Monday, 12 December 2016 12:41

ፌስቡክ፣ ማይክሮሶፍት፣ ጎግልና ትዊተር ሽብርን ለመዋጋት ተስማሙ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ታላላቆቹ የአለማችን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፌስቡክ፣ ማይክሮሶፍት፣ ጎግልና ትዊተር በማህበራዊ ድረገጾች አማካይነት የሚሰራጩ ከሽብርተኝነት ጋር የሚገናኙ መረጃዎችን በማስቆም ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ተስማምተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ የጋራ የመረጃ ቋት በመፍጠርና የሽብር ቡድኖችን የፕሮፓጋንዳ መረጃዎችን የሚያሰራጩ የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎችን በመከታተል መሰል መረጃዎች እንዳይሰራጩ ለማገድ ማቀዳቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
“ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የጽሁፍ፣ የምስልና የቪዲዮ መረጃዎች እየተከታተልን በመገምገም እንዳይሰራጩ እናግዳለን፣ የሚመለከታቸው አካላት እርምጃ እንዲወስዱም መረጃ እንሰጣለን” ብለዋል፤ ኩባንያዎቹ በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጡት የጋራ መግለጫ፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት ባለፈው ጥር ወር ላይ ከአፕል፣ ፌስቡክ፣ ማይክሮሶፍትና ትዊተር ኩባንያዎች ተወካዮች ጋር ተመሳሳይ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ትዊተር ባለፈው ነሃሴ ወር ሽብርተኝነትን የሚያስፋፉ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን ከ235 ሺህ በላይ አካውንቶችን በመዝጋት ከአገልግሎት ውጭ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

Read 1739 times