Monday, 12 December 2016 12:43

“ሱፐርቴክ” 12 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ ይቆጥባል ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 የኢጣሊያ ቴክኖሎጂ ስሪት የሆነው ሱፐርቴክ የተባለ መሳሪያ የከባቢ አየር ብክለትን እንደሚቀንስና የነዳጅ ፍጆታን እንደሚቆጥብ ተገለጸ፡፡
ባለፈው ሳምንት መሳሪያው በመንገድ ትራንስፖርት አዳራሽ በተዋወቀበትና ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው በተገለጸበት ወቅት፣ የበካይ ጋዝ ልቀትን 80 በመቶ በመቀነስ የአካባቢ ብክለትን እንደሚታደግ፣ ከ6-12 በመቶ የነዳጅ ፍጆታ እንደሚቀንስ፣ የመኪና ዕድሜ እንደሚያስረዝም፣ ለሞተር የበለጠ ጉልበትና ዕድሜ እንደሚሰጥ፣ የጥገና ወጪ ዝቅተኛ እንደሆነና ጪስ ማውጫ እንደሚያፀዳ ወይም ዝቃጭ የመፍጠር አቅሙ አነስተኛ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ሱፐርቴክ እነዚህን ጥቅሞች የሚሰጠው በነዳጅ መያዣ በርሜል ወይም ታንክ ውስጥ በነዳጅ ውስጥ ከወለሉ ¾ ሴ.ሜ ከፍ ብሎ ሲንጠለጠል እንደሆነ የጠቀሱት የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ባልደረባ አቶ ዮሐንስ ወ/ገብርኤል፤ መኪናው ሲንቀሳቀስ የነዳጅና የኦክስጅን ውህደት ይጨምራል፡፡ በዚህም የተነሳ የነዳጁን የመቀጣጠል ኃይል ይጨምራል፣ የጋዝ ልቀትን ይቀንሳል፣ የሞተሩን አከዋወን እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡
በዚህም ሂደት የነዳጅ ፍጆታ ከ10-12 በመቶኛ፣ የበካይ ጋዝ ልቀት 80 በመቶ እንዲቀንስ የሚያደርግ ሲሆን ሞተሩ የበለጠ ኃይልና የተሻለ ሕይወት እንደሚኖረውና የእድሳት ወጪው አነስተኛ እንደሆነ አቶ ዮሐንስ ጠቅሰው፣ በዓለም ላይ 10 ዩኒቨርሲቲዎች፣ 7 የመንግሥት ተቋማት፣ 8 የግል ላቦራቶሪዎች፣ 25 ትላልቅ የበረራ ድርጅቶችና 12 ትላልቅ የትራንስፖርት ኩባንያዎች ስለ መሳሪያው ምስክርነት መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሱፐርቴክ አንዴ ነዳጅ መያዣው ውስጥ ከተንጠለጠለ ለ5 ዓመታት እንደሚያገለግልና ወጪውም አነስተኛና ኪስ የማይጎዳ መሆኑን የጠቀሱት የሱፐርቴክ አስመጪና የኢዙኬም ትሬዲንግ  ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ  አብዱልአዚዝ  ከማል ዋጋው ከ25-100 ዮሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መሳሪያው በእርሻ ትራክተሮች፣ ኧርዝ ሙቨር በሚባሉት ዶዘሮችና ቡልዶዘሮች፣ በቤት አውቶሞቢሎች፣ በመካከለኛና ከፍተኛ የጭነት መኪኖች፣ በነዳጅ በሚሠሩ ጀነሬተሮቸ ነዳጅ መያዣ ታንከሮች ውስጥ ተንጠልጥሎ አገልግሎት ይሰጣል። መሳሪያው ጣሊያንን፣ ፈረንሳይን፣ ጀርመንን፣ እንግሊዝን፣ ሩሲያን፣ ሉቴንያን፣ ላቲቪያን፣ ዩክሬንን፣ ሮማንያን፣ ቻይናን፣ ሞንጎሊያን፣ ቪየትናምን፣ ሶሪያን፣ ኢራንን፣ እስራኤልን፣ ግብፅን፣ ብራዚልን፣ ሜክሲኮን፣ ቺሊን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ30 በሚበልጡ አገሮች ሥራ ላይ መዋሉ ታውቋል፡፡

Read 1063 times