Saturday, 10 March 2012 12:26

ብዙአየሁ ጀምበሩ አፋጣኝ እርዳታ ያስፈልጋታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ለሉሲዎች የደረት መከለካያ ትጥቅ ተሰጠ

የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የነበረችውን ብዙአየሁ ጀምበሩ ለመርዳት የሚደረገው ጥረት ቢቀጥልም ተጨዋቿ ሙሉ ለሙሉ ለመዳን የውጭ ህክምና ከ2 ወር ባነሰ ጊዜ ባገኝ ጥሩ ነው ስትል ለስፖርት አድማስ ተናገረች፡፡ ብዙአየሁ ለብሄራዊ ቡድን እየተጫወተች በልምምድ ላይ በሁለቱ ጉልበቶቿ ላይ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ይሄው ጉዳት ከስፖርቱ እንደምትገለል ምክንያት ከመሆኑም በላይ እየሰራች እንዳትኖር እክል  ፈጥሮበታል፡፡ ብዙአየሁ ሙሉ ለሙሉ ለመዳን 2 ግዜ ተመላልሳ በታይላንድ ባንኮክ ህክምና ማድረግ አለባት፡፡ በጉልበቶቿ ላይ በደረሰው ጉዳት በተመርቅኩበት የነርሲንግ ሙያ ለመስራት ያደረግኩትን ሙከራ ከ5 ቀናት በኋላ እንዳልቀጥል አድርጎኛል የምትለው ብዙአየሁ በየቀኑ ከጉዳቱ ጋር በተያያዘ ከሚያሳቃያት ልዩ ህመም ባሻገር ብቸኝነት እና ተስፋ መቁረጥ እየጎዳኝ ነው ብላለች፡፡ አስፈላጊውን ህክምና ለማግኘት ችዬ ከዳንኩ በስፖርቱ በመቀጠል በዳኝነት እና በአሰልጣኝነት ሙያ የመስራት ፍላጎት አለኝ ስትልም ለስፖርት አድማስ ተናግራለች፡፡ ብዙአየሁ በሴቶች እግር ኳስ ያሉ ተጨዋቾች በየክለቦቻቸው የዋስትና መብት ተገብቶላቸው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርባለች፡፡

ብዙአየሁ ጀምበሩ ወላጅ አልባ ሆና ያደገች ነች፡፡ እናቷን በ11 ዓመቷ አጥታታለች፡፡ በየዘመዱ እየተጠጋች በመኖር አድጋ በድሬዳዋ ከነማ ክለብ እየተጫወተች ለብሔራዊ ቡድን ደረሰች፡፡ በብሔራዊ ቡድን እየተጫወተች ልምምድ ላይ በደረሰባት አጋጣሚ ጉልበቷ ዞሮ ለከፍተኛ ጉዳት ተጋልጣለች፡፡  በሌላ በኩል ለ6 ዓመት ለብሄራዊቡድን የተጫወተችውን ብዙአየሁ ጀምበሩን ለመታደግ ከየአያቅጣጫቸው የሚደረገው ጥረት ግን እንደቀጠለ ነው፡፡ የቀድሞው እግር ኳስ ተጨዋች ዳዊት ጌታቸው በኢትዮጵያውያን ተጨዋቾችና ደጋፊዎች የበጐ አድራጐት ድርጅት  በኩል  ብዙአየሁ ጀምበሩን ለመርዳት የምናደርገው እንቅስቃሴ ከመጨረሻው ምዕራፍ መድረሱን ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡  እስማማለሁ በሚለው የቲቪ ፕሮግራም 15ሺ ብርና የሞራል ድጋፍ ማግኘቷን የገለፀችው ብዙአየሁ  የደደቢቱ ተጨዋች ምን ያህል ተሾመ ፖስተሯን አሳትሞ በሌክስ ፕላዛ ህንፃ በመለጠፍ ገቢ ሊያሰባስብላት  እየጣረ መሆኑን ገልፃለች፡፡ ስለ ብዙአየሁ ጀምበሩ ጉዳት  ቅ/ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና በስታድዬም በተጫወቱበት ወቅት  ብሄራዊ ድጋፍ እንዲያደርግላት በይፋ ሲጠየቅ ሰማሁ ያለው አቶ ዳዊት ጌታቸው ልጅቷን  በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በኩል ለመርዳት ያለንን ፍላጐት በመጀመሪያ ያሳወቅነው ለፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ ነበር ይላል፡፡ ከድሬዳዋ የትራንስፖርት ወጪዋን ከፍሎ ወደ አዲስ አበባ ካመጣት በኋላ የጉዳቷን ሁኔታ የሚያስፈልጋትን ህክምና የሚገልፁ ሰነዶች ወደ አሜሪካ ይዞ በመመለስ የበጎ አድራጎት የበላይ ጠባቂ የመረዳጃ ማህበር አብይ ኮሚቴ አባላት ሁለትና ሦስቴ ባደረጉት ስብስባ  ለህክምናዋ 75ሺ ብር እንድታገኝ አድርጓል፡፡ በረጅም ጊዜ የጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊነቱ የሚታወቀው እና በሰሜን አሜሪካ ቦስተን የሚኖረው አቶ ዳዊት ጌታቸው ይህች ወገናችን ቆማ እንድትሠራ ማድረግ አለብን ብሎ ባቀረበው ጥሪ በአጭር ጊዜ  ሙሉ ለሙሉ ህክምና አግኝታ እንድታገግም በምናደርገው ጥረት እንቀጥል ሲል ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡

በተያያዘ  ዜና አሁን ያለው የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቅርብ ጊዜ ወደ ለንደን ኦሎምፒክ ለማለፍ እስከመጨረሻው ምዕራፍ የተጓዘበትን ጥንካሬ በአድናቆት መከታተሉን የገለፀው  አቶ ዳዊት  ጌታቸው ትናንት ለብሄራዊ ቡድኑ የደረት መከላከያ ትጥቅ አበርክቷል፡፡ አቶ ዳዊት የፌዴሬሽኑን ፀሃፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ  ከ2 ወር በፊት ሳገኛቸው ተጨዋቾቹ በትጥቃቸው የደረት መከላከያ ልብስ የላቸውም ብሎ ሲነገረኝ በጣም ደነገጬ የትጥቅ እርዳታውን ለመለገስ በአፋጣኝ ወስኛለሁ ብሏል ፡፡ የደረት መከላከያ የሆነው የውስጥ ልብስ ለሴት ተጨዋቾች እጅግ አስፈላጊ ትጥቅ ሲሆን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሳይሟላ መቆየቱ ያሳስብ ነበር  ፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ የተለገሰው የደረት መከላከያ ትጥቅ ሲለበስ ተጨዋቾች ከደረታቸው እስከአንገታቸው ያለውን የሰውነት ክፍል ከማንኛውም ግጭት እንዲከላከሉበት ያስችላቸዋል፡፡

ለሉሲዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል በግል ሙሉ ትጥቅ መስጠታቸው መስማቴ እኔንም አነሳስቶኛል ያለው አቶ ዳዊት ጌታቸው  ወደፊትም በላቁ የድጋፍ ስራዎች ከሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ጋር የመስራት ሃሳብ አለኝ ብሏል፡፡

 

 

Read 2017 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:33