Print this page
Monday, 12 December 2016 12:31

የሰውነት ቢሻው የእግር ኳስ አካዳሚ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(9 votes)

 አድናቆት፣ ትኩረት፣ ድጋፍ - የሚያስፈልገው አገራዊ ራዕይ
      የሰውነት ቢሻውና ቤተሰቡ የታዳጊና ወጣቶች የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው። ስራ ከጀመረ 19 ወራት ተቆጥረዋል፡፡  በእግር ኳስ የመሰልጠን ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች የሚያስተናግድ ነው፡፡ በትክክለኛ የዕድሜ ደረጃ ሰልጣኞቹን እየመለመለ ይሰራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ120 በላይ ታዳጊና ወጣት ሰልጣኞችን በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች በመያዝ እያስተማረ ነው፡፡ ባለፉት የክረምት ወራት የሰልጣኞቹ ብዛት እስከ 270 ሁሉ ደርሶ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ፤ ከአሜሪካ ለእረፍት በሚመጡ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም አገር ውስጥ ባሉ የውጭ ዜጎች ሰልጣኞችን በማካተት ሰርቷል፡፡  በአካዳሚው በ4 የተለያዩ የዕድሜ መደቦች በመከፋፈል ስልጠና እየተሰጠበት ይገኛል። በመጀመርያው ምድብ 8፣ 9ና 10 ዓመት፤ በ2ኛው ምድብ 11፣ 12ና 13 ዓመት፤ በ3ኛው ምድብ 14ና 15 ዓመት እንዲሁም በ4ኛው ምድብ በ16ና በ15 ዓመት ታዳጊና ወጣት ሰልጣኞችን እየተቀበለ ይሰራል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የሚታዩትን መሰረታዊ ችግሮች ለማስተካከል የተነሳ ነው፡፡ የታዳጊዎችና የወላጆቻቸውን ፍላጎት መሰረት አድርጎም ተቋቁሟል። ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ የአካዳሚው መስራች ብቻ ሳይሆኑ ስራ አስኪያጅ ጭምር ናቸው፡፡ የእግር ኳስ  መሰረታዊ ስልጠናዎች ውጤታማ የሚያደርጉት ከ17 ዓመት በታች በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች ከተሰራባቸው መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ የአካዳሚ እንቅስቃሴያቸው ደረጃ በደረጃ በማሳደግ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለመለወጥ እንጂ ከገና ክጅምሩ በትርፍ ለመንበሽበሽ እንደማይሰሩበትም ገልፀዋል፡፡
የአካዳሚው ችግሮችና ፈተናዎች
አካዳሚው በመስራቹና በቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የስራ ፍቅርና ትጋት ያለፉትን 19 ወራት የተንቀሳቀሰው በርካታ ችግሮችና ፈተናዎችን በመጋፈጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው ፈተና የማሰልጠኛ ሜዳ ችግር ነው፡፡  ሰልጣኞቹን እያሰራ የሚገኘው በልዩ ድጋፍ እና ትብብር በነፃ  በተፈቀዱለት ሁለት ሜዳዎች ነው፡፡ የመጀመሪያው በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ትብብር ፍቃድ ያገኘበት የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲሆን በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ ጠዋት ከ1-3 ሰዓት በሁሉም ዕድሜ መደብ ያሉትን ሰልጣኞች ያሰራበታል።  ሁለተኛው ሜዳ ደግሞ ጦር ኃይሎች አካባቢ በፖሊስ ጊቢ የሚገኘው የኦሜድላ ሜዳ ነው፡፡ በየሳምንቱ ሰኞ፣ ረቡዕና አርብ ከ9-12 ሰዓት ዕድሜያቸው 16ና 17 ዓመት የሚሆናቸው የሚሰሩበት ነው፡፡
አካዳሚው ሁለቱንም ሜዳዎች በነፃ ድጋፍ ሲሰራባቸው ቢቆይም በዘላቂነት እና በበቂ ሁኔታ ለመጠቀም እንዳይችሉ  የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለስፖርት አድማስ የገለፁት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ ይህም  የጀመሯቸውን ስኬታማ አቅጣጫዎች እንዳያጓትትባቸው ሰግተዋል፡፡ ምናልባት ለሜዳዎቹ የኪራይ እንዲከፍሉ ቢጠየቁ መቸገራቸው አይቀርም፡፡  አካዳሚው አሁን ባለበት ደረጃ የስልጠና ሜዳዎችን በክፍያ መገልገል ይከብደዋል፡፡ በከተማዋ ያሉ ብዙዎቹ ሜዳዎች ለአንድ የስልጠና መርኃ ግብር ከ1500-3000 ብር የሚያስከፍሉ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ የሚጠቀሙበት የአበበ ቢቂላ ስታድየም ብዙ መሰናክሎች እያጋጠሙ ናቸው፡፡ የጤና ቡድኖች በየሳምንቱ ሜዳውን የኪራይ በመክፈል ይጫወቱበታል። አንዳንዴ  ግጥሚያዎች ሁሉ እየተካሄዱ ስልጠናዎች ይስተጓጎላሉ፡፡  በአጠቃላይ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እንደሚናገሩት ችግሩ ለመፍታት የሚችሉት በራሳቸው መሬት ላይ አካዳሚውን ማንቀሳቀስ ሲችሉ ነው፡፡ የከተማው መስተዳድር መሬት እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ አመልክተዋል፡፡ መሬት የለም ተብለዋል፡፡ “ወይንም ቶሎ ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ መሬት ቢሰጠኝ ማለዳ 12 ሰዓት ገብቼ 12 ሰዓት ሰርቼ ማታ እወጣ ነበር” ነው የሚሉት፡፡
የሰውነት ቢሻው የእግር ኳስ አካዳሚ ሌሎች ፈተናዎች  ከስልጠና ቁሳቁሶች እና ሌሎች መርጃ መሳሪያዎቹ የሚያያዝ ነው፡፡  በተለይ አካዳሚው በቂ የማሰልጠኛ ኳሶች የሉትም፡፡ ኳሶቹን በበቂ ብዛት ለሰልጣኞቹ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረትም  ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ተቸግሯል፡፡ በተለይ ደግሞ በተለያየ ዕድሜ ደረጃ ለሚገኙ ሰልጣኞች የተለያየ መጠን ያላቸው ኳሶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከሌሉ ስልጠናዎችን በተገቢው መንገድ እንዳይሰሩ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ዕድሜያቸው 9 እና 10 ዓመት የሚሆናቸው የአካዳሚው ሰልጣኞች በ3 ቁጥር ኳስ መስራት ነበረባቸው፡፡ ግን ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በመጀመርያ 3 ቁጥር ኳሶች በአገር ውሰጥ ገበያ የሉም፤ ዋጋቸውም ውድ ነው፡፡ ይህም ችግር ህፃናቱን ለዕድሜያቸው በማይመጥን ሁኔታ በ5 ቁጥር ኳስ ስልጠናውን እንዲወስዱ አስገድዷል፡፡ 5 ቁጥር ኳሱን አላልቶ በመንፋት፤ የሽፋኑን ቆዳ በመላጥ ስልጠናውን ለመቀጠል ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ጊዜያዊ መፍትሄ የሚያወጣ አይደለም፡፡  5 ቁጥር ኳስም ቢሆን ዋጋው ውድ ነው በበቂ ብዛት ለሰልጣኞች ማቅረብ እየከበዳቸው ሲሆን የአንዱ ዋጋ እስከ 2800 ብር ነው፡፡
የአካዳሚው ችግሮች በኳሶቹ እጥረት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ለስልጠና የሚያስፈልጉ ሌሎች ቁሳቁሶችም በበቂ ሁኔታ አልተሟሉም፡፡ ቢትስ፣ ኮንስ፣ ሃርድል፣ ላደርና ሌሎች የስልጠና መርጃ መሳሪያዎች በቂ አይደሉም፡፡ ለአካል ብቃት ማሳደጊያ የሚሆኑ የፊትነስ መሳሪያዎች ቢያስፈልጉም በአቅም ማነስ ለማሟላት አልተቻለም፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ለስፖርት አድማስ እንደተናገሩት ባለፉት 19 ወራት ለአካዳሚው ለማሰልጠኛ ኳሶች እና ሌሎች የስልጠና መርጃ መሳሪያዎች ከ150 ሺ ብር በላይ ወጭ አድርገዋል፡፡ ይህ ወጭ ለአሰልጣኞች በየወሩ  ከ42 ሺ ብር በላይ የሚከፈለውን ደሞዝ   ሳይጨምር ነው፡፡ የአካዳሚው ብቸኛ ገቢ ከሰልጣኞቹ የሚቀበለው 500 ብር ወርኃዊ ክፍያ ብቻ ነው። በልዩ ድጋፍ ያለ ወርሃዊ ክፍያ የሚሰለጥኑ ጥቂት አለመሆናቸውም ገቢውን ይቀንሰዋል፡፡ ስለሆነም ባለፉት 18 ወራት አካዳሚው ከወላጆቹ ድጋፍ በማሰባሰብ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ሰልጣኞቹ የሚለብሷቸውን ማልያዎች ሊያሟላ የቻለውም ከወላጆች በተሰባሰበ ገንዘብ ነው። በተለያዩ ጊዜያት መጠነኛ ድጋፍ ለአካዳሚው የሰጡ ተቋማትም አሉ፡፡ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የኳሶች ድጋፍ አድርገዋል፡፡ አንዳንድ የስፖርት ትጥቅ መሸጫ ሱቆችም የተወሰነ ድጋፍ ነበራቸው፡፡ አካዳሚው ለተጋረጡበት ፈተናዎች ዋናው መፍትሄ የስፖንሰሮች ድጋፍ ነበር፡፡ ይሁንና ምንም አይነት የስፖንሰር ድጋፍ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ከባለድርሻ አካላት ማለትም ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከመንግስት፣ ከእግር ኳስ ክለቦች መገኘት ያለባቸው ድጋፎች መጠናከር አለባቸው፡፡ “እኔ ልጅ እያፈላሁ የምሸጥ ሰው አይደለሁም፡፡ አገሩን ጥሎ እንዲሰደድም አይደለም፡፡ አገሩን እንዲወድ፤እንዲያስጠራ በስነምግባር የታነፀ ትውልድ እንዲኖር ነው የምሰራው›› በማለት ዓላማቸውን የሚገልፁት አሰልጣኙ፤‹‹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲሸነፍ ፤ ሁሉም ያዝናል መንግስት ያዝናል፡፡  ታድያ ከመሰረቱ እንዲሰራ ሁሉም ባለድርሻ አካል ለምን ይሆን የማይደግፈው፡፡ ለምንድነው ትኩረት መስጠት የማይቻለው፡፡” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
የአካዳሚው ፍሬዎች
የሰውነት አካዳሚ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትኩረት እንደሚያንሰው የስፖርት አድማስ ዘገባ በመስክ ጉብኝት ያረጋገጠው ነው፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከላይ በተጠቀሱት የተለያዩ የአቅም ችግሮች ፈተናዎች ቢበዙባቸውም ስራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ግን ያስደንቃል፡፡ በአበበ ቢቂላ ስታድዬም በሁሉም የእድሜ መደቦች የሚያከናውኗቸውን ስልጠናዎች ባለፈው እሁድ ባስጎበኙን ወቅት የታዘብነውም ይህንኑ ትጋት እና የዓላማ ቁርጠኝነት ነው፡፡ በአበበ ቢቂላ ስታድዬም ሜዳ ላይ “ወሬ አታውሩ፤ ቄንጥ አታብዛ፤ በትክክል ስራ” እያሉ እያንዳንዱን ሰልጣኝ በስም እየጠሩ ሲያሰሩ ተመልክተናቸዋል፡፡ ከሌሎች አሰልጣኞቻቸው ጋር ሆነው በልዩ ክትትል ስልጠናዎችን ሲያካሄዱ በሚያስደንቅ ትኩረት እና የስራ ፍላጎት ነበር። ከታዳጊዎቹ ጋር አብረው ኳስ ይጫወታሉ፡፡ ልጆቹም “ኮች፤ ጋሼ” እያሉ ሰውነትን በመጥራት ስልጠናቸውን በትጋት ይሰራሉ፡፡ ታዳጊዎቹ በተለይ እድሜያቸው ከ11 እስከ 13 የሚሆናቸው ፍላጎታቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ ማንን ተምሳሌት እንደሚያደርጉ ሲጠየቁ ሜሲ እና ክርስትያኖ ሮናልዶን መሆን ይፈልጋሉ፡፡ እኔ ሜሲ ነኝ፤ እኔ ክርስትያኖ ሮናልዶ እያሉ ሲከራከሩ ደስ ይላሉ፡፡ ሮናልዶ ነኝ ያለን ታዳጊ ስልጠናቸውን ከመጀመራቸው በፊት በራሱ የአበበ ቢቂላን ስታድዬም 5ቴ እንደዞረ ሲነግረን ነበር፡፡
ገና 10 ዓመት ያሞላቸው ህፃናትም በስልጠናው ስር ይገኛሉ፡፡ ወንድሞቻቸውን ተከትለው የመጡ ናቸው፡፡ ወደ አካዳሚው መግባት ይፈልጋሉ፡፡ አምስት፤ ስድስት ሰባት ዓመት የሚሆናቸው እነዚህን ህፃናት ጭምር ሰውነት ቢሻው በቅርብ ክትትል ከኳስ ጋ እያላመዷቸው ነው፡፡ ህፃናቱም ወላጆቻቸውን ወደስልጠናው መግባት እንደሚፈልጉ ሲጠይቁ፤ ፍላጎታቸውን ኳሶችን በማንከባለል ሲያሳዩ ነበር፡፡  የፊርማ ሚሊዮን ብር ተከፍሎኝ ክለብ ይዤ ማሰልጠን እችል ነበር የሚሉት ሰውነት ቢሻው፤ በታዳጊዎች ላይ የምሰራው ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ስለምፈልግ ነው ይላሉ፡፡ በወላጆችና ልጆቻቸው የሁል ጊዜ ተሳትፎ አበረታቷቸዋል፡፡
የአካዳሚው ፍሬያማነት የሚያሳዩ ሌሎች ምልክቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሚሆናቸው ሰልጣኞችን ያሰባሰበው ቡድናቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ለአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎች ያደርጋሉ፡፡ ተጋጣሚያቸውን በሰፊ የግብ ልዩነት የማያሸንፉ ናቸው፡፡ ሰልጣኞቹ በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን በትምህርታቸው ጎበዝ፤ በስነ ምግባራቸው የታነፁ ሆነዋል፡፡ እስከ 15 ዓመታቸው ድረስ በሚያገኙት ስልጠና ከቴክኒኩ እና ከዲስፕሊኑ ባሻገር በአካል ብቃታቸው ሰውነታቸው እየዳበረ፤አጥንታቸው እየጠነከረ ቁመታቸው እያደገ ነው የሚሄዱት፡፡ ከ15 ዓመት  በኋላ ደግሞ ጡንቻቸው መፈርጠም ይጀምራል፡፡ ይሁንና ጡንቻን ለማውጣት ለማጠንከር በሜዳ ላይ ከሚሰጡ ስልጠናዎች ባሻገር በጂም የሚሰሩ እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ናቸው፡፡  በሰውነት አካዳሚ ግን የጂም እንቅስቃሴዎችን ለመስራት የሚቻልበት አቅም የለም፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ክለቦች በእድሜ አይደለም የሚሰሩት፡፡ ብዙውን ጊዜ ተጨዋቾችን የሚመለምሏቸው በቤተሰብ፤ በዘመድና በአጓጉል መጠቃቀም እንደሆነ ይነገራል፡፡ የራሳቸውን መልማይ ቀጥረው እንኳን አይሰሩም፡፡ የሚገርመው ነገር አንድም ክለብ ለሰውነት እግር ኳስ አካዳሚ ድጋፍ እየሰጠ አይደለም፡፡ አንዳንዶች ግን ከ17 ዓመት በታች ውድድር ለመግባት ብለው በትክክለኛ እድሜ በሰውነት የተመለመሉ ሰልጣኞቻችን ሲወስዱ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ነው፡፡ ይህን አካሄድ ለአካዳሚው መታወቅ የተወሰነ እገዛ ይኖረዋል በሚል ስሜት ብዙም እነ አስልጣኝ ሰውነት አልታቃወሙትም።  ወደፊት ግን አስፈላጊውን መመርያ አዘጋጅተን በህግ የምንከላከለው ነው ብለዋል፡፡
ብዙ ክለቦች በመንግስት ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ ነው የሚሰሩት፡፡ በባንክ፤ በመድህን ተቋማት፤ በክልል መንግስታት እና የከተማ መስተዳድሮች ስር ያሉ ክለቦች ሁሉ በርካታ በጀት በማዋል በእግር ኳሱ እንደሚንቀሳቀሱም ይታወቃል፡፡ ያ ሁሉ በጀት በታዳጊና ወጣት ደረጃ ካልተሰራበት ለክለቦች ዘላቂ እድገት አይሆንም፡፡ ስለሆነም ከሚሰጠው በጀት የተወሰነውን ለታዳጊዎች ድጋፍ እንዲያውሉ በትኩረት መስራት አለባቸው፡፡
የሰውነት የእግር ኳስ አካዳሚ ባለፉት 19 ወራት ባከናወናቸው ተግባራት የኢትዮጵያ  ክለቦች እየተጠቀሙ ናቸው የሚለው በአካዳሚው የ15 የ16 ዓመት ሰልጣኞችን የያዘው አሰልጣኝ ሰለሞን ባዩልኝ ይባላል፡፡ ፌደራል ፖሊስ፣ ቦሌ ገርጂ፣ ቡራዩ ከነማ እና መድሃኒያለም የተባሉ ክለቦችን  በብሄራዊ ሊግ እና ሱፕር ሊግ በማሰልጠን ልምድ ያካበተ ነው፡፡ እሱን ጨምሮ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጋር የሚሰሩት አሰልጣኞች 3 ናቸው፡፡ በስፖርት ሳይንስ  የማስተርስና የባችለር ዲግሪዎች ያላቸው በካፍ ደረጃ የስልጠና ሰርተፊኬት የወሰዱ ናቸው፡፡ ናቸው፡፡
ባለፈው ዓመት ከአካዳሚው 15 ዓመት 17 ዓመት የሚሆናቸው 9 ሰልጣኞች በተለያዩ ክለቦች ሀ - 17 ቡድኖች መግባታቸውን የሚናገረው አሰልጣኝ ሰለሞን ባዩልኝ ነው፡፡ የሰውነት አካዳሚ ፍሬ የሆኑት እነዚህ 9 ልጆች ለመብራት ኃይል፣ ለደደቢት ፣ ለጊዮርጊስና ለወላይታ ዲቻ ክለቦች የተሰጡ ናቸው፡፡  በወጣቶች የስፖርት አካዳሚ የነፃ ትምህርት እድል ያገኘ ሰልጣኝም አለ፡፡ በቅርቡ አንድ የአካዳሚው ልጅ ወደ ቱርኩ ክለብ ጋላታሰራይ የሙከራ እድል አግኝቶ ሄዷል፡፡ በአሜሪካ የነፃ ትምህርት እድል አግኝተው የሄዱ ሌሎች የአካዳሚው ፍሬዎችም አሉ፡፡

             ‹‹አካዳሚው የልጆቻችንን ፍላጎት የምንለካበት ነው፡፡ ››
                አቶ ሬድዋን በድሩ

       ሬድዋን በድሩ እባላለሁ፡፡ በሙያዬ ነጋዴ ነኝ። የአገራችንን እግር ኳስ ደጋፊ ሆኜ እከታተል ነበር። በደርግ ጊዜ  ስታድዬም ውስጥ በተፈጠረ ረብሻ፤ ትዝ ይለኛል ትግል ፍሬ እና መቻል ሲጫወቱ ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ፤ ብዙ ሰው ተጎዳና ስታድዬም መግባቱን ተውኩት፡፡
ዛሬ ወደ አካዳሚው የመጣሁት  4 ዓመት ሊሞላው አራት ወር ከቀረው ልጄ ጋር ሲሆን ታላቁ የሆነው ሌላው ልጄ ሳሚር ይባላል፤ የአካዳሚው ሰልጣኝ ሆኖ ከገባ ሁለት ቀኑ ነው፡፡ እኛም እሱን ተከትለን ወደ አበበ ቢቂላ ስታድዬም መጥተናል፡፡ ሳሚርን ወደ አካዳሚው ያስገባሁት የእህቴን ልጅ ለውጥ ተመልክቼ ነው፡፡ ልጆቹ ፍላጎት አላቸው፣ በሂደት ብዙ ለውጥ እንደሚኖርም አምኜበታለሁ፡፡ አካዳሚው የልጆቻችንን ፍላጎት የምንለካበት ነው፡፡
ማንም ወላጅ የልጆቹን ፍላጎት እና ችሎታ መረዳት የሚችለው በለጋ እድሜያቸው ነው፡፡ ትምህርታቸውን እየተማሩ ጎን ለጎን ሁሉንም ነገር እንዲሞክሩ፤ እንደተሰጥኦዋቸው እንደዝንባሌያቸው ሙያ እንዲፈልጉ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ክትትል ወላጆች ልጆቻቸው ምን እንደሚፈልጉ የሚረዱበትን እድል ይፈጥራል፡፡  በአጠቃላይ የአካዳሚውን እንቅስቃሴ ገና በሁለት ቀን በታዘብኳቸው ሁኔታዎች አርክቶኛል፡፡ ሴት ልጆችም አሉኝ፡፡ እነሱም በዚህ አይነት መስመር እንዲያልፉ ነው የምፈልገው፡፡ ሁሉም  ልጆቼ ስፖርት ይወዳሉ፡፡ በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በውሃ ዋና ፍላጎት አላቸው፡፡

               ‹‹ልጆች አገር ይረከባሉ፤ ያስጠራሉ ከተባለ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል፡፡›› አቶ
                 ዮሃንስ ነሲቡ

      ዮሃንስ ነሲቡ እባላለሁ፡፡ በብሩህ ተስፋ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ምክትል ዲያሬክተር ሆኜ እየሰራሁ ነው። የእኔን ልጆች  ወደ አካዳሚው ያስገባኋቸው ባለፈው ክረምት ነው፡፡ ጋሽ ሰውነት በጣም ታዋቂ እና ስኬታማ አሰልጣኝ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ብዙ ዓመታትን የሰራ ባለሙያ በመሆኑ በሚሰጣቸው ስልጠና ጥሩ ክህሎት እንደሚያስገኝላቸው እምነቱ አለኝ፡፡ ሜዳ ላይ የአርሰናል ማልያ ለብሶ የምታየው አንደኛው  ልጄ  ሙሴ ዮሃንስ ይባላል፡፡  13 ዓመቱ ነው፤ በጣም ለእግር ኳስ ፍቅር አለው፡፡ በአካዳሚው ልጆቻችን በጣም ቆንጆ ስልጠና እያገኙ ስለሆነ ደስተኞች ሆነናል፡፡ የሚገርምህ ከባለቤቴ ጋር እነሱን ተከትለን እየመጣን  እኛም ስፖርተኞች እየሆንን ነው፡፡ በርግጥ ወላጆች ልጆች ወደ ትምህርት እንዲያተኩሩ ይፈልጋሉ፡፡ ግን ከትምህርት ውጭ ያሉ ፍላጎቶቻቸውን በመመልከት ክህሎታቸውን አሳድገው ሙያቸው ሊሆን በሚችል ስልጠና እንዲሰሩ መደገፍም ተገቢ ነው፡፡ እግር ኳስ መዝናኛ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር የአካል ብቃትን የሚያዳብር፤ ቅልጥፍናን የሚሰጥ፤ አዕምሮን የሚያሳድግ  ስፖርትም ነው፡፡ በአጠቃላይ ስፖርት የመጨረሻው ግብ ደስታ ነው፡፡ በአግባቡ ሰርተህበት ውጤታማ ስትሆን በጣም ያስደስታል፡፡
የሰውነት አካዳሚው በቂ ኳስ፤ ትጥቅ ያስፈልገዋል። በተለይ ደግሞ ስልጠናውን የሚያካሂድበት ይህ ሜዳ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ  ልጆች  አገር ይረከባሉ፤ ያስጠራሉ ከተባለ በሁሉም አቅጣጫ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

             ‹‹አካዳሚው የአዲስ አበባ ምርጥ ተጨዋችን ሊያወጣ ይችላል፡፡››
                አቶ ታምራት አገኘው
 
      ታምራት አገኘው እባለለሁ፤ በግል ስራ ነው የምተዳደረው፡፡ በአካዳሚው ላለፉት 8 ወራት ሲሰሩ የቆዩ የ13 እና የ10 ዓመት ልጆች አሉኝ፡፡  ልጆቼን ወደ አካዳሚው ለማስገባት የወሰንኩት ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር በመደገፍ ነው፡፡ አቶ ሰውነት በእግር ኳስ ከፍተኛ ልምድ ያለውና የተከበረ ባለሙያ እና አሰልጣኝ እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ ተወልጄ ያደግኩት በአዲስ አበባ ነው፡፡ አበበ ቢቂላ ስታድዬም ከመገንባቱ በፊት በዙርያው ከ8 በላይ ሜዳዎች ነበሩ፡፡ በእነዚህ ሜዳዎች ጠዋት ማታ የምጫወት ነበርኩ፡፡ ዛሬ የሰውነት  አካዳሚን እንቅስቃሴ ስመለከት ተስፋ የማደርገው  የአዲስ አበባ ምርጥ ተጨዋች ሊያወጣ እንደሚችል አምኜበት ነው፡፡ እንደምታውቀው በፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች  ሆነ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከአዲስ አበባ የሚገኝ ምርጥ ተጨዋች ከጠፋ ቆይቷል፡፡ በከተማዋ ሜዳ የለም፤ ድሮ ከአዲስ አበባ በኳሱ ተሰጥኦ ያላቸው ብዙ ልጆች  በየሰፈሩ ካሉ ሜዳዎች የሚገኙ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ሜዳዎች በመጥፋታቸው ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆች ከከተማዋ እያገኘን አይደለም፡፡ እናም የሰውነት አካዳሚ መፍትሄ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ እግር ኳስ እንዲህ ከስር መሰረቱ በታዳጊዎች ላይ ተመስርቶ ስልጠና እየተሰጠበት መንቀሳቀስ ይኖርበታል።  ልጆች በእድሜያቸው ተገቢውን ስልጠና አግኝተው ማደግ አለባቸው፡፡ በአካዳሚው የሚሰጠውን ስልጠና  እያስተዋልክ ይመስለኛል፡፡ የ11ና የ12 ዓመት ልጆች ኳሷን ሲያንከባልሉ፤ ሲቀባበሉ፤ ሲቆጣጠሩ፤ ታክል እየገቡ፤  ቦታ ይዘው ሲጫወቱ፤ አብረው ሲያጠቁና ሲከላከሉ፤ አንዳንዶቹ  የሊብሮን ሚና ሲጫወቱ የሚያደንቅ አይደለም ወይ፡፡ በቃ ይህ ነው መፍትሄው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ብዙ ተስፋ የምናይባቸው ታዳጊዎች የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው፡፡ ስለሆነም የከተማው መስተዳድር ለአካዳሚው ድጋ በመስጠት ትልቁን ሃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡ በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ባለድረሻ አካላት መረባረብ እንደሚኖርባቸው ነው ጥሪ የማቀርበው፡፡ ጋሽ ሰውነት እኮ ብዙ ልጆችን በነፃ እያሰለጠነ ነው፡፡ ሌሎች ልጆች  በሜዳው ዳር ዳር ቆመው በስልጠናው ለመግባት የሚያሳዩትን ፍላጎት አያየህ አይደለም፡፡ የእነሱን ፍላጎት ለማሳካት  ድጋፎች መጠናከር አለባቸው፡፡

               ‹‹አካዳሚው በራሱ ሜዳና የስፖርት መሰረተ ልማቶች መጠናከር አለበት››
                 አቶ አስፋው አየለ
   
      አስፋው አየለ እባላለሁ፡፡ አበበ ቢቂላ ስታድዬም ሆኖ ሳይታጠር በፊት በነበሩት ሜዳዎች ኳስን እየተጫወትኩ አድጊያለሁ፡፡ ዛሬ ግን ልጆቻችን የሚጫወቱበት ሜዳ በአዲስ አበባ ከተማ የለም ማለት ይቻላል፡፡ የሚገርምህ  ልጆቼን በእረፍት ቀናቸው ኳስ የማጫውተው ሱልልታ ድረስ እየወሰድኩ ነበር፡፡
እንዲህ ሩቅ እየተጓዝን ስንጫወት በልጄ ችሎታና ፍላጎት አንድ ወዳጄ ይገረም ስለነበር ትልቅ ቦታ እንዲደርስ ለምን  ሰውነት አካዳሚ አታስመዘግበውም ብሎ መከረኝ፡፡ አራቱንም ልጆቼ ይሄው በአካዳሚው አስመዝግቤ ስልጠናውን እንዲያገኙ አድርጊያለሁ፡፡ በአካዳሚው ሲሰለጥኑ ከ8 ወር በላይ ሆኗቸዋል፡፡  
ዛሬ ልጄ ምርጥ ችሎታ እያሳየ በማደጉ ለሚማርበት ትምህርት ቤት ቡድን ዋና ተሰላፊ ሆኖ እየተጫወተ ነው። ሌሎቹ ልጆቼ 3ቱም ሴቶች ናቸው  በጣም ከፍተኛ ለውጥ እያሳዩ ነው፣ ሴቶችንም የሚያሳትፍ አካዳሚ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ግን ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡  
አካዳሚው በልጆቻችን እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን በቅርበት እየተመለከትነው ነው፡፡ የባለድርሻ አካላት ድጋፎችን በበቂ ሁኔታ የሚያገኝ ከሆነ ከፍተኛ ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል  አምነንበታል፡፡
ስለዚህም የሰልጣኞች ወላጆች ጋሽ ሰውነትን በተለያየ መንገድ ድጋፍ እያደረግልነት እያበረታታነው ነው፡፡  
የአካዳሚው 1ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተመካክረናል፡፡ ባደረግናቸው መዋጮዎችም የተወሰኑ ድጋፎችን ማረግ ችለናል፡፡
ወደፊትም አጠናክረን የምንቀጥልበት ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን አካዳሚው የራሱን ሜዳ ማግኘት አለበት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ትኩረት አድረጎለመሬት ጥያቄው ምላሽ እንደሚሰጥ ተስፋ እያደረግን ነው፡፡ አካዳሚው በራሱ ሜዳና የስፖርት መሰረተ ልማቶች መጠናከር አለበት፡፡
ሜዳ ቢገኝ ቤተሰቡ የበኩሉን ምክክር አድርጎ አካዳሚው የሚያስፈልገውን ደረጃ ባሟላ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ በሚያደርጉ ትብብሮች ለመስራት ሊነሳሳ ይችላል፡፡

              ‹‹ የሰውነት አካዳሚን ተምሳሌት በማድረግ ሌሎች አካዳሚዎች እንዲኖሩን እመኛለሁ፡፡››
                     አቶ ሙሉ ኡርጌ
       
     ሙሉ ኡርጌ እባላለሁ ነጋዴ ነኝ፡፡ በአካዳሚው ሰልጣኞች ያሏቸው ወላጆች ተወካይ ሆኜ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡   በአካዳሚው ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ የ12 እና የ14 ዓመት ናቸው፡፡ አካዳሚው የራሱ ሜዳ ያስፈልገዋል፡፡ በሁሉም የእድሜ መደቦች ያሉትን ሰልጣኞች በበቂ ሁኔታ ለማሰራት የሜዳ መጠንና የሰዓት መጣበብ ጫናዎች ስለሚፈጥር ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በሰውነት ብርታት እና የተወሰነ አቅም ልጆቻችን በሚያገኙት ስልጠናና እያሳዩ ባሉት እድገት ሁላችንም እየረካን ነው፡፡ ግን አካዳሚው በሚያስፈልገው ፍጥነት እና ሂደት ለመስራት ብዙ አቅሞች የሉትም፤ የኛ ድጋፍ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑና ሌሎች ተቋማት አካዳሚውን እንደትምህርት ቤት  እውቅና ሰጥተው በሚችሉት ድጋፎችን  ማድረግ አለባቸው፡፡
በርግጠኝነት ከዚህ አካዳሚ ወደፊት በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አገርን የሚወክሉ ልጆች ይወጣሉ፡፡ በእኔ በኩል የሰውነት አካዳሚን ተምሳሌት በማድረግ ሌሎች አካዳሚዎች እንዲኖሩን እመኛለሁ፡፡

Read 5169 times