Monday, 12 December 2016 12:12

ፊደል ካስትሮ - “የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ!!”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

‹‹ካስትሮ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ነበሩ››
አቶ ተስፋዬ ወንድሙ
(የ”ግራንማ 72” ኩባ የተማሩ መኮንኖች ማህበር ፕሬዚዳንት

አገራችን ኢትዮጵያ በሶማሌ ወራሪ ሀይል በተከበበችበት በዚያን ክፉ ወቅት ማንም ከአጠገቧ አልነበረም፡፡  ወራሪዋን ካባረረች በኋላም ወረራ በድጋሚ ቢመጣ አገሪቱን ከውድቀት የሚጠብቅ፣ የተማረና የሰለጠነ የውትድርና መኮንን ይፈለግ ነበር፡፡ በወቅቱ የትምህርት ደረጃችን ለዚህ ስልጠና የሚያበቃንን ኩባ ወስደው፣የኬሚካል ጦር መሳሪያ መከላከልን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ ሥልጠና ሰጥተውን፣ 500 ምሩቃን መኮንኖች ወደ አገራችን ተመልሰናል፡፡ ከ500 ውስጥ በማህበራችን 150 ሰዎች ናቸው በአባልነት ያሉት፡፡ የተቀሩት ግማሹ በሞት፣ በዕድሜ መግፋት፣ በህመም---- የሉም። ማህበራችን አሁን በኢትዮጵያ ከሚገኘው የኩባ ኤምባሲ ጋር የጠበቀ ወዳጅነትና ግንኙነት አለው፡፡ አብዛኞቻችን ከትምህርት በኋላ እንደገና ተመልሰን ወደ ኩባ በመሄድ አገሪቷን ጎብኝተናል፡፡ ዋናው የማህበራችን አላማ፣ ከ35 ዓመት በፊት ስንገናኝ የነበረንን አንድነት፣ ወዳጅነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ ጠብቆ ማቆየት ነው፡፡ ከፊደል ካስትሮና ከኩባ የተማርነው ይህንን ነው፡፡
   ዛሬም በዚህ ስነስርዓት ላይ የተመለከትሺያቸው በህክምና፣ በምህንድስና፣ በቴክኒክና ሙያ፣ በIT የትምህርት ዘርፍ ከኩባ ተምረው መጥተው አገራቸውን የሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ በየዘርፉ ማህበር አቋቁመው ይገናኛሉ፣ ይወያያሉ፣ ይረዳዳሉ፡፡ የእኛም ማህበር እንደዛው በሀዘንም በደስታም እንገኛናለን፡፡ ምንም እንኳን እዛ በምማርበት ጊዜ ፊደል ካስትሮን በአካል ባላገኛቸውም ከሚዲያ በተለይም ከቴሌቪዥን አይጠፉም ነበር፡፡ ሁልጊዜ እሳቸው የሚናገሩትን ማዳመጥ ትምህርት መቅሰም ማለት  ነው፡፡ ህዝባቸውን፣ አገራቸውን የሚወዱ መሪ ነበሩ፡፡ እውነት ለመናገር የኢትዮጵያም የቁርጥ ቀን ወዳጅ ናቸው፡፡ ህዝባቸውም ቢሆን የሁሉንም አገር ህዝብ በእንግድነት ይቀበላል፤ እንደ እኛ አይነት ህዝብ ነው። በተለይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለው ፍቅርና አክብሮት ይለያል፡፡ ይሄንንም በክፉ ቀናችን ህይወታቸውን ሰጥተው አረጋግጠውልናል፡፡ እዚያም ስንኖርና ስንማር እንግድነትና ባዕድነት ጨርሶ ሳይሰማን ነው የተመለስነው፡፡
ፊደል ካስትሮ ሮዝ፤ ለኩባ ህዝብና ለመላው ዓለም ድሃና ድምፅ አልባ ህዝቦች የታገሉና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡ እኛም በጠላት ተወርረን አቅም ባነሰን ጊዜ  ወታደሮቻቸውን ከጎናችን በማሰለፍ፣ ጠላት ከአገራችን ተጠርጎ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ ከዚያ በኋላም በጦርነቱ አባቶቻቸውን ያጡ ከ6ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ህፃናት ኩባ ሄደው እንዲማሩ በማድረግ፣ተመልሰው አገራቸውን በየተማሩበት ዘርፍ እንዲያገለግሉ አድርገዋል፤ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ፊደል ካስትሮ ለአገራቸው፣ ለአፍሪካና ለዓለም ህዝብ ትልቅ ድጋፍ ያደረጉ ቆራጥ መሪ ናቸው፡፡ እንደተወደዱና እንደተከበሩ ነው የኖሩት፡፡ ሁሌም በውስጣችን ይኖራሉ፡፡ እሳቸው ቢያልፉም አስተሳሰባቸውን በብዙ ሺ ህዝቦች ውስጥ ያሰረጹ በመሆናቸው ሁሌም ይታወሳሉ፡፡ ሌጋሲያቸውን ታናሽ ወንድማቸው ራውል ካስትሮ ያስቀጥላሉ የሚል እምነት አለን፡፡

============================

“ጂሚ ካርተር ፊት ሲነሳን፣ ፊደል ደርሶናል”

ጀነራል አሰፋ አፈሮም (የቀድሞ መንግስት የጦር መሪ)

በሙያዬ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የዘመቻ መኮንን በመሆን አገሬን አገልግያለሁ፡፡ የመጨረሻ ቢሮዬ ፊት ለፊትሽ የምታይው (ጥቁር አንበሳ፣ድላችን ሃውልት ጋ ነበርን) መከላከያ ሚኒስቴር ነበር። በኢህአዴግ አራት አመት ታስሬ ተፈትቻለሁ፡፡ በምስራቅ ኢትዮጵያ የዘመቻ መሪ ሆኜ ጦር ስመራ፣ ከኩባዎች ጋር አብረን ነበርን፡፡  የኩባን ወታደሮች በቅርበት አውቃቸዋለሁ፡፡ እኔ በወቅቱ የምመራው ብርጌድ፣ ተጎጫሌ ኢኖጎሃ ተፈሪ በር በሚባል ቦታ ሀርጌሳ ላይ ነበር፡፡
ይህን ጦር እኔ ከመምራቴ በፊት ሶማሌ ስትወረን፣ በሶማሌ ግንባር አካባቢውን ነፃ ያወጣ ብርጌድ ነበር፡፡ ሚሊሺያ ብርጌድ ነው፣ ታጠቅ ሰልጥኖ ግንባር በመሄድ ሶማሊያን ከኦጋዴን ያስወጣ ብርጌድ ነው፡፡ ያን ጊዜ ኩባዎቹ የሚኖሩት ጅጅጋ ሲሆን ከጎቶ ጫሌ 50 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነበሩ። ታዲያ ለራሳቸው ልምምድ ሲያደርጉ፣ በእኛ በኩል ያልፉ ስለነበር ከእኔ ጋር ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰን ነበር፡፡ ጦሬን ሊያሰለጥኑልኝ ቃል ገብተውልኝም ነበር፡፡ ሆኖም በ1974 ዓ.ም ለቀይ ኮከብ ዘመቻ አስመራ ተጠርተን ሄድን፡፡ ያን ጊዜ ኩባዎቹ እዛው ቀሩ፡፡
 እዚህ የመሪው ስንብት ላይ በህይወት ኖሬ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ እድለኛም ነኝ እላለሁ። ምክንያቱም ፊደል ካስትሮ የኢትዮጵያ ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በክፉ ቀን ያልከዳ፣ በችግርና እርዳታ በሚያስፈልገን ቁርጥ ቀን የደረሰልን ሰው ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ፊደል ካስትሮም ይሄ ክብር ቢያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም፡፡ ዛሬ ስለሳቸው ሲባል ሲነገር የዋለውን ሰምተሻል፤ ነገር ግን ካስትሮ ከዚህም በላይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ለወዛደር አለም አቀፋዊነት በቁርጠኝነት የታገሉ፤ በአላማቸው ፀንተው የቆዩ መሪ ናቸው፡፡ ፊደል ካስትሮን በአካል አግኝቻቸው አውቃለሁ። የኢትዮጵያ ጦር ሶማሌያን በመልሶ ማጥቃት ከኦጋዴን ካባረርናት በኋላ ጎዴ ላይ በተደረገው “የአርሚ ሾው ኦፍ ፎርስ” ላይ ከመንግስቱ ኃ/ማሪያም ጋር ተገኝተው፣ ከኩባውያን ጋር ተሰልፈን የጦር ልምምድ አድርገናል፡፡ በወቅቱ ማዕረጌ ሌተናል ኮሎኔል ነበር፡፡ ካስትሮ በጣም ወዳጃችን ነበሩ የምለው ዝም ብዬ አይደለም፡፡ በሶማሊያ ወራሪ ኃይል በተከበብንበት ጊዜ፣ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር የጦር መሳሪያ ከልክሎ፣ ፊት ነስቶ ሲመልሰን፣ ይህ ሰው በርካታ ወታደሮችና የጦር መሪዎችን በመላክ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ መቼም የሰው ፍፁም የለምና ምንም እንኳን ካስትሮ ለሶሻሊዝምና ለዓለም አቀፋዊ ወዛደርነት ቢታሉም፣ በጣም አምባገነን ነበሩ፡፡ ይሄን ያህል ዓመት ስልጣን ለሌላ ትውልድ ሳያስተላልፉ የሙጥኝ ብለው ይዘው ሲገዙ መኖራቸው፣ አምባገነንነት ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?! የኩባ ብሄራዊ ጀግና የሆነውን ጀነራል ኦችዋን በአደባባይ መግደልም በስልጣን መባለግን ያሳያል። ማዕረጋቸውን መግፈፍና ማሰር ሲቻል፣ ‹‹ኮኬይን ከውጭ አመጣህ›› ብሎ በአደባባይ ብሄራዊ ጀግናን መግደል የለየለት አምባገነንነት ነው፡፡ ኮሎኔል መንግስቱም “ከደቡብ 10 ኪሎ ቡና አመጣችሁ” ብሎ ከከፍተኛ ስልጣን አውርዶ የጣላቸው ትልልቅ የጦር መሪዎች ነበሩ፡፡
ይሄም አምባገነንነት ነው። በአገራችን ከ500 ሺህ ብር በላይ ሀብት ማካበት አይቻልም የሚል ህግ ወጥቶ ነበር - የሶሻሊዝም አስተሳሰብ አይፈቅድም በሚል፡፡ ይህም ስህተት ነው፡፡ ባለሀብቱን ከዚህ በላይ ሀብት እንዳታፈራ ማለት ሶሻሊዝምን በአግባቡ አለመተርጎም ነው፡፡ ፊደል ካስትሮና ኮሎኔል መንግስቱ በዚህ ባህርያቸው ይመሳሰላሉ፡፡ በመጨረሻ የፊደል ካስትሮን ነፍስ ይማር እላለሁ!!

=======================================

“ፊደል ካስትሮ ሁሉ ነገራችን ነበር”  

ዶ/ር ሙሉዓለም ለገሰ (በየካቲት 12 ሆስፒታል፣ የጨቅላ ህፃናት ስፔሻሊስት)

ፊደል ካስትሮ አገራችን ድረስ የራሱን ወታደሮች ልኮ በጦርነቱ ከማገዝና ከመዋጋት ባሻገርም በጦርነቱ አባታቸውን ያጡ በርካታ ህፃናትን ወደ አገሩ በመውሰድ፣ አገራችንን የምንጠቅም ዜጎች እንድንሆን፣ በሥነ ምግባር ተቀርፀንና ታንፀን እንድናድግ ትልቅ እድል ሰጥቶናል፡፡ አገራችን እንደ ማንኛውም የአፍሪካ አገራት ደሀ አገር በነበረችበት በዚያን ወቅት ኢኮኖሚዋን አሳድጎ የሚለውጣት የተማረና በቅጡ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋት ነበር፡፡ ፊደል ካስትሮ ለእኛም ለአገራችንም ይህን ትልቅ እድል ሰጥቶናል፡፡ ለዚህ ነው ፊደል ካስትሮ ሁሉ ነገራችን  ነበር የምለው፡፡
እኔ ከእህትና ከወንድሜ ጋር ሶስት ሆነን ነበር የሄድነው፡፡ በወቅቱ እኔ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ስሆን እህቴ የ8ኛ፣ ወንድሜ ደግሞ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ኩባ አደግን ተማርን፣ ሰለጠንን። እኔ - ህክምና፣ እህቴ - ኢኮኖሚክስ፣ ወንድሜ - ኢንጂነሪንግ ተምረን ወደ አገራችን ተመለስን፡፡ እዚያ በነበርንበት ወቅት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ህዝቦች በተለየ ይወዱንና ይንከባከቡን ነበር፡፡ ሁሌም የበለጠ ነገር ለእኛ ይደረግልን ነበር፤ ደግሞ ለራሳቸው በቂ ሳይኖራቸው ነው የሚሰጡንና የሚንከባከቡን። ፍቅርና አክብሮትን አስተምረውናል፡፡ ህዝቡ፣ ፍቅርና አክብሮት ይሰጠን የነበረው ከመሪው ተምሮ ነው። ፊደል ሁሌም ስለ ሰው ህይወትና ስለ ሰብአዊነት የሚያስብ መሪ መሆኑን በቅርበት  አይተነዋል። ስለዚህ ነው ህፃናትም፣ ትልልቅ እድሜ ያላቸው አያት፣ ቅድመ አያቶችም ኩባ ውስጥ  በብዛት የሚኖሩት፡፡ ሰው ለመኖር የሚያስፈልገው ፍቅር፣ ምግብ፣ መጠለያና ሁሉም ነገር በደንብ ሲሰጠው ያየሁበት አገር ኩባ ነው፡፡
በህክምና ዘርፍ የተማርነው ቁጥሩን በትክክል ባላውቀውም፣ ብዙ መሆናችንን ግን አስታውሳለሁ። ዛሬ ሁሉም ኩባ የተማረ ኢትዮጵያዊ በሰለጠነበት ዘርፍ አገሩን እያገለገለ ይገኛል፡፡
ከኩባ ተምረን የመጣን ተማሪዎች፤ ሌላ አገር ሄደው ከተማሩት የምንለየው፣ ህዝቡ ባስተማረን ፍቅር፣ አንድነትና የአገር ፍቅር ምክንያት ነው፡፡ በትንሽነታችን ስለሄድን የህዝቡን አኗኗር፣ ፍቅር፣ ለሰው ልጅ የሚሰጡትን ክብርና ባህላቸውን ወርሰናል፡፡ አገራችንን እንወዳለን፡፡ ህዝባችንን እንወዳለን፤ እናገለግላለን፤ እርስ በርሳችንም እንዋደዳለን፡፡  
ስለ ፊደል ካስትሮ ብዙውን እዚሁ ሰምታችሁታል፤ ‹‹ሶሻሊዝምን ያራምዳል፤ አምባገነን ነው›› ይባላል፡፡ ይህን የሚሉት ቀርበው የማያውቁት ናቸው፡፡ እሱ ግን የዋህ ነው፤ ደግ ነው፤ ሰራተኛ ነው። ጭንቅላቱ በየሰከንዱ የተለያዩ ሀሳቦችን ያስባል፡፡ እሱ ሀኪም ብቻ አይደለም፤ ዳኛም ብቻ አይደለም፤ መሀንዲስም ብቻ አይደለም፤ እሱ ሁሉም ነገር ነው። ስለ ሁሉም ነገር ያውቃል፡፡ የሚማሩትን ይጎበኛል፤ ይመክራል፡፡
ህዝቡ ያዳምጠዋል፡፡ መስራት ህዝቡን ማገልገል የሚወድ ታላቅ ሰው ነው፡፡ በቃ ካስትሮ ይሄ ነው፤ ሁሌም በውስጣችን ይኖራል፤ ለዚህ አብቅቶናል፤ ብዙዎች በእሱ ትምህርትና ፍቅር እዚህ የደረሱ ናቸው፡፡

===================================

“ብሄራዊ ጀግና በመግደላቸው አዝኜባቸዋለሁ”

ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ (የቀድሞው መንግስት የጦር መሪ)

አዘጋጆቹ ባይጠሩኝም በፕሮግራሙ ላይ የተገኘሁት ለፊደል ካስትሮና በችግራችን ወቅት አብረውን ለነበሩት የኩባ ወታደሮች እንዲሁም የጦር መሪዎች አድናቆት ስላለኝ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ካስትሮ የላኳቸውን ወታደሮች ወደ አገራችን ሲመጡ፣ መከላከያን ወክዬ አሰብ ላይ የተቀበልኳቸው እኔ ነኝ፡፡ በ1969 መጨረሻ ታንኮችና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ይዘው ሲመጡ እስከ ኦጋዴን በማጓጓዝ፣ ከእነሱ ጋር በቅርበት ሰርቻለሁ። በወቅቱ ሻለቃ ነበርኩኝ፡፡ በእርግጥ ከካስትሮ ጋር በአካል አልተገናኘሁም፡፡ ካስትሮ ከቆራጡ መሪያችን ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር በተዋወቁ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን ለመርዳት ባሳዩት ቁርጠኝነት አደንቃቸዋለሁ፡፡ ለአገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ ሶማሌ በእብሪት ወደ ግዛታችን 700 ኪ.ሜ ገብታ፣ ወርራን በነበረበት በዚያ ቀውጢ ጊዜ የደረሱልን የመጀመሪያው መሪ ናቸው፡፡ እንኳን የአሁኑ የወደፊቱም የኢትዮጵያ ትውልድ የፊደል ካስትሮን፣ የኩባንና የህዝቡን ውለታ ፈጽሞ ሊረሳ አይችልም፡፡ በዚህ ግርማ ሞገስ ያላቸው መሪ ናቸው። ዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ምሁርም ናቸው፡፡
በእሳቸው ቅር ስሰኝበት የምኖረውና የምነቅፋቸው፣ የኩባን መከላከያ ወክለው በኒካራጓ፣ ሞዛምቢክ፣ አንጎላና ኢትዮጵያ የኩባ ሚሽን አዛዥ ሆነው የሰሩትን የጦር መሪ፣ “ብሄራዊ ጀግና” ጀነራል ኦቹዋን፤ ‹‹ኮኬይን ከውጭ አምጥተሃል›› በሚል ተልካሻ ምክንያት በማስገደላቸው ነው፡፡ ለይስሙላ የ42 ጀነራሎች ፍርደ ሸንጎ አቋቁመው፣ እንዲገደሉ በማስደረጋቸው አዝኜባቸዋለሁ፤ አወግዛቸዋለሁም። ጀነራል ኦችዋ ጦር መርተው ሲመጡም የተቀበልኳቸው፣ ሲሄዱም ጦሩን የተረከብኳቸው እኔ ነበርኩ፤ በቅርበት አውቃቸዋለሁ፡፡ ጀነራሉ በዓለም ላይ ከሚታወቁ ምርጥ የጦር ጀግናዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ኮሎኔል መንግስቱም ለእኚህ ጀግና ሽልማት ሰጥተዋቸዋል፡፡ ጓድ መንግስቱ ጀነራሉ እንዳይገደሉ ብዙ ጥረት አድርገው የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም፡፡
ጀነራል ኦችዋን ተክቶ የነበረው የኩባ ሚሽን መሪ በኢትዮጵያ፣ ሎሬቲንስ ሊዮን ወደ አገሩ ከመመለሱ በፊት እንዲህ ቃል ተገባብተን ነበር፡፡
ሎሬቲንስ ሊዮን - ‹‹እኔና ህዝቤ ለአንተ ነፃነትና ህይወት ደማችንን አፍስሰናል፤ እኔን ኢምፔሪያሊዝም ቢወረኝ ትዋጋልኛለህ?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡
እኔም ተንበርክኬ - ‹‹ቃል እገባለሁ፤ እዋጋለሁ›› ብዬ ባንዲራውን ተረከብኩት፡፡
 ፊደል ካስትሮ በብሄራዊ ጀግናቸው ላይ በወሰዱት እርምጃ ባዝንባቸውም ለኢትዮጵያ በዋሉት ውለታ ዘላለማዊ ክብርና አድናቆት አለኝ፡፡

Read 5775 times