Monday, 12 December 2016 12:45

4ኛው ዲፕሎማቲክ ባዛር ዛሬ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 አራተኛው ዲፕሎማቲክ ባዛር ዛሬ ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በተባበሩ መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ (ECA) ይከፈታል፡፡ በባዛሩ የተለያዩ አገር ምግቦች፣ የባህል አልባሳት፣ የስጦታ እቃዎች፣ መጠጦችና ህፃናት የሚዝናኑበት ጥግ መሰናዳቱን አዘጋጆች ገልፀዋል፡፡
ከ62 አገራት በላይ በሚካፈሉበት ከዚህ ባዛር የሚገኘው ገቢ በእናቶች ልማትና በተጋላጭ ህፃናት ዙሪያ ለሚሰሩ የእርዳታ ድርጅቶ ገቢ ይደረጋል የተባለ ሲሆን ከዚህ በፊት በተካሄዱት ሶስት የዲፕሎማቲክ ባዛሮች የተሰበሰቡ ገቢዎች በትግራይና በኦሞ ለሚገኙ በእናቶችና ህፃናት ላይ የሚሰሩ 26 ፕሮጀክቶች ድጋፍ መዋሉም ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ከባዛሩ 3.9 ሚ. ብር የተገኘ ሲሆን ከዛሬው ባዛር 4 ሚ. ብር እንደሚጠበቅም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ ወደ ባዛሩ ለመግባት ለአዋቂዎች 50 ብር፣ ለህፃናት ደግሞ 10 ብር እንደሚከፈል ተገልጿል፡፡
ባዛሩን ሄኒከን ቢራ፣ አዲስ ኢንተርናሽናል ካተሪንግ፣ ኖርዲክ ሜዲካሌ ኬር፣ ካፒታል ሆቴል፣ ማሪዮት ሆቴል፣ ኬንያ አየር መንገድ፣ ራዲሰን ብሉ ሆቴል፣ ራማዳ ሆቴልና ገልፍ አየር መንገድ ስፖንሰር እንዳደረጉትም ታውቋል፡፡

Read 1122 times