Monday, 12 December 2016 12:20

የታሪካዊ ምሥጢራችን ፋና ወጊ መጽሐፍ!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 የመጽሐፉ ርዕስ፡- ዘፍ ያለው
                  ደራሲ፡- ሌተና ኰሎኔል ተፈራ ካሣ
                   የገጽ ብዛት፡- 340
                    ዋጋ፡- 150 ብር
             ገምጋሚ፡- ብርሃነሥላሴ ኃ/መስቀል

     ማርክ ክራመር  በቀዝቃዛው ጦርነት ዙሪያ  በኤም አይ ቲ ፕሬስ የሚዘጋጀው ‹‹ዘ ጆርናል ኦፍ ኮልድ ዎር››  የተሰኘው ጆርናል ኤዲተር ነው፡፡ “ሰፓይስ” በሚል ርዕስ በዚህ ጆርናል ላይ በተካተተው ጽሑፍ መግቢያ ላይ “Espionage and covert operations are notoriously difficult to study” ይላል- ስለላና ምሥጢራዊ ዘመቻዎችን ማጥናት የቱን ያህል አስቸጋሪ  እንደሆነ ሲያብራራ፡፡
እነዚህን ተግባራት ለማጥናትና ጽሑፎችን ለመጻፍ በድርጊቱ ውስጥ ተዋናይ መሆንንን ይጠይቃል፡፡ ያ ደግሞ ሕይወትን ሊያስከፍል ይችላል፡፡ እንደዛም ሆኖ በእንደነዚህ ዓይነት ተግባራት ላይ ምሥጢራዊነት እጅግ ስለሚበዛ በድርጊቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነውም የተሟላ መረጃ ለማግኘት እጅግ አዳጋች እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም ነው የስለላና ምሥጢራዊ ዘመቻዎችን የተመለከቱ ታሪኮች “በስማ በለው!” ሳይሆን ድርጊቱ ውስጥ በነበሩ ግለሰቦች  ሲተረኩ እጅግ ጣፋጭና ተዓማኒነት ያላቸው የሚሆኑት፡፡
የስለላ ሥራ በዓለም ላይ መቼ እንደተጀመረ እስካሁን ድረስ በግልጽ ባይታወቅም ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች፤ በተለይም ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የስለላ ተግባር ጎልቶ የወጣበት ጊዜ ነበር፡፡ የጦርነቱን መገባደድ ተከትሎም በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ እራሳቸውን ያገኙት ኃያላን ሀገራት፤ በምድሪቱ ላይ የኃይል ሚዛኑን የበላይነት ለመረከብ በምዕራቡና በምሥራቁ ጎራ ተሰልፈው ከባድ ወደ ሆነ መጠላለፍ ውስጥ ገብተው እንደነበር የሩቅ ጊዜ ትዝታ አይደለም፡፡
የቀዝቃዛው ጦርነት የማይረሳ ዋነኛ መለያውም በጊዜው ይከናወኑ የነበሩ “የሾተላዩ ሰላዮች” ዓይነት ለሁለት ወገን የሚሠሩ የምሥጢራዊ ወኪሎችና የበላይነቱን ለመያዝ በየቦታው የሚፈፀሙ ግድያዎች ታሪክ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ምሥጢራዊነትንና ግለሰቦችን መንታ ሰብዕና እንዲኖራቸው ያደርግ የነበረ ተግባር፣ ጠላት ተብለው የተፈረጁ ሃገራት መንግሥታዊ መዋቅርና ተቋማት ውስጥ ሰርጎ ለመግባት የሚያስችል ጥበብ የታከለበት ነበር፡፡
የወቅቱ ኃያላን ሃገራት በተለይም ደግሞ፣ አሜሪካና ሶቭየት ሕብረት በእጅጉ እዚህ ተግባር ውስጥ ተዘፍቀው ነበር፡፡ የስለላን ሥራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና በረቀቁ ዘዴዎች ለመደገፍ፣ የበቁ ሰላዮችንና ምሥጢራዊ ወኪሎችን ለመመልመል  ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ ያደርጉ እንደነበርም ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በተመሳሳይ ቡድን ውስጥ የተካተቱ ሃገራት እየተጣመሩ የተቃራኒን ጎራ የስለላ መዋቅር ለመበጣጠስ ጥረት አድርገዋል፡፡ አንዱ በአንዱ ቡድን ላይ የበላይነቱን ለመውሰድ በብርቱ ሲደክሙ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ጠላት በሚሏቸው ሃገሮች ላይ ሰላዮቻቸውን በመበተን የየሃገራቱን ምሥጢር ሲቦጠቡጡ፣ ወታደራዊ አቅማቸውን፣ የሚያደርጓቸውን ዝግጅቶችና የሚያራምዷቸውን ርዕዮተ ዓለሞች ሲሰልሉ፣ ፖለቲከኞችንና የተቃራኒ ጎራ ወኪሎችን ሲያስገድሉና ሲያሳፍኑ መዋል የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነበር፡፡
እነዚህ “የኢምፔርያሊስቱና የሶሻሊስቱ ጎራ” በሚል የተሰለፉ ሃገራት፣ በተለይ ከ1940ዎቹ አንስቶ በአፍሪካ ሃገራት ላይ የነበራቸውን ተቀባይነት ለማስፋፋት መረቦቻቸውን ዘርግተው የተንቀሳቀሱበት ወቅትም ነበር፡፡ በየሃገራቱ ላይ መረቦቻቸውን በመዘርጋት ሊያራምዱት የሚፈልጉትን ተግባር ለማከናወን ረቀቅ ያሉ የስለላ መዋቅሮችን በአፍሪካ ሃገራት ላይ ዘርግተው ተንቀሳቅሰዋልም፡፡    
በዚያን ወቅት ኃያላኑ ሃገራት የየጎራዎቻቸውን ርዕዮተ ዓለም በሌሎች፣ በተለይም ደግሞ አዳጊ በሚባሉት ሃገራት ላይ ለመጫን ሲጣደፉም የነበረበት ወቅት ነው። ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው እንደ ምሥራቅ አፍሪካ ባሉ ቦታዎች፣ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የነበረው የሁለቱ ጎራዎች ትንቅንቅና ሽኩቻ ደግሞ እጅግ አስገራሚና ፍትጊያ የበዛበት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዚህ ሽኩቻ ውስጥ ኢትዮጵያ አጭር በሚባል የጊዜ ልዩነት ውስጥ የሁለቱንም ጎራዎች ርዕዮተ ዓለም ተቀብላ ያስተናገደችበት ታሪካዊ አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር፡፡ መጀመሪያ ከምዕራቡ አለም ጋር ወግና የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ከአብዮቱ መፈንዳት በኋላ ደግሞ ወደ ምሥራቁ አለም ጠቅልላ የገባችበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነው  እ.ኤ.አ በ1977 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር አድርጋው የነበረው ጦርነት፤ የቀዝቃዛው ጦርነት አስተሳሰብ የተንጸባረቀበት ጦርነት ተደርጎ የሚወሰደው፡፡  ከ1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ እስከ አብዮቱ መባቻ ድረስ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ተወጥራ፣ ከወዲያ ወዲህ መላወስ ተስኗት የከረመችበት ጊዜ ነው፡፡ በወቅቱ በሹማምንቱ መካከል የነበረው የእርስ በእርስ ሹክቻ የገነገነበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህም ሃገሪቱ በሰከነ መንፈስ የውጭ ጠላቶቿን ሁኔታ እንዳትከታተል እንቅፋት ሆኖባታል፡፡ በስለላና በአፈናው መረብ ተወጥራ እንደነበር፣ የሌተናል ኮሎኔል ተፈራ ካሣ ‹‹ዘርፍ ለው የተሰኘ መፅሃፍ ይገልፃል (ገፅ 314) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች “ሃገሪቱ ለውጥ ያስፈልጋታል! መሬት ላራሹ!”። የሚለውን የትግል እንቅስቃሴያቸውን በተደራጀ ሁኔታ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በሰሜኑና ሰሜን ምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል አሰቃቂ ረሀብ ተከስቶ፣ “ገባሩ ሕዝብ በጠኔ ተመትቶ እንደ ቅጠል እየረገፈ ነው፡፡ ‹‹የሚቆረጥልን ደመወዝ አንሶናል፤›› የሚሉ ወታደሮች በሃገሪቱ አራቱም አቅጣጫ በጉርምርምታ ላይ ናቸው፡፡ ለንግሥና ያቆበቆቡ የቤተ መንግሥት ሰዎች፣ አፍንጫቸውን ነፍተው በንጉሡ ዙሪያ ተሰባስበው የሚሆነውን በጉጉት ይጠባበቁ ይዘዋል፡፡ ሹማምንቱና መኳንንቱ የአስተዳደር ሥራዎቻቸውን ቸል ብለው በየራሳቸው የግል የንግድ ሥራ በመጠመዳቸው በሃገሪቱ የፍትህና የአስተዳደር ተግባር እንዲዳከም ሆኖ፣ የመንግሥት መዋቅሩ በህዝብ ብሶት እየተንገጫገጨ ነው”  ከዚህም ባሻገር፣ ሹማምንቱ በተማሪ አመፅና ተቃውሞ ስም ወረቀት እያስበተኑ ንጉሡ የተሳሳተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ሊያደርጉ ሲሞክሩ ጥበበኞቹ የህዝብ ደህንነት ባለሙያዎቻችን ደርሰውበት ውርደትን እንዲከናነቡ አድርገዋቸዋል ይላል  መፅሀፉ፡፡ (ገፅ 172)
በእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች መላወሻ ያጡት ሃገሪቱና ንጉሡ በትካዜ ተውጠዋል፡፡ አዛውንቱ ንጉሥ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በአዕምሯቸው እየተመላለሱ እረፍት ቢነሷቸውም፣ አልጋቸውን ወርሶ ሃገሪቱን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የሚያሸጋግራት ሁነኛ ሰው የማጣታቸው ነገር ቢያብሰለስላቸውም ተስፋ ግን አልቆረጡም፡፡ በዋነኛነት ዘወትር አያሳፍረኝም በሚሉት ፈጣሪያቸው ተማምነዋል። ከፀሎትና እምነት በሻገርም ታማኝና ትጉህ ናቸው ከሚሏቸው ባለሟሎቻቸው ጋር ሆነው የጎበጠውን ለማቅናት፣ የደፈረሰውን ለማጥራት፣ የፈሰሰውን ለማፈስ፣ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ አብዝተው ይደክማሉ፤ ይዘክራሉ፡፡ በአዛውንት ጉልበታቸው  ጎንበስ  ቀና ይላሉ። በዚህ መካከል ግን፣  “ሲያመጣው ልክ የለው” እንዲሉ፣  ሃገሪቱንና ንጉሠ ነገሥቱን ከሌላ አቅጣጫ የሚወጥር ክስተት ተከስቷል ይሉናል ደራሲው፡፡   
ከዚህ ሁሉ ውጥረት በስተጀርባ ከብዙሃኑ የአገሬው ሰው የተሰወረ የአፈናና የስለላ ትንቅንቅን፣ በአለም የኃይል ሚዛን ላይ በከባድ ሚዛን ምድብ ውስጥ የተመደቡ ሃገራትን የስለላ አቅም የፈተነ፣ የድሀይቱን ምሥራቅ አፍሪካዊት ሃገር፣ የኢትዮጵያን “የህዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት” አገርን ያኮራ ተግባር የሚያስቃኝ መጽሐፍ ነው- ‹‹ዘፍ ያለው››፡፡
“ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” እንደሚባለው፣ ኰሎኔሉ፣ “አስጨናቂና እንቅልፍ አልባ የአፈና እና የስለላ ትንቅንቅ” በሚል መፅሃፍ ውስጥ በገለፁት ተልዕኮ ወስጥ ተሳታፊ የነበሩ፣ የሕዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ባልደረባ መኮንን ናቸው፡፡  ደራሲው ጥብቅ ምሥጢሮችን አዋቂ እንደሆኑም ከታሪኩ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ምሥጢር አጠባበቅን በተመለከተ እንዲህ ያስረዳሉ፡- “በምሥጢር የተሠራ በግልም ሆነ የአገር ጉዳይ እስከነ አካቴው /መጨረሻው/ ድረስ ተደብቆ ምሥጢር ሆኖ አያልፍም፡፡ ምሥጢር ሽታ አለው፣ የሚተንም ነው፡፡ የተወሰነ ዕድሜም አለው…”
ማናቸውም የአገርንና የሕዝብን ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚደረጉ ምሥጢር ነክ ጉዳዮች ሁሉ ሊሸከሟቸው በሚችሉ ዜጎች አዕምሮ ውስጥ መቆለፍ እንዳለባቸው እሙን ነው፡፡ የአገርን ምሥጢርን ጠብቆ እስከ ውጤትም ማቆየት፣ ከውጤትም በኋላ ቢሆን፣ የምሥጢርን ዕድሜ በትንሹ ከሃያ እስከ ሠላሳ ዓመት ማቆየት” ጠቃሚ ነው ይሉናል፡፡ ዛሬም ልጆቻቸው ከዓመታት በኋላ መጽሐፉን ለህትመት ብርሃን ሲያበቁት፤ “የአሳታሚው ማስታወሻ” በሚለው ስር፣ ልጃቸው ቴዎድሮስ ተፈራ ከገለፀው መረዳት እንደሚቻለው፣ ከመጠነኛ አርትኦትና ከአንዲት ሃረግ በስተቀር የቀነሰውና የጨመረው የለም፡፡
የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጉዳይን ዋነኛ መሠረት አደርጎ የተዋቀረው “ዘፍ ያለው” የተሰኘው መፅሃፍ፤ “የተደገሰን የእልቂት ሽል ማጨናገፍ አስፈላጊነቱን አምነውበት ከአገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው የነበሩት የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ ኰሎኔል ጋሌብ ሐጂ ዩኒስ አሊ፤ ወደ ኢትዮጵያ በመሰደዳቸው ብቻ በኢትዮጵያ ላይ ሠይጣናዊ ጠላትነት ያሳደሩ ሦስት አገሮች፡- በታሪክ ተመዝግበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር፣ የሶቪየቱ ዲፕሎማትና የኬጂቢ ሰው ጋር ሦስተኛው ዲፕሎማት፣ ‘ከአንድ አፍሪካዊት ዓረብ አገር’ የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረው ኰሎኔል አፍነው በመውሰድ፣ ኢትዮጵያን ሦስት ሆነው ብቻዋን በስለላና በአፈና ትንቅንቅ ሲገጥሟት፣ ‘አገሬ ላይ ነኝ’ ብላ ሳትንቅ የተቋቋመችው በዘዴ ነበር፡፡”   በማለት መፅሃፉ የታሪኩን አኩሪ ተልዕኮ ይዘከዝክልናል፡፡  
ሃገርን ከወራሪ ጠላት ለመታደግ የሚያስችል መረጃን ያቀበለ የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ የነበረን ኰሎኔል ለመጠበቅ ሲባል የተደረገ ውጥረት የተሞላበት ትንቅንቅ ነው፡፡ መፅሃፉ የሚተርከው፡፡ የሕዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ለሃገራቸው ሲሉ፣ በኃያላን ሃገራት የስለላ ተቋማት ጣልቃ ገብነት ወደ ሶማሊያ ኤምባሲ ታፍኖ የተወሰደውን ሶማሊያዊ ኰሎኔል ከአፋኞቹ እጅ ፈልቅቆ ለማውጣት “እንቅልፍ ለምኔ?” ብለው፣ ውሎና አዳራቸውን በቢሯቸው ውስጥ አድርገው የፈፀሙትን እልህ አስጨራሽ ግብግብ ያስቀኛል  የኮሎኔል ተፈራ ካሣ መፅሃፍ፡፡ “በአደገኛ ሰላይነቱ (የኬጂቢ ሰላይ) ከተሰጠው የዲፕሎማቲክ ሥራ ውጪ አልፎ ያልተፈቀደለትን በመሥራቱ /ፐርሶና ኖን ግራታ/ ተሰጥቶት ከአገር እንዲባረር ተደርጓል” (ገፅ 175) ያሉት ሰው ተባሮ ሲወጣ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ሲሳፈር፣ “ዛሬ ብታስወጡኝ ነገ በክብር ተመልሼ እንደምመጣ እንድታውቁት!” ብሎ ዝቶባቸው፤ ዳግም ተመልሶ ወደ ሃገራችን መግባቱን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? ከዲፕሎማቲክ ግኝኙነት ውጪ ሲንቀሳቀስ ተገኝቶ የተባረረ ዲፕሎማት፤ መንግስት ቢለወጥ እንኳ ዳግም ወደተባረረበት ሃገር እንዳይገባ የሚደነግገውን የቬይና ኮንቬንሽን በማንና ለምን ተጥሶ ወደ ሃገራችን ሊገባ ቻለ? ድርጊቱ በመፈፀሙ ለሃገራቸው ሲሉ የደከሙና በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ዋነኛ ተጠቃሽ የሆኑትን የጸጥታ ባለሙያዎቻንን (ደራሲውን ጨምሮ) ያሳዘነና ያስከፋ እንደነበር በሚጋባ በቁጭት ተርኳል፡፡      
የመጽሐፉ ዓቢይ የታሪኩ ማዕከል የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ በነበረው ኰሎኔል ዙሪያ የሚያጠነጥን ቢሆንም በአጠቃላይ በወቅቱ በሃገሪቱ የነበረው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዴት በውጥረቶች የተሞላ እንደነበር ደራሲው በጥልቀት ገልፀውታል፡፡
መፅሃፉ፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ጃንሆይ) በዙሪያቸው ያጋጠማቸውን ከባድ ፈተና እያስታወሱ ሲቆዝሙ ያስቃኘናል፡፡ ንጉሡ የገጠማቸው ፈተና፤ “አይጋፉት ባላጋራ” ዓይነት ሆኖ ሲሰማቸው፣ ደግሞ መለስ ብለው “እስካሁን የጠበቀን እግዚአብሔር ነው፡፡ አሁንም እሱ ነው ተስፋችን” እያሉ ሲጽናኑ፤ በስነ ጽሑፋዊ ጥበቡ እንድንሰማው ሲያደርገን፣ ሹማምንቶቻቸው፣ መኳንንቶቹና መሳፍንቶቹ በወሬ፣ በስብቅ፣ በሸፍጥ በአሉባልታ ምን ያህል ይጠላለፉ እንደነበር መረጃን መሠረት አድርጎ፤ ምሥጢራቸውን ሲካፍለን፣ ይህም በሕዝብ አስተዳደር ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ ይተነትንልናል፡፡ደራሲው የመጽሐፉ ዓቢይ ገፀ ባህሪ አድርጎ “በራሪ የሠላም አምባሳደር በሚል” የሰየመው፣ የሶማሊያው አየር ኃይል አዛዥ ኰሎኔል ጋሌብን ሕይወት ከልጅነት ጊዜው ጀምሮ በቅኝ ገዢ የእንግሊዝ የጦር መኮንኖች ቤት ያሳለፈውን፣ አየር ኃይሉን የተቀላቀለበትን ሁኔታ፣ በፖለቲካዊ አመለካከቱ ሳቢያ በወጉ ሳያጣጥመው ስለከሸፈው ጅምር የፍቅር ሕይወቱ፣ በአገሩ ሶማሊያ ላይ እንደ አልቅት ተጣብቀው ሀብቷን ስለሚቦጠቡጡ ወዳጅ ነን ባይ ሃገራት ስለሚሰማው ሰሜትና ስለደረሰበት በደል፣ በሃገራችን በስደት በቆየበት ጊዜ ያሳለፋቸውን ገጠመኞች እንዲሁም በጣልያን ሃገር በሮም ከተማ ዳግም በስደት ሲኖር ባደረገው ታጋድሎ፣ የኢትዮጵያ የውጭ መረጃ /ፎሪን ኢንተልጀንስ/ ሰዎች ስላደረጉለት ድጋፍና በመጨረሻም ባደረገው ፅናትና ተጋድሎ በመገረም፤ “የሮም ከተማ ከአፍሪካ ዳግማዊ ዘርዓይ ደረስን ወይንም አብዲሳ አጋን ልትፈጥር ይሆን?! (ገፅ 310)” ስላሉበት ዝርዝር ምሥጢር በጥልቀት ይተርክልናል፡፡
የሕዝብ ጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ መኮንኖችና ባልደረቦች ከ1953 መፈንቅለ መንግስት በኋላ ‹‹ተገፍተናል›› የሚል ስሜት ተሰምቷቸዋል፡፡ የእኛን ተግባር ሌሎች ታማኝ ነን ባዮች እንዲሠሩት ተደርጓል የሚል ቅሬታ ውስጣቸው ገብቷል፡፡ ከፍተኛ መኮንኖቹ በየአጋጣሚው ብሶታቸውን ይገልፃሉ (ገጽ 168)፡፡  “ደግሞስ ከእናንተ ምን ይጠበቃል? ተባልን፤ አመኔታ ከአጣን አሥር ዓመት አለፈን” ሲሉ አቤቱታቸውን እናነባለን፤ ቢሆንም ግን ስለ ሥራ ክፍላቸው አብዝተው ይጨነቃሉም ይላል- “ዘፍ ያለው”፡፡
“ስለ ኢንተለጀንስ ክፍሉ ሥራ ኃላፊነት፣ በተለይ ‘የጃንሆይንና የዘውዱን ክብርና ሞገስ ተዳፈሩ’ የምንላቸው ሰዎች ላይ ብቻ ማተኮር የለብንም፡፡ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ እንሥራ” (ገፅ 166) የሚል ሀገራዊ ስሜት በውስጣቸው የሚመላለስባቸው ስለመሆናቸውም ያስረዳናል፡፡ የተቋሙ ኃላፊ የበላይ መኮንኖችን የተከፋ ስሜት ለንጉሡ በማቅረብ የነበረውን ስሜት ለማደስ ሲውተረተሩም እናያለን፡፡ ይህም ተሳክቶላቸው ለሚካሄደው ዘመቻ መኮንኖቹን በነቃ ሁኔታ የሚያሳትፉበትን ታሪካዊ ክስተት መፍጠራቸው መጽሐፉ ይዳስሳል፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የሶማሊያ አምባሳደር፣ ከዲፕሎማሲ ሥራው ባሻገር ወዳጅ ከሚላቸው ሃገራት የሰለላ መዋቅሮች ጋር አብሮ የሃገሪቱን ምሥጢር በመሰለል ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ በተለይም ደግሞ  “ከአንበሳ መንጋጋ ሥጋ ፈልቅቄ ወስጃለሁ” ብሎ ካመነ ወዲህ ኩራትና ትዕቢት ልቡን ወጥሮታል፡፡ የፈለቀቀውን ሥጋ ከኢትዮጵያ በሆነ ዘዴ አሾልኮ በሃገሩ መሬት  ከሃገሩ መሪዎች ጋር ሊያላምጠው ቋምጧል፡፡ ለዚህም በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ ሁለት ቁመተ ሎጋ ኮማንዶዎችን ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ ወዲህ ደግሞ “የፈለቀቁትን ሥጋ አፋቸው ሳይከቱት መልሰን እንነጥቃቸዋለን” የሚሉት የኢትዮጵያ የሕዝብ የጸጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ መኮንኖችና ባልደረቦች፣ ሥራዎቻቸውን በተጠና እና ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ እያከናወኑ ነው፡፡ “/Mission Accomplished/ ተግባር ተፈፀመ!” ይሉናል። ግን እንዴት የቀረውን አንብባችሁ ድረሱበት- ከመፅሃፉ፡፡ ትገረማላችሁ፡፡ ትደመማላችሁ፡፡

Read 1896 times