Sunday, 18 December 2016 00:00

ግልገል ጊቤ 3 ኃይል ማመንጫ ዛሬ ይመረቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

ግንባታው ከ10 ዓመት በፊት የተጀመረው የግልገል ግቤ III ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት እንደሚመረቅ ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ በተለይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፤ የግልገል ጊቤ III ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 450 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በደቡብ ክልል በወላይታና ዳውሮ ዞኖች ድንበር ላይ የተገነባው ኃይል ማመንጫ፤ የግድቡ ቁመት 246 ሜትር፣ ውሃ የመያዝ አቅሙ 14 ሚሊዮን 700 ሺህ ኪዩቢክ ሚትር፣ አጠቃላይ ኃይል የማመንጨት አቅሙ 1870 ሜጋ ዋት ሲሆን በዓመት በአማካይ 6500 ሜ.ዋ ኃይል እንደሚያመነጭ ታውቋል፡፡
የጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎና ከቻይናው ዶንግ ፋንግ በጋራ ያከናወኑት ፕሮጀክት 1.5 ቢሊዮን ዩሮ የወጣበት ሲሆን የገንዘቡ 60 በመቶ ከቻይናው አይሲቢሲ ባንክ የተገኘ ነው ተብሏል፡፡ ቀሪው 40 በመቶው በኢትዮጵያ መንግሥት መሸፈኑ ታውቋል። ፕሮጀክቱ ለ7 ሺ ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን 700 የውጭ አገር ዜጎችም ተሳትፈውበታል፡፡
ከጊቤ III ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ወላይታ ሶዶ - አዲስ አበባ 401 ኪ.ሜ ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ የተከናወነ ሲሆን፣ ባለ 400 ኪ.ቮ የወላይታ ሶዶና የአቃቂ II አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችም ተገንብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት ዓመታት ባደረጋቸው ጥረቶች፣ ከ20 በላይ የውሃና የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች የገነባ ሲሆን በዕለቱ የሚመረቀውን ግልገል ጊቤ III ጨምሮ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ከ4,260 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዳላት የጠቀሱት አቶ ምስክር፤ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ከውሃ ኃይል 50 ሺህ ሜ.ዋ፣ ከንፋስ 1.3 ሚ.ሜ.ዋ፣ ከእንፋሎት ከ10 ሺህ ሜ.ዋ በላይ ታዳሽና አረንጓዴ እምቅ አቅም እንዳላት አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡
ግንባታው 54 በመቶ የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሁለት ዩኒቶች በሚይዙት የውሃ መጠን ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ 254 ሜ.ዋ እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው ገናሌ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ 88.7 በመቶ መከናወኑን፣ 50 ሜ.ዋ ኃይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ 87.5 በመቶ መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
ዛሬ የሚመረቀው የግልገል ጊቤ III ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ በ1998 ሐምሌ ወር ላይ ግንባታውን የጀመረው፡፡  

Read 3896 times