Monday, 12 December 2016 12:47

ጡት ማጥባት የግል ውሳኔ ነው

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(12 votes)

 • ጡት ማጥባት ለልጅዎ ምን ይጠቅማል?
      • ጡት ማጥባት ለእናትየውስ ምን ይጠቅማል?
      • ለልጄ የሚበቃ ወተት ይኖረኛልን?
      • ልጄን በምን አቅጣጫ ይዤ ማጥበት ይኖርብኛል?
      • ጡት ለማጥባት አስቀድሜ እንዴት መዘጋጀት አለብኝ?

      ለዚህ እትም ከላይ ያነበባችሁን ጠቀሜታ ያላቸው አርእስቶች መርጠናል።
ጡት ማጥባት የግል ውሳኔ ነው የሚለው አርእስት የተወሰደው ቁምነገሮቹን ካገኘንበት ዌብ ሜዲካል ከተሰኘው ድረገጽ ነው። ጡት ማጥባት የማንኛዋም እናት እንዲሁም ቤተሰብ ምርጫ ቢሆንም ማጥባት ግን ግዴታ ተደርጎ መወሰድ አለበት። አለምአቀፍ የጤና ተቋማትም ይህንኑ አበክረው ይመክራሉ። በጽሁፉ ልጁ እየተባለ የተጠቀሰው ልጅትዋ ተዘንግታ ሳይሆን ለሁለቱም እንዲያገለግል አንባቢን ይቅርታ እንጠይቃለን።
ጡት መጥባት ለልጁ ትዋ የሚሰጠው ጥቅም ምንድነው?
የእናት ጡት ወተት አስፈላጊ የሆነና የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ያለው ነው። በትክክለኛው መንገድ የተዋሀዱ ቫይታሚኖች ፣ፕሮቲን እና ስብ የተካተተበት ሲሆን ሌሎችም ልጅ እንዲያድግ የሚያግዙ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው።
ጡት የሚጠቡ ልጆች ከእናታቸው ጋር በመቀራረብና ቆዳ ለቆዳ የሰውነት ንክኪ እንዲሁም በአይን በመተያየት ምክንያት ቅርበትን ስለሚፈጥሩ ልጆቹ ደህንነት እንዲሰማቸው ያደርጋል።
የጡት ወተት ከህጻኑ ንዋ ሰውነት ጋር በቀላሉ የሚዋሃድ ወይንም የሚፈጭ ነው።
የህጻኑ ንዋ ሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም እንዲኖረው ያደርጋል። ባክሪያና ቫይረስ የመሳሰሉትን ይከላከላል።
ለ6ወር ካለምንም ተጨማሪ ምግብ የእናት ጡት ወተት የጠቡ ህጻናት የጆሮ ኢንፌክሽን፣ የመተንፈሻ አካል ሕመም ፣የተቅማጥ በሽታ የመሳሰሉት ችግሮች አይገጥማቸውም።
ጡት የሚጠቡ ልጆች ጠንካራና ክብደታቸውም ተመጣጣኝ ይሆናል።
ጡት መጥባት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ፣የስኩዋር ሕመም እንዲሁም ለካንሰር ተጋላጭ እንዳይሆኑ ይረዳል።
ጡት ማጥባት ለእናትየው የሚሰጠው ጥቅም ይኖራልን?
ሕጻናቱ ጡት በመጥባታቸው ምክንያት ከሚያገኙት ጥቅም በተጨማሪ እናቶቹም ጡት በማጥባታቸው ምክንያት የሚያገኙት ጥቅም መኖሩን ድረገጹ እንደሚከተለው ዘርዝሮአል።
አንዲት እናት ልጅዋን ጡት የምታጠባ ከሆነ በሰውነትዋ ውስጥ የሚገኘው ካሎሪ ስለሚቃጠል በእርግዝና ምክንያት የተከሰተ ውፍረትን በቀላሉ ማስወገድ ትችላለች።
ጡት ማጥባት ሆርሞን ቄቦሽቄሰሽቃ የተባለ ቅመም በሰውነት ውስጥ ስለሚለቅ ማህጸን ከእርግዝና በፊት ወደነበረበት ቦታ ወይንም ቅርጽ እንዲመለስ ይረዳዋል።
ጡት ማጥባት የጡት ካንሰርና የማህጸን ካንሰር እንዳይከሰት ይረዳል።
ጡት የምታጠባ እናት ጊዜዋንና ኢኮኖሚዋን እንዳይባክን ታደርጋለች። ምክንያቱም የወተት እና ተጨማሪ ምግቦች ግዢ እና የጡጦ እና ሌሎች የምግብ እቃዎችን መቀቀል የመሳሰሉት ስራዎች አይኖሩባትም።
ጡት የምታጠባ እናት ልጅዋን የምታገኝበት በቂ ጊዜ ስለሚኖራት ዘና ማለትና መደሰት ትችላለች።
ጡት ለማጥባት ጡ በቂ ወተት ይኖረዋልን?
ብዙ እናቶች ጡ ወተት የለውም ሲሉ ይሰማሉ። በዚህም ምክንያት ልጆች እንዳይራቡና እንዳይጎዱ በማሰብ ትክክለኛ ወዳልሆነው አቅጣጫ ሲሔዱ ይስተዋላሉ። እንደባለሙ ያዎቹ መረጃ ጡ ወተት የለውም በሚል ተጨማሪ ምግብን ፣ወተትን ፣ውሀንና ሌሎች ፈሳሾችን መስጠት ትክክለኛው መንገድ አይደለም፡ :
ልጅ እንደተወለደ የሚገኘው የመጀመሪያው ወተት እንገር ይባላል። እንገር ብጫ እና ወፍራም ወተት ነው። ይህ ወተት ለተወለዱት ልጆች እጅግ ጠቃሚ ንጥረ ነገርን የያዘ ነው። እንገር የሕጻኑ ንዋ ሰውነት ምግብን ተቀብሎ መፍጨት እንዲችል የሚያጠነክረውና የሚያዘጋጀው ስለሆነ ጠቃሚ ወተት ነው ።
የእናት ጡት ወተት መጠን የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰውም እንደሕጻነናቱ አጠባብ ነው። ሕጻናት በትክክል እና እስኪጠግቡ በበቂ የሚጠቡ ከሆነ ወተቱም በዚያው ልክ ይመረታል።
ሕጻን ከተወለደ እስከ 6 ወር ድረስ ጡት ብቻ መጥባት የሚገባው ሲሆን ከ6 ወር በሁዋላ ግን ተጨማሪ ምግቦች ያስፈልጋሉ። ቢሆንም ግን የእናት ጡት ወተት እስከተቻለ ድረስ መቋረጥ የለበትም።
ሕጻን ጡት እንዲይዝ ለማድረግ ምን ማድረግ አለብኝ?
አብዛኛዎቹ የእናቶችና የህጻናት ሕክምና ተቋማት በተለይም የመንግስት የሆኑት እናቶችከመው ለዳቸው በፊት ማለትም በእርግዝና ክትትል ወቅት ስለሚወለዱ ሕጻናት ጡት አጠባብ እና አያያዝ የተለያዩ መረጃዎችን ይሰጡአቸዋል። እናቶች ከሚሰጣቸው መረጃ በመነሳት ለሚወል ዱት ልጅ እንክብካቤ ያደርጋሉ ቢባልም አንዳንድ ጊዜ ግን ስህተት ይስተዋላል።
በመጀመሪያ ልጁ በእናትየው ክርን አንገቱ ወደጡት ዞሮ እና ምቹ በሆነ ሁኔታ መታቀፍ አለበት።
በሌላኛው እጅ የጡትን ጫፍ በመያዝ የልጁን የታችኛውን ከንፈር በማስነካትና አፉን እንዲከፍት በማድረግ ጡቱን ወደአፉ ማስገባት፣
የልጁን አንገት ወደላይ በመደገፍ አፉ ከጡት ጫፍ ጋር በደንብ እንዲገናኝ በማድረግ የጡት ጫፉ ወደልጁ አፍ መሀል እንዲገባ ማድረግ፣
ሕጻኑ የጡት ጫፉን እና በጫፉ ዙሪያ ያለውን ጠቆር ያለ የጡት ክፍል ወደአፉ በማስገባት መጥባት ሲጀምር በትእግስት በመቆጣጠር እስኪጠግብ ማጥባት ይገባል።
ጡት ለማጥባት አስቀድሜ እንዴት መዘጋጀት አለብኝ?
አንዲት እናት ልጅዋን ጡት ለማጥባት የተወሰነ ጊዜ እና ቦታ ማዘጋጀት ይገባታል። አንዳንድ ጊዜ እናቶች ስራ ላይ ሆነው ወይንም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ጡት ለልጃቸው በሚሰጡበት ወቅት ልጁ በትክክል ተመችቶት መጥባቱ ያጠራጥራል።
ዌብ ሜድ የተባለው የህክምና ድረገጽ እንዳስነበበው ጡት ለማጥባት ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። እነርሱም ፡- (ABC) A= Awareness (ንቃተ ሕሊና) B= Be patient (ትእግስት ) C=comfort (ምቾት ) ናቸው።
A= Awareness --- (ንቃተ ሕሊና )
ጨቅላ ሕጻናት በሚርባቸው ጊዜ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያሉ። የተራቡ ጨቅላዎች እጃቸውን ወደአፋቸው በማድረግ አፋቸውን እና አፍንጫቸውን ያሻሻሉ ። ስለዚህ ከማልቀሳቸው በፊት የሚያሳዩትን ምልክት ተረድቶ ጡት ለመስጠት የሚያስችል ንቃተ ሕሊና እናቶች ሊኖራቸው ይገባል።
B= Be patient ---(ትእግስት )
ጨቅላው ጡት በሚጠባበት ጊዜ እስኪጠግብ ድረስ ታግሶ ጡቱን መስጠት እንጂ ማስቸኮል ወይንም እንደበቃው ምልክት ሳያሳይ ጡቱን መንጠቅ አይገባም። ሕጻኑ ከ10-20 ደቂቃ ድረስ ጠብቶ ሊጨርስ ይችላል። በተወለደ በመጀመሪያው ሳምንት በ24 ሰአት ጊዜ ውስጥ ከ8-12 ጊዜ ማጥባት ያስፈልጋል።
C=comfort (ምቾት )
ምቾት መሰረታዊ ነገር ነው። እናት ጡት ለማጥባት ስትዘጋጅ በሚመቻት መንገድ መቀመጥ ይኖርባታል። እናትየው ጡት ከመስጠትዋ በፊት ልጅን ያቀፈችበትን ክንድ በትራስ መደገፍ፣ አንገትና ጭንቅላትዋ በሚመች መልኩ ደገፍ ማለት፣ እግርዋ በሚመች መንገድ ማረፍ መቻ ሉን ማረጋገጥ አለባት። እናትየው አቀማመጥዋ ከተመቻት የጡት ወተቱ ለልጁ በደንብ ይፈሳል።
(ምንጭ web med medical reference)

Read 8781 times