Sunday, 18 December 2016 00:00

የፔፕሲ የሃዋሳ ቅርንጫፍ ፋብሪካ ታሸገ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(7 votes)

- በምርት ጥራቱ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው ተብሏል
- ‹‹ፋብሪካው የታሸገው ለእድሣት ነው›› የፔፕሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ

የሞሃ ለስላሣ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክስዮን ማህበር የሃዋሳ ቅርንጫፍ ፋብሪካ ከምርት ጥራት ጋር በተያያዘ ለምርመራ መታሸጉ ተጠቁሟል፡፡
የኩባንያው ሃዋሣ ቅርንጫፍ ፋብሪካ ውስጥ በተመረቱ  ምርቶች ላይ ታዩ የተባሉ የጥራት ጉድለቶችን ለመመርመርና የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ ፋብሪካው እንዲታሸግና ምርቶቹ እንዲታገዱ መደረጉ ታውቋል፡፡
የሞሃ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው ቢርቦን ስለ ፋብሪካው መታሸግ ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹ፋብሪካው የታሸገው ቴክኒካል እድሳት ለማድረግ ነው›› ብለዋል፡፡ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ዋና ሥራ አስፈፃሚው፡፡
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የኮርፖሬሽን ኮሙኒኬሽንና ፕሮሞሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ተክኤ ብርሃነ፤ ፋብሪካው የታሸገበትን ምክንያትን በተመለከተ ተጠይቀው፤ መ/ቤታችው በተለያዩ ፋብሪካዎችና አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች በዓመት አራት ጊዜ መደበኛ ፍተሻዎችንና ምዘናዎችን እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ከታዩም ድንገተኛ ፍተሻ ለማድረግ ድርጅቱ እንዲዘጋና ምርቶቹ እንዲታሸጉ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በዚህ ፋብሪካ ላይም የተደረገው ተመሳሳይ ነገር መሆኑ ጠቁመው፡፡  የጥራት ፍተሻና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነና ውጤቱ ገና አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ከተደረገው ምርመራ የተገኘውን ውጤት አስመልክቶ አቶ ተክኤ ሲያብራሩ፤ ‹‹በፋብሪካው ላይ የተደረጉ የጥራት ፍተሻዎችንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ መረጃ ለመስጠት ጊዜው ገና ነው፤ የምርመራ ውጤቱ አልተጠናቀቀም›› ‹‹በፋብሪካው የተመረቱ የለስላሣ መጠጦች በከተማዋ ገበያም ሆነ ለአገር አቀፉ ሽያጭ  እንዳይወጣ ታግዶ ፋብሪካው እንዲታሸግ ተደርጓል›› ብለዋል፡፡

Read 2591 times