅትም የሚፈልግ ይመስለኛል። “ከምንና ስለምን፣ ከማንስ ጋር!” የሚለው አስቀድሞ የሚታወቅና ካደረው ከሰነበተው ቢጀመር የሚሻል ይመስለኛል። ያለበለዚያ የሚገባውን ክብደት ያጣና የለበጣ ያስመስለዋል ብዬ እፈራለሁ። የሚያወሩትን ማጣትም ሳይሆን ይቀራል? “ዝም አይነቅዝም !” ጥሩ አማራጭ ይመስለኛል። መስመር የለቀቅሁ መሰለኝ! የኔ ነገር!
ታዲያ “አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ፦” ያልኳት ልጅ “አይ! ገና ነው! ገና ነው!” አለችኝ፤ ኮስተርና ፍርጥም ብላ! ጥያቄዬን እንደ ዋዛና ለሰላምታ በር መክፍቻ እንዳቀረብኩት አልቆጠረችውም። የምታየውንና የሚታያትን እውነት የተናገረች መሰለኝ። ከዚህ ተነስቼ አንድ ለማስረጃነት የሚሆን አቀርባለሁ።
*   *   *
7--Eleven የሚባል በአሜሪካ ሁሉ የተዳረሰ፤ዛሬ በሌላውም አለም ያለ፤ ከብዙ አመታት በፊት ቴክሳስ የተጀመረ ኩባንያ ነው። ስሙ 7-Eleven መሆኑ በወቅቱ ያ ሱቅ ክፍት የሚሆንበትን ሰአት ማመልከቱ ነው። ከጥዋቱ 1 ሰአት ይከፈትና ማታ በ5 ሰአት ይዘጋል ለማለት ነው። አሁን ሰአቱ ቀርቶ ስሙ ብቻ ነው የተረፈው! 24 ሰአት ክፍት ነው። እንዲህ አይነት ሱቆችን Convenience Store ይሏቸዋል። ትርጉሙ፡-
Convenience store - Wikipedia
A convenience store is a small retail business that stocks a range of everyday items such as groceries, snack foods, confectionery, soft drinks, tobacco products, over-the-counter drugs, toiletries, newspapers, and magazines.
ዳላስ Downtown መርካቶ ማለት ነው፤ያለው 7-Eleven አንድ ሲቀር በሙሉ በኢትዮጵያዊያን የሚካሔድ ነው። የሚካሔድ ያልኩትን በኋላ አስረዳለሁ።
የዛሬ 3 አመት ገደማ ይመስለኛል የመጀመሪያውን 7-Eleven ያየሁት- Gaston and Peak መንገድ ነበር። ቡናና ሲጋር ልገዛ ገብቼ ኢትዮጵያውን ብቻ ሳይ አንዱን ጠየቅኩት፤ “የኛው ነው!” አለኝ። የቻልኩትን ያክል አመሰገንኩ፤ አበረታታሁና ወጣሁ። ከዚያ በኋላ ባለፈው ሁለት አመት ነው አራት አዳዲስ 7-Eleven መርካቶ ያየሁት። የመርካቶው ሲገርመኝ የዛሬ አመት ገደማ ይመስለኛል አዲስ የተከፈተውን ቢጫ (Yellow Line) የባቡር መስመር መጨረሻ መቆሚያ ለማየት ተሳፈርኩና Buckner የሚባል መንገድ ደረስኩ። ከመቆሚያው ማዶ አንድ 7-Elevem አየሁና የሆነ ነገር ለማግዛት ስሔድ ሻጩ ኢትዮጵያዊ ነው። እኔ ለየሁት! እሱ አለየኝም! በአማርኛ ሰላምታ ስሰጠው ደነገጠ! ጥቁር አሜሪካዊ ብለው የሚገምቱኝ አይጠፉም! ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ወዲያውኑ የማይረዱ ያጋጥሙኛል። ይኸኛው ከዚያ አንዱ ነው። ደስ አለው! ፈነደቀ! እዚያ አካባቢ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አያዘወትሩም መሰለኝ። ደጋግሜ እንድመጣም ጋበዘኝ። እቃ ለመግዛት ሳይሆን አገሩን እንዳስታውሰው አይነት መሰለኝ። ከወደ ጎንደር የመጣ መሰለኝም። አማርኛውም መስተንግዶውም ሞቅና ለየት ያለ ነበር።
ዳላስ የተለያዩ ከተሞች አቀፍ (Metropolitan) ከተማ ነው። በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶችና ሱቁች አሉበት። በተለይም Park Lane በሚባለው መንገድ ሞቅና ደመቅ ያሉ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶችና ሱቆች እንደ ልብ ናቸው። ይህ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ከተማ የተለመደ ነው። ተመጋቢው፣ ሸማቹ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ፈረንጁንም ይጨምራል። ሎስ አንጀለስ የነበርኩ ጊዜ፤ መርካቶ፣ የዳዊት ምግብ ቤት፣ ፈረንጁ ከአበሻው ጋር መሳ ለመሳ ሲሆንም አይቻለሁ። ሽሮውን፤ጎመኑንና የክክ ወጡን ጤናማ ምግብ (Health Food) ሲሉም ሰምቻለሁ። የበለጠ ደምቆ ያየሁት በዋሽንግቶን ዲሲ፤ በሜሪላንድ (አገረ ማርያም) እና በቨርጂኒያ ነበር። አንድ ቀን ሲለኝ እመለስበታለሁ። አሁን ወደተነሳሁበት ልመለስ።
ይህንን 7-Eleven አይነቱን የንግድ ሥራ ፍራንቻይዝ (Franchise) ይሉታል። ትርጉሙ ይኸውና።
franchise; an authorization granted by a government or company to an individual or group enabling them to carry out specified commercial activities, e.g., providing a broadcasting service or acting as an agent for a company’s products
ገባ ብለን ብናየው ዘመናዊ ገባርነት መሆኑ መሰለኝ። ባለሀብቱ፣ ኩባኒያው፣ ምን መሸጥ እንዳለበት ዋጋውን ጨምሮ ይነግረውና ይህንኑ በሱ ፈቃድ ስም እንዲሸጥ ይፈቅድለታል። ፈቃዱን አከራየው ማለት ነው። ለዚያ በስምምነቱ መሠረት ለባለሀብቱ ይገብራል። እሱ(ሷ)ም ድርሻ አላቸው! ይኸ ነገር ኢትዮጵያም አለ። ይህ ሁሉ ነዳጅ ማደያ፤ የግል የራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ፍራንቻይዝ መሆኑ ነው።
ይኸ ሁሉ ሲሆን በአብዛኛው የአሜሪካ ከተሞች ሱቆቹና ንግዱ የሚካኸደው በፈረንጅ ካልሆነ እንደ ኢትዮጵያዊው በመጤው ነው። የሚበዙት ላቲኖ የሚባሉ አሜሪካኖች፤ ማለትም የእስፕየን ዝርያ ነን በሚሉት፤ በቻይናውያን፤ በፓኪስታንና ህንድ… ምኑ ተቆጥሮ ነው። “ጥቁሩ አሜሪካዊ የለበትም!” ለማለት ነው።
“ለምን፣ ስለ ምን ጥቁር አሜሪካዊ ንግድ ሥራው ውስጥ የለበትም?” ጥሩ ጥያቄ ነው! መልሱ የአሜሪካን ታሪክ አካል ነው! አብርሐም ሊንክን ተብሎ በሚዘመርለት ፕሬዚዳንታቸው ዘመን “ነጻ ወጡ!”(Emancipation Declaration) ተባለ። ከዚያ በፊት በተለይ ደቡብ ክፍል በጌቶቻቸው መሬት ላይ የሚያርሱ፤ የሚኖሩ ነበሩ። “ነጻ ወጣ!” ሲባል ባሪያ አሳዳሪው ከመሬቱ አባረራቸው! ወደ ከተማ ገቡ! ትምህርት፤ ዕውቀት፤ የሥራ ልምድ፣ ገንዘብ ሳይኖራቸው መለመላቸውን ነው የተነቀሉት። በዚህም በየከተማው የተረገጠ የተረሳ ጥጋ ጥግ ታጎሩ! ተጠራቀሙ! ጌቶ (Ghetto) የሚባለው ይህ ነው! አሜሪካ ጥቁሩ አብዛኛው የሚኖረው ጌቶ ነው። “ኑሮ ካሉ መቃብር ይሞቃል!”ም የሚባለውንም የሚያሟላ አይመስልም።
የንግድ ስራ አሁን ትምህርት ቤት ተገብቶ የሚማሩት ሙያ ቢሆንም ከትውልድ ትውልድ ለዘመናት የሚተላለፍ ነው። ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ የነጋዴ ልጅ ቢሆን ባይሆንም ስለ ንግድ እውቀት አለው። ገቢያ ሲሄድ፤ ሲገዛ፤ ሲሸጥ ሲለዋወጥ እያየ ነው ያደገው። ስለዚህም ንግድ ሲጀምር የሚጀምረው ከሀ አይደለም። ያ ለዘመናት የተወራረደው አለው። እርሾ ማለት ነው! ይህ ለኢትዮጵያ ያልኩት ለቻይናዎቹ፤ ሕንዶቹ፤ ፓክሲታኖቹ ለሌሎች ሁሉ ይሰራል። ጥቁር አሜሪካኑ ይህ የትውልድ ውርስና ቅርስ የለውም! ልጀምር እንኳን ቢል ንግድ የውድድር ጉዳይ ነውና አብረው መወዳደሪያው ሜዳ የተሰለፉት በዘመናት ይቀድሙታልና ከስሮ ይወጣል ማለት ነው።
አሜሪካን ጥቁሮቹ በትግላቸው ያስገኙት (Civil Rights Movement) ብዙ መብቶች አሉ። ይህ እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ የታገሉለትና የሞቱለት! የዚህ ትግል ውጤት ለቁጥረ- አናሳ(Minority) ለሆኑ ዜጎች ለትምህርትም ሆነ ለንግድ የተሻለ እድል በሕግ መድቧል። እነዚህ ከሌላ የመጡት፤ ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ የዚህ የጥቁሩ አሜሪካዊ የትግል ውጤት የሆነውን መብት ተጠቃሚ ናቸው። ቁጥረ-አናሳ (Minority) ናቸውና!! ጥቁር አብዛኛው አልተጠቀመበትም! ሊጠቅምበትም አይችልም! ከላይ በገለጽኩት ምክንያት! እርሾው የለውምና!
*   *   *
አሁን ወደተሳሁበት ከፊል ዋንኛው ነጥብ ልግባ። ይህም የጥቁር አሜሪካኖችና የዶናልድ ትራምፕ ምርጫ መሆኑ ነው። በተለምዶ ጥቁር አሜሪካውያን ዴሞክራቶች ናቸው። ይህም ማለት ሂለሪ ክሊንተንን ይደግፋሉና ይመርጣሉ እንደማለት ነው። በውድድሩ ወቅት “ጥቁሮቹ በዚህ ምርጫ ትራምፕን ነው የሚደግፉት!” የሚል ዜና አልፎ አልፎ ቢናኝም ለማመን የሚያስቸግር ነበር። ለማመን የሚያስቸግረው ክሊተን ለጥቁር አድማጮችዋ ያ የተለመደውን ዴሞክራት ተወዳዳሪ የሚለውን አለች። የተጠናውን! ትራምፕ ግን ግልጽ ነበር። “እኔን ምረጡኝ ! ዲሞክራት መርጣችሁ ያለፈላችሁ ነገር የለም! እኔን ብትመርጡ የምታጡት ነገር የለም! What have You Got to Loose ! ማንም ሆነ ማን ሊያደርግላችሁ የሚችለው ነገር የለም!” እንደማለት ነው። “ያው በገሌ! ናችሁ !” ማለት ነው:: እውነትም ነው! ስድብም ነው!
ትራምፕ ሌላ ያለው ነገር አለ። “እዚህ የተጠራቀመውን የውጭ ዜጋ በተለይም ሚክሲካኖችን አስወጣና፤ እንዳይገቡም አጥር አጥራለሁ!” አለ። ለጥቁር አሜሪካኖች ያቃጨለው ይህ ነው። ጠራርጎ ሲያስወጣልን ሥራ እናገኛለን ነው። እኔ ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን ወዳጆች አሉኝ። አሜሪካዊ ወዳጅ የሚባል ነገር ካለ! ስለዚህም በምርጫውም ውስጥ ከምርጫውም በኋላ እናወራለን። “ለመሆኑ መቼ ነው የምትሔደው?” ይላሉ። “አይ አልሔድም ቴክሳስ ተስማምቶኛል” እላለሁ:: “የለም ወደ አገርህ ማለታችን ነው!” ይላሉ። ከዚያም አጠገባችን ያሉ ሜክሲካኖችን ያሙልኛል። “ቆይ ታዘበኝ አሁን ትራምፕ ተመርጧልና በሚመጣው ሳምንት አታገኛቸውም!” ይላሉ። ይኸው ነው። ይህ ለኢትዮጵያውንም የሚሆን ነው። የደረሱበት አዘቅት ሥርአቱ መሆኑን ትተው “መጤው ነው እንጅ!” ማለታቸው ነው። እውነቱን ከፍተው ለማየት አለማቻል፤ ወይም አለመፈለግ፤ ወይም ምርጫ እንደማጣት ነው። “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል…!” አይነት መሆኑ ነው።
የሚገርመው ወይም የሚያስቀው ይህ እናስወጣለን የሚሉት ሜክሲኮአዊ ያለበት አገር፤ አሜሪካ አገሩ፤ ትላንት Spanish American War ,Mexican American War በሚሉት ጦርነት የተወሰደ ነው። ለምሳሌ ቴክሳሳን ቴክሳስ ብለን የምንጠራው በእንግሊዝኛ ሲሆን ነው። ያለበለዚያ ቴሐስ ነው:: X በስፓኒኛ ሀ ተብሎ ነው የሚነበበው። ከዚህም ሌላ የግዛቶቹ ስም፣ ካሊፎርኒያ፤ ኔቫዳ፤ ኒው ሜክሲኮ፤ ኮሎራዶ፤ አሪዞና እንዳለ በእስፔይን ቋንቋ ነው። በተለየ ካሊፎርኒያ ከሳንፍራንሲስኮ እስከ ሳንዲያጎ ሎስ አንጀለስን ጨምሮ የካቶሊክ ቅዱሳን ስም ነው፤ የካሊፎርኒያ ዋና ከተማ ስም ሳክራሜንቶ (Sacramento) “ቅዱስ ቁርባን” ማለት ነው።
ይህን መነሻ በማድረግ ሰፋ ተደርጎ ከታየ ትልቁ ምስል የሚታይ ይመስለኛል። “ከኋላ የመጣ ቀንድ አወጣም!”ንም የሚያጣ አይመስለኝም። “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት!” ማለትም ይኸው ይመስለኛል!
አንድ ቀን ሲመቸኝ ወይም ሲለኝ ስለ “ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ!” እመለስበታለሁ፡፡

Read 2273 times