Saturday, 10 March 2012 12:19

ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ የእኔ ስኬት መገለጫ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

9ኛው ቅድሚያ ለሴቶች የጐዳና የ5 ኪ.ሜ ሩጫ በነገው ዕለት ሲካሄድ 9ሺ ሴቶችን ሊያሳትፍ ነው፡፡ ሩጫው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ከዋናው የ10ኪ.ሜ የጐዶና ላይ ሩጫ ቀጥሎ ከፍተኛ ስኬት የታየበት ነው ፡፡ በሌላ በኩል በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዝግጅት አስተባባሪ የሆነችው ወይዘሪት ዳግማዊት አማረ በተቋሙ ባገለገለችባቸው 9 ዓመታት ለከፍተኛ ለውጥ ያበቃትን ልምድና ዕውቀት ማግኘቷን ለስፖርት አድማስ ስትናገር ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ የእኔ ስኬት መገለጫ ነው ብላለች፡፡

ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከስምንት አመት በፊት ሲጀመር ተሳታፊዎቹ 5ሺ የነበሩ ሲሆን ከነገ  በፊት የተካሄዱ ስምንት ውድድሮች ለሴቶች እኩልነት ባነገባቸው መርሆች በመታጀብ ማራኪ የስፖርት ፌስቲቫል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ ለተተኪ አትሌቶች መፍለቂያ መድረክ መሆኑም ታይቷል፡፡ በ2007 እና በ2009 እኤአ ላይ ውድድሩን ያሸነፈችው አትሌት አሰለፈች መርጊያ እና የመከላከያ ክለብ አትሌት የሆነችው ሱሌ ኡትራ ለዚህ ውጤቱ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ አሰለፈች መርጊያ በዚህ ውድድር ለ2 ጊዜያት ሻምፒዮን ከሆነች  በኋላ በ2008 በዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር የነሀስ ሜዳልያ ከመውሰዷ ሌላ በ2010 የለንደን ማራቶን 2ኛ እንዲሁም ዘንድሮ የዱባይ ማራቶንን በማሸነፍ ስኬታማ ሆናለች፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫን ያሸነፈችው የመከላከያ ክለብ አትሌት ሱሌ ኡትራ ደግሞ ከ8 ወራት በኋላ ትልቁን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎሜትር ውድድር ከማሸነፏም በላይ በ10ሺ ሜትር የአፍሪካ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃች ናት፡፡ልዩነት ለማምጣት ሴቶችን ማብቃት  የሚለው የተባበሩት መንግስታት መፈክር የዘንድሮው ቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ አብይ መርህ ሲሆን  ዲኬቲ ኢትዮጵያ ‹የቤተሰብ ምጣኔ ከቾይዝ ጋር ነው› እንዲሁም ኮንሰርን ዓለም አቀፍ ‹ፆታዊ ጥቃት ለማስቆም ቁልፍ ሚና አለዎት› የሚሉ መፈክሮቻቸውን ያስተጋባሉ፡፡ መነሻና መድረሻው አትላስ  ባደረገው የ5 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው ላይ 150 አትሌቶች  በዋናው ውድድር የሚሳተፉ ሲሆን ለ1ኛ 10ሺ  ብር ሲሸለም 2ሺ  ብር ለሪኮርድ እንደሚታሰብ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ከ9 ዓመት በፊት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ፋይናንስ ክፍል ተቀጥራ ስራ የጀመረችው ወ/ሪት ዳግማዊት  አማረ ዛሬ በተቋሙ የዝግጅት አስተባባሪ ሆና የማገልገል ደረጃ ደርሳለች፡፡ ማንኛውንም ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ የማከናወን ሰፊ ልምድና በራስ መተማመን ማዳበሯን የገለፀችው ዳግማዊት፡፡ ተቋሙ በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ስኬታማነት ብቻ ሳይሆን ጎን ለጎን በሚንቀሳቀስባቸው መርሆች ውጤታማ መሆኑ የሚያኮራ ነው ትላለች፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዝግጅት አስተባባሪነት በያዘችው ኃላፊነት ዳግማዊት አማረ የተሳታፊዎች ምዝገባን በተያዘ እቅድ ለማሳካት፤ ከውድድሮቹ ጋር በተያያዘ በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የሚሰጡ ድርጅቶችን በማሰባሰብና በቀጣይነት አብረው ከተቋሙ ጋር በመስራት እንዲቀጥሉ በማግባባት፤ ከሚዲያና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለውድድሮች የተሳካ ሂደት ተቀራርቦ በመስራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ታደርጋለች፡፡ወ/ሪት ዳግማዊት አማረ  ለውድድሮች  በሚደረጉ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችንና በውድድር ወቅትና ከዚያ በኋላ የሚሠሩ ስራዎችን ለማከናወን በቡድን እንደ ቤተሰብ ተቀራርበን የምንሠራበት መንገድ በታላቁ ሩጫ ውስጥ በመስራቴ   የምደሰትበት ዋና ነገር ብላዋለች፡፡  በምናዘጋጃቸው ውድድሮች በየዓመቱ የተሳታፊዎች ቁጥር እያደገ ሲሄድ፣  አብረውን የሚሠሩ ድርጅቶች በስፖንሰርሺፕ ድጋፋቸው በመርካት ድጋፋቸው ቀጣይነት ሲኖረው አዘጋጆች ከፍተኛ እርካታ እናገኛለን በማለትም ተናግራለች፡፡ በምናዘጋጃቸው ውድድሮች ያቀድነውን የተሳታፊ ብዛት በቶሎ መዝግቦ  ለመጨረስ አለመቻል፣ ለየውድድሩ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በሚያቀርቡልን ድርጅቶች በምንፈልገው ጊዜና የጥራት ደረጃ አቅርቦታቸው የማያረካን መሆኑ ለዝግጅት አስተባባሪዎች እንቅፋት የሆኑ ችግሮች መሆናቸውን ወ/ሪት ዳግማዊት አማረ ስትገልፅ ከዓመት ዓመት ግን በእነዚህ ችግሮች ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን በመጠቆም ነው፡፡

 

 

Read 2169 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:22