Sunday, 18 December 2016 00:00

ኦፌኮ ህልውናው አደጋ ላይ መሆኑን ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ግማሽ ያህል አመራርና አባላቱ እንደታሰሩበት አስታውቋል

የፓርቲውን ሊቀመንበርና ም/ሊቀመንበZ ጨምሮ አብዛኞቹን ዋና አመራሮች በእስር ማጣቱን የጠቆመው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኢፌኮ)፤ ህልውናዬ አደጋ ላይ ወድቋል አጠያያቂ ሆኗል ብሏል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀደም ብሎ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባላት የሆኑትን፡- አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጉርሜሣ አያኖ፣ አቶ ደረጀ መርጋ፣ አቶ አዲስ ቡላላ እና አቶ ደስታ ዲንቃን በእስር ማጣቱን ያስታወቀው ፓርቲው፤ አሁን ደግሞ ሊቀመንበሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና እንደታሰሩበት አስታውሶ ሁኔታው የፓርቲውን ቀጣይነት አጠያያቂ አድርጎታል ብሏል። ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከዋናዎቹ አመራሮች በተጨማሪ የተለያዩ ዞኖች የፓርቲው አደረጃጀት አመራሮች
መታሰራቸውን የጠቀሡት የኦፌኮ ም/ሊ ቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ “በአሁኑ ወቅት የፓርቲያችን እንቅስቃሴ በእጅጉ ተገድቦ፣ ከፍተኛ ጫና እየደረሰብን ነው” ሲሉ አማረዋል፡፡
‹‹አሁን ኦፌኮ አለ ማለት አይቻልም›› ያሉት አቶ ሙላቱ፤ ከአመራሮቹ በተጨማሪ ከግማሽ በላይ አባላቱንም በተመሳሳይ መንገድ ማጣቱን ይናገራሉ። በአሁን ወቅት ከከፍተኛ አመራሮቹ በፓርቲው የዕለት ተዕለት ስራ ላይ የሚገኙት እሳቸውን ጨምሮ አቶ ገብሩ ገ/ማርያምና አቶ ጥሩነህ ገሞታ ብቻ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለነው አመራሮችም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን›› ብለዋል - አቶ ሙላቱ፡፡ፓርቲያቸው የሃገሪቱን ህግ አክብሮ በሠላማዊ መንገድ እንሚንቀሳቀስና ከዚህ መርህ ያፈነገጡ ፀረ ዲሞክራሲያዊ ቡድኖችን
አጥብቆ እንደሚቃወም የጠቆሙት ሌላው የፓርቲው አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ ‹‹ባለፉት ጊዜያት ስለ ኦፌኮ በርካታ መራራ ቃላት ሲነገሩ ከርመዋል” ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረንስ (ኦፌኮ)፤ የዶ/ር መረራ ጉዲናን መታሠር እንደሚቃወም ሰሞኑን ባወጣው የአቋም መግለጫ አስታውቋል፡፡
የህዝቡን ትክክለኛ ጥያቄ ተገን በማድረግ ወንጀል የፈፀሙና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ የተጠረጠሩ የገዥው ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ ህግ ለማስከበር ሲባል በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ  በተደጋጋሚ የገለፀው መንግስት በበኩሉ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህግን
አክብረው በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ላይ ምንም አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማይኖረው ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ኦፌኮ የሁለት ፓርቲዎች ውህደት የፈጠረው ፓርቲ ሲሆን በዶ/ር መረራ ጉዲና ይመራ የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ (ኦህኮ) እና በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ የነበረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) በመዋሃድ የመሰረቱት የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡




Read 1332 times