Monday, 12 December 2016 12:14

ግጥማችን የወጌሻ ያለህ ይላል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(77 votes)

 ኢትዮጵያዊያን በግጥም ባህር ውስጥ የምንዋኝ ዓሳዎች ነን፤ … ዓሳ ከባህር ከወጣ በኋላ ህይወት እንደማይኖረው ሁሉ እኛም ያለ ግጥም ህልውናችን ያከትማል እስከማለት የደረሰ ኩራት ያለን ይመስላል። ምክንያቱም ስንዘፍን በግጥም፣ ስናለቅስ በግጥም፣ ስንዘምር በግጥም ስናቅራራና ስንፎክርም በግጥም ነው ብለን እናምናለን፡፡
በዚህ ላይ ተቃውሞ የለኝም፡፡ …. ነገር ግን ይህ ኩራታችንና “ገጣሚ ነን!” የሚለው እምነታችን የወለዳቸው ችግሮች፣ ዛሬም ለጥበቡ ራስምታትና የልብ ቁርጠት የሆኑ ይመስለኛል፡፡ በዓመት ውስጥ ከ365 ያላነሱ የግጥም መጻህፍት መታተማቸው አንድ ማሳያ ነው፡፡
ለምን የሚታተሙት ግጥሞች በአብዛኛው መናኛ ሆኑ ስንል፣ ሀጢአቱን ወስደን የምንደፈድፈው ገጣሚዎቹ ላይ ነበር፡፡ አሁን ግን በየአጋጣሚው ባየሁዋቸው የአደባባይና የጓዳ ውስጥ ውይይቶች የታዘብኩት የግጥሙ ዓውድማ በእንክርዳድ ለመሞላቱ ሰበቡ እኛው ስነ ጽሑፉ አካባቢ የምንገኝ ሰዎች መሆናችንን ነው፡፡ ለመሆኑ እንደ ስለ ግጥም አስተያየት የሚሰጥ ሰው “አሪፍ ግጥም ነው፤ ወይም ቀሽም ግጥም ነው!” ሲል ምንን መሰረት አድርጎ ነው?... ትልቁ ችግር የተፈጠረው እዚህ ጋ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎቻችን “የሚገርም ግጥም ነው!” ስንል ሀሳቡንና የገጣሚውን አተያይ ብቻ መሰረት አድርገን ነው፤ ፈረንጆቹ “Meaning and Idea” የሚሉትን፡፡ … ግን ይህ ብቻውን ግጥምን ያሰኛል እንዴ? … በፍፁም! … ግሩም ሀሳብ ያለው መጣጥፍም አለ’ኮ! … ግጥምን ግጥም የሚያሰኘው ዋናው ነገር ምጣኔና ምቱ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈው ስዕል አለው፡፡ ቁጥብ ነው፣ እምቅ ነው፣ ቃላትን መርጦ በተመረጠ ሁኔታ ይደረድራል፡፡
ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ግጥም በሀሳቡ ብቻ ምርጥና ቀሽም የሚባለው! ለዚህ ነው ኤስ.ኤች.ቡርቶን፤ አስተያየት የሚሰጥ ሰው ጠንቃቃ መሆን አለበት የሚሉት፡፡ “--- patiently and carefully, the true critic works; informed always by a desire for truth; animated by a love of poetry; guided by imagination and common sense; and working with purpose and method.”
ይሁን እንጂ እኛ ሀገር ስለ ግጥም አስተያየት የማይሰጥ ሰው የለም፣ … ምክንያቱ ደግሞ ዝርዝሩን የሚጠይቀን ሰው ስለሌለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በአደባባይና በፕሬሶች ላይ ስለ ግጥም የተሰጡ አስተያየቶችን እንኳን ስንፈትሽ ሁሉም ማለት ይቻላል፣ ለግጥም ምልዐት የሚያዋጡትን አላባውያን ሁሉ ወደ ጎን ብለው ስለ ሀሳቡ ብቻ የሚያወሩ ናቸው፡፡ …. ግን ግጥም ያለ ሸጋ ውቅር፣ ያለ ምርጥ ዜማና ምት ምን ውበት አለው? … እያንዳንዱ ነገር የምልዐቱ ብልት ነው፡፡ አንድ በግ ሁለት እግር ቢጎደለው ውበት ብቻ አይደለም የሚያጣው አካል እንጂ! ይህም ከዚያ ያልተናነሰ ጉድለት ነው፡፡ እስቲ ስለ ግጥም ስንነጋገር አብረውን ያሉ ሰዎችን እንጠይቅ - “የእገሌ ግጥም ቆንጆ ነው!” ያለበት ምክንያት ምንድን ነው? …. ብዙዎች ይህን ምክንያት አያውቁትም! … ምናልባትም አንዳንዶቹ ከሀሳብ ይነሱና ወደራሳቸው ዝንባሌ ያጋድላሉ፡፡ ፍልስፍና የሚወድ፣ ነገሮችን መፍተልና ማውጠንጠን ነፍሱ የምትጠማ አንባቢ፣ ወደ ፍልስፍና ያደላ ግጥም ካነበበ፣ ወይም ካደመጠ “ግጥም ማለት ይህ ነው” ብሎ ያርፈዋል፡፡ … ግን እውነት ነው! … በፍጹም! ያ የግጥሙ ምልዐት አንድ ቅንጣት እንጂ፣ የግጥሙ ሙሉ መልክ አይደለም፡፡ …አንድ የግጥም ተመራማሪ፤ “It’s primary concern is not with beauty, not with philosophical truth; ….” ይላሉ፡፡
ይህ እንግዲህ ሀሳቡን በተመለከተ ብቻ ነው። ከዚያ ባለፈ ዜማ እንዳይሰብር፣ የተገጣጠመ ውቅር እንዲኖረው፣ የምቱን ጥብቀትና ልልነት፣ ልብ ማለት አያሻም? … የዘይቤዎች አጠቃቀም፣ የቃላት ምርጫስ? … ትርፍ አንጀት ናቸው? …
እስቲ ስለ አንጓዊ ቅርፅ ባህርያት የአገራችን የግጥም ተመራማሪ ብርሃኑ ገበየሁ በ”የአማርኛ ስነ ግጥም” መጽሐፉ ያሰፈረውን እንመልከት፡- “በስንኞቹ መጠን፤ በቤት አመታት፣ በምጣኔ ስልትና በአዝማች ቅምብት (ግጥሙ አዝማች ሲኖረው)----”
እንግዲህ  ይህንና ሌሎችንም የግጥም መመዘኛዎች  ባለመከተላችን ግጥሞቻችን  ሁለንተናዊ ዕድገትና ምልዐት እንዳይኖራቸው አድርገናል፤ አቀጭጨናል። ምክንያቱም  ዓይኖቻችንን ከይዘት ወደ ቅርፅ መመለስ አልቻልንምና! ለመሆኑ እኛ ሀገር በአንጓዊ ቅርፅ ሸጋ የምንላቸው ገጣሚያን አሉን? … የሚለውን ጥያቄ እንዳናነሳ ያደረጉን አደባባዮቻችን በሀሳብ ልዕቀት ላይ ብቻ ያተኮሩ አስተያየቶች መናኸሪያ ስለሆኑ ነው፡፡ ምናልባት ስለነዚህ ነገሮች አስተያየት ሲሰጥ የሰማሁት የኮተቤው የሻው ተሰማ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ እኔ በግሌ አልገጠመኝም፡፡
ለምሳሌ ብዙዎቹ የመቅደስ ጀንበሩ ግጥሞች በአንጓዊ ቅርፅ፣ በተለይ በቤት አመታት የተዋጣላቸውና የሚደነቁ ናቸው፡፡ (የቃላት አጠቃቀምዋን ሳንጨምር)
“ምስጢር” የሚለውን ግጥሟን ለአብነት ያህል እነሆ፡-
በግል ናላ የሸመቀ፣
    ድብቅ እስር ያልተፈታ፣
ከራስ አልፎ ያልታወቀ    
    የከበረ በመታገስ … የነጠረ በዝምታ፣
በሰው ላንቃ ያልደቀቀ
    ያልዳሰሰው አሉባልታ
ነፋስ ገብቶት ያልደረቀ
ያልተንቋቋ በየስፍራው … ያልረከሰ የትም ቦታ
ሽፍን ስሜት ያልተላጠ
    ተዘዋውሮ ያልተጉላላ
ከስሮ ከብሮ ያልተሸጠ
ያልተሻሸ በሰው ስሜት … በሰው ቅኝት ያልተብላላ፡፡
ከላይ ያየናቸው የመቅደስ ጀንበሩ ስንኞች ‹‹በሀለ-ሀለ›› ቤት የሚመቱና ከአማርኛ ስነ ግጥም ነባር ልምዶች የተወረሱ ናቸው፡፡ አበባይሆይና ሆያ ሆዬ ግጥሞች ለዚህ ዝምድና ማሣያ ሊሆኑን ይችላሉ፡፡ ይህ የቤት አመታት ስልት ደግሞ አንባቢን እንዳይሰለች ለማድረግ ምቱን እየቀያየረ አዲስነትና ይሰጠዋል፡፡ ምናልባትም ከሌሎች የቤት አመታት ስልቶች የበለጠ ትጋትንና ቅንጅትን ይጠይቃል፡፡ የመቅደስ ግጥሞች ውበት ይህ ብቻ አይደለም፤ የቤት አመታቱ ፍዝና ኢ-ፍፁም አይደለም፤ ሁሉም ጥብቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ የቤት መምቻ ተናባቢዎች ደካማ ድምፆች አይደሉም፡፡ አናባቢዎቹም በተፈጥሮ ባህርያቸው ደካማ ሳይሆኑ ጠንካራ ድምፅ ያላቸው ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ ለምሳሌ ሁለተኛው፣ አራተኛው፣ ስድስተኛው፤ ስምንተኛው፣አስረኛው፣ አስራ ሁለተኛው ስንኞች አናባቢያቸው ‹‹ኣ›› ነው፤
እንግዲህ የስንኞችን ምጣኔ የቅርፃዊ መዋቅርን፣ የቃላትን አመራረጥን፣ የሀሳቦችን እርስ በርስ መያያዝ ግጥምን የተሻለና ምሉዕ የሚያደርገው ከሆነ፤ ከሀሳብና አተያይ እሥረኝነት ነፃ መውጣት እንዳለብን ማመን የምንቸገር አይመሥለኝም፡፡ በግጥም ውቅር ብዙ ኢትዮጵያዊ ገጣሚያን የተሳካላቸው አይደሉም፤…ከጥቂቱ በቀር!
በሀሳብ ደግሞ የሚያስደስቱን አሉ፡፡… ከፍ ያለ እይታ፣ የተለየ ሽንቁር ያላቸው፡፡ ለምሳሌ የገጣሚ በላይ በቀለ ወያን  ‹‹አልነጋም›› የተሰኘ ግጥም ተመልከቱ፡-
ፀሐይ ስትወጣ- ‹‹ነግቷል›› ለምትሉ
ንጋት ላልገባችሁ- ጨለማዎች ሁሉ
አልነጋም ነው መልሴ- ለናንተ አኩኩሉ፡፡
አልነጋም
አልነጋም
አልነጋም
አልነጋም
እንደኔ ላለ ሰው
በረሀ ተወልዶ-በረሀ ላደገ
ፀሐዩ ጠላቱ ነች
ሰርክ የሚደበቃት- ጥላ እየፈለገ፡፡
ግጥሙ ላይ ትንተና አያሻንም፡፡ ሀሳቡ ጥልቅ ነው፤ ተምሳሌታዊም ነው - ከልጅነት አኩኩሉ ጋር ማዶ ለማዶ ያስቀመጣት የ ‹‹ንጋት›› ጉዳይ። የትርጓሜዋም ልዩነት የትየለሌ ነው፡፡ ንጋት ላንዱ ሲሣይ፤ ለሌላው ሥቃይ ነው፤ እያለ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ሀሳቦች ያሏቸው ወጣት ገጣሚያን በርካታ ናቸው፡፡ …ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም በሀሳቦቹ ከፍታ ይታወቃል፤… ታገል ሰይፉ ደግሞ በምትና ሙዚቃው ድምቀት አይረሳም፡፡ አሁን አሁን ሁለቱን ያጣመሩ ጥቂት ገጣሚያን ብቅ ብቅ እያሉ ነው። በዚህ ዘመን ትልቁ ጉድለት የንባብ ጉዳይ ነው። ከቀድሞ ግጥሞች ጋር ሲተያዩ፣ ለንፅፅርና ዝንቅ ሀሳቦችና ባህሎች እጥረት ያመጣው ያ ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር ሌላው ጣጣና፣ ልባችን ውስጥ ቦታ ያላገኘው እውነት ግጥሞችን ደግሞ መፃፍና ማብሰልን እንደ ድክመት ማየት ነው፡፡ ይሁንና በዓለማችን ላይ ትልቅ ናቸው የተባሉና ዘውድ የተደፋላቸው ገጣሚያን እማኝነት ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ … ደጋግሞ መጻፍ ግጥምን በእሳት እንደተፈተነ ወርቅ ብርቅርቅና ውድ ያደርገዋል፡፡
ታላቁና ዝነኛው ገጣሚ ዊልያም በልተር የትስ እንኳ በዚህ መንገድ እንዳለፈ እማኝነት የሰጡት የዘርፉ ተመራማሪዎች አሉ፡፡ “The study considers the various changes in manuscript from prior to publication. Yeats labored and lessly before he considered his poem ready for publication.”
በእርግጥም የትስ የመጽሐፉን ጥራዝ ማተሚያ ቤት ከማድረሱ በፊት በእጅጉ ይደክምባቸው እንደነበር እማኞቹ ብዙ ናቸው፡፡ … እንግዲህ ለእኛም ልብ ይስጠን ነው!… ይሁንና የእኛ ሀገር ግጥም ጣጣው ብዙ ነው፣ …. ቀናነትና ጥናትን ያቀናጁ ወጌሻዎች ያስፈልጉኛል፡፡  

Read 31208 times