Saturday, 10 March 2012 13:04

ምን ዓይነት ዘይት ይጠቀማሉ? የተጣራ ወይስ ያልተጣራ?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

በሚገባ የተጣራ ዘይት የምንም ነገር ሽታ የለውም …

ያልተጣራ ዘይት መጥበሻ ላይ ሲደረግ ይኩረፈረፋል

የሁዳዴ ፆም ከተጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ የፆም ወቅት እጅግ ተፈላጊ ከሆኑ የምግብ ምርቶች ዘይት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡ እንደየደረጃቸው ዋጋቸው የሚለያዩ የዘይት አይነቶች በከተማችን በስፋት አሉ፡፡ በየመንደሩ ከሚገኙ የዘይት መጭመቂያ ቤቶች ከሚመረቱ ዘይቶች አንስቶ፣ በፋብሪካ ደረጃ ተመርተውና በሚገባ ተጣርተው ለገበያ እስከሚቀርቡ ዘይቶች ድረስ ሁሉም ገበያውን አጥለቅልቀውታል፡የመርጋት ባህርይ ያላቸውና ከማሌዥያና ከሌሎች አገራት የሚመጡት የፓልም ዘይቶችም በስፋት ገበያው ውስጥ ይገኛሉ፡፡

አብዛኛው ህብረተሰብ የቀረቡለት የዘይት ዓይነቶች የመግዛት አቅሙን ያገናዘቡ መሆን አለመሆናቸውን ከማረጋገጥ ውጭ የጥራት ደረጃቸውና ንፅህናቸው እምብዛም የሚያሣስቡት አይመስልም፡ የደረጃዎች መዳቢና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት በገበያ ውስጥ ያሉ ዘይቶችን ጥራት የመቆጣጠርና ደረጃቸውን ያልጠበቁትን ምርቶች እንዲወገዱ የማድረግ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የችግሩ አሳሳቢነት ግን አሁንም ድረስ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በየመንደሩ በሚገኙ የዘይት መጭመቂያዎች እየተጨመቁ ለተጠቃሚው የሚደርሱ ዘይቶች የጥራት ደረጃ ጉዳይ ቸል ሊባል የሚገባው አይደለም፡፡ በአነስተኛ ካፒታል፣ በየመንደሩ የተቋቋሙ የዘይት መጭመቂያ ድርጅቶች፤ የማጣራት ሥራውን ለማከናወን የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅ በመሆኑ የማጣራት ሂደቱን ያላጠናቀቀና ደረጃውን ያልጠበቀ ዘይት ለተጠቃሚው እንደሚያሰራጩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት መ/ቤቶች የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆን ተግባር ላይ የተሰማራ አንድ የዘይት መጭመቂያና ማጣሪያ ፋብሪካ መኖሩን ሰማንና ወደዛው አመራን፡፡ አዲስ ሞጆ የምግብ ዘይት መጭመቂያና ማጣራት ፋብሪካ ይባላል፡፡ ከዛሬ አራት አመት በፊት ከመንግስት ድርጅትነት ወደ ግል ይዞታነት የተዛወረው የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ፤ በሞጆ ከተማ የሚገኝ ሲሆን የዘይት ማጣሪያው ደግሞ እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ይገኛል፡፡

የዚህ ፋብሪካ 70 በመቶ ባለድርሻ “አሚበራ እርሻ ልማት” የተባለና በጥጥ ምርቱ የሚታወቅ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከጥጥ እርሻ የሚያመርተውን የጥጥ ፍሬ ወደ ዘይትነት በመቀየር ለገበያ ለማቅረብ ጥምረት እንዲፈጥር ታስቦ የተቋቋመ ቢሆንም፣ የፋብሪካው አቅም ከፍተኛ መሆን ወደ ሌሎች ሥራዎች ፊቱን እንዲያዞር አስገድደውታል፡፡ በዚህ ምክንያትም በከተማው ውስጥ በስፋት ተሰራጭተው የሚገኙትንና የማጣራት ሂደታቸውን ሣያጠናቅቁ ለተጠቃሚው የሚደርሱትን የዘይት ምርቶች እየሰበሰበ በማጣራትና ለሰውነት ጐጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በማስወገድ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የዘይት ምርቶች ለገበያ የማቅረብ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ በሽር ስለ ፋብሪካው ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች ሲናገሩ፤  “ፋብሪካው በዋናነት የጥጥ ፍሬን በግብአትነት የሚጠቀም ቢሆንም የኑግ፣ የተልባ፣ የሱፍና የጐመንዘር ዘይቶችንም እየጨመቀና እያጣራ ለተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡ የፋብሪካው የማጣራት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑና በራሱ ፋብሪካ ብቻ የሚጨመቀውን የዘይት ምርት በማጣራት ሥራ ላይ ተወስኖ መቅረት ስለማይገባው፣ በከተማው ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙና ዘይት ከሚጨምቁ ድርጅቶች የተጨመቀውን ዘይት እየሰበሰበ፣ የጥራት ደረጃው ከፍተኛ በሆነ ቴክኖሎጂ እንዲጣሩ በማድረግ ለተጠቃሚው ያደርሳል” ብለዋል፡፡ ፋብሪካው የሚሰጠው አገልግሎትም በደረጃዎች መዳቢና በአለም አቀፍ የጥራት ቁጥጥር ISO የብቃት ማረጋገጫ እንደተሰጠው ገልፀውልናል፡፡

በፋብሪካ የማጣራት ሂደቱን ያላጠናቀቀ ዘይት የሚያቀርቡ ከሃያ በላይ ድርጅቶች በመዲናዋ እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ካሊድ፤ በእነዚህ ድርጅቶች ስር የተደራጁ አነስተኛ የዘይት መጭመቂያዎችም በብዛት እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ እስከአሁን ድረስም፡-

29 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የጥጥ ፍሬ

24 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የኑግ ፍሬ

4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የጐመን ዘርግ

1.2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የሱፍ ዘይቶችን ከየመጭመቂያ ድርጅቶች እየሰበሰቡ ማጣራታቸውንና ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

በከተማው ውስጥ በተለያዩ አነስተኛ የመጭመቂያ ድርጅቶች እየተጨመቁ ለገበያ የሚቀርቡ ዘይቶች፣ የማጣራት ሂደታቸው ያልተጠናቀቁ መሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ካሊድ፤ ዘይት ተጨመቀ ማለት ፈሳሹ ወጣ ማለት እንጂ ተጣራ ማለት እንዳልሆነ ጠቁመው፤ በተጨመቀው ዘይት ውስጥ የተለያዩ ኬሚካሎች፣ አላስፈላጊ ጣዕሞች፣ ሽታዎችና ለሰውነት አደገኛ የሆኑ ባዕድ ነገሮች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡ “እነዚህን ለጤና ጠንቅ የሆኑ አላስፈላጊ ነገሮችን በጣም ሣይንሳዊ በሆነ መንገድና በጥንቃቄ ልናስወግዳቸው ይገባል” ይላሉ - አቶ ካሊድ፡፡ ያልተጣሩ የዘይት ምርቶች በጤና ላይ የሚያስከትሉትን ችግር አስመልክተው የአዲስ አበባው ፋብሪካ ኦፕሬሽን ዳይሬክተርና የጥራት ቁጥጥር ባለሙያው አቶ አብርሃም ዳኜ  ሲናገሩ፤ ያልተጣሩ ዘይቶች የተለያዩ አሲዶችና ኬሚካሎች በውስጣቸው የሚይዙ ከመሆኑም በላይ በሻጋታ የሚፈጠሩና ጉበትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጐዳ አትላቶክሲን የተባለ ኬሚካል እንዲሁም በከብቶች ንክኪ የሚፈጠር ታይኦክሲን የተባለ አደገኛ ነገሮችን ሊይዙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ለጤና እጅግ አደገኛ የሆኑ ነገሮች፣ በማጣራት ሂደቱ ውስጥ ኒውትራላይዝ፣ ብሊችና፣ ዲዮድራይዝ ማድረግ የተባሉትን ሶስት የማጣራት ሂደቶች አልፈው እስካልሄዱ ድረስ ወደ ሰው አካል ውስጥ በመግባት አደጋ ያደርሳሉ፡፡” ብለዋል፡፡ የቅባት እህሎች በባህርያቸው ተመርተው ከታጨዱ በኋላ የአሲድ መጠናቸው እየጨመረ እንደሚሄድ የተናገሩት ባለሙያው፤ እነዚህ አሲዶች ካልተጣሩና ካልተወገዱ በሰውነት ውስጥ ቃር በመፍጠር የጨጓራ ህመም ስሜትን እንደሚያመጡ ይናገራሉ፡፡ በፀረ አረም ኬሚካሎች ከሚጠቀሙ የእርሻ ሥፍራዎች ከሚሰበሰቡ ምርቶች የሚመረተው ዘይት፣ በዚህ የማጣራት ሂደት እንዲያልፍና ኬሚካሉ እንዲወገድ ሊደረግ ይገባዋልም ብለዋል፡፡ በሚገባ ያልተጣሩ ዘይቶች ለተለያዩ የጤና ችግሮች መዳረጋቸውን የሚስማሙበት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ፊትኢ መሀመድ ዘይቱን ለማቆት የሚጨመሩ የተለያዩ አሲዶችም ችግሩን እንዲባባስ ያደርጉታል ብለዋል፡፡ በተገቢው የማጣራት ሂደት በቅባት እህሎቹ ውስጥ የነበሩት የፀረ ተባይ ኬሚካሎችና የተለያዩ ፈንገሶች እንዲወገዱ ካልተደረገ በጤና ላይ  የሚያስከትሉት ችግር ከፍ ያለ መሆኑን ዶ/ር ፈታኢ አክለው ገልፀዋል፡፡ያልተጣራ ዘይት በመጥበሻ ላይ ሲደረግ የመኩረፍረፍና አረፋ የማውጣት ባህርይ እንዳለው የሚናገሩት አቶ አብርሃም፤ ለዚህም ምክንያቱ በውስጡ ያለው የሙጫ መጠን ከፍተኛ መሆን ነው ይላሉ፡፡ ለመጥበሻነት በሚጠቀሙበት ጊዜም ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታና ጣዕም አይኖረውም የሚሉት ባለሙያው፤ ይኼም የሚሆነው በውስጡ የሚገኘው የአሲድ መጠን ከፍተኛ በመሆኑና የእሣቱን ሙቀት መቆጣጠር ባለመቻሉ የተነሳ ነው ብለዋል፡፡ ሽታውም ያልተጣራ ዘይትን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አብርሃም፤ በሚገባ የተጣራ ዘይት የምንም ነገር ሽታ የለውም ይላሉ፡፡

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት እያመረተ ለገበያ የሚያቀርበውን የተጣራ ዘይት የራሱን የማከፋፈያ ሱቆች ጨምሮ፣ ወደ 60 በሚጠጉ የኢት ፍሩት ሱቆችና በአከፋፋዮች ለተጠቃሚው እያደረሰ ሲሆን የአንድ ሊትር ዘይት ዋጋም 40 ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

Read 3007 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 13:55