Sunday, 18 December 2016 00:00

የዩኒቨርስቲ አመራሮች የሚሾሙበት አዲስ መስፈርት ተዘጋጀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

የትምህርት ሚኒስቴር ወትሮ የነበረውን የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮች አሿሿምን ይለወጣል ያለውን አዲስ መስፈርት ያዘጋጀ ሲሆን በተዘጋጀው መስፈርት ረቂቅ ላይ ከትናንት በስቲያ በካፒታል ሆቴል ውይይት ተደርጓል፡፡
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮች ምደባ ላይ ከዚህ በፊት በርካታ ጉድለቶች እንዳሉ የሚጠቁመው ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ሰነድ በተለይ የአመራርነት ብቃትና ክህሎት ያላቸውን አስተዳደሮች በመመደብ በኩል ክፍተት እንደነበረ ጠቅሶ በቀጣይ ለሚያከናውኑት እያንዳንዱ ተግባር ሃላፊነት የሚወስዱ፣ የትምህርት ነፃነትን የሚያስጠብቁና የትምህርት ፖሊሲውን በጥራት የሚያስፈፅሙ አመራሮች አዲስ በተዘጋጀው መስፈርት መሠረት ተመልምለው እንደሚሾሙ በረቂቅ ሰነዱ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ በኋላ በዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት የሚሾሙ አመራሮች ዋነኛ መመዘኛ በትምህርት ያላቸው ውጤት እና የስራ ልምድ መሆኑን የሚጠቅሰው ሰነዱ በሚያስገቧቸው የትምሀርትና የስራ ልምድ ማስረጃዎች መሰረት ሁሉም በእኩል እንደማንኛውም ስራ ተወዳድረው ባስመዘገቡት ውጤት ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ጠ/ሚኒስትሩ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት በቀጥታ ይሾሙ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነትና ለም/ፕሬዚዳንትነት እንዲሁም ለሌሎች ከፍተኛ አመራርነት የሚወዳደሩ ግለሰቦች ቢያንስ የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪ ያላቸውና ከ4 ዓመት በላይ የስራ ልምድ ያላቸውና የምርምር ውጤቶቻቸው በተለያዩ ጆርናሎች ላይ የታተመላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ የሚጠቅመው ከተዘረዘሩት መስፈርቶች መካከል ይገኝበታል፡፡
አመልካቾች የሚያቀርቧቸውን ማስረጃዎች የሚመረምር ኮሚቴ በትምህርት ሚንስቴር አማካሪነት በዩኒቨርሲቲ ቦርድ እንዲቋቋም ተደርጎ በተዘጋጀው መስፈርት መሰረት እጩዎችን መርጦ ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ በማቅረብ እንዲሾመው ያደርጋል ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት፣ ም/ፕሬዚዳነትነት፣ ዳይሬክተር፣ ዲን እና የዲፓርትመንት ኃላፊ ይከፈል የነበረው ደሞዝ ቅዝተኛ፣ የማይመጥንና ሳቢ ያልሆነ መሆኑን የጠቀሰው ሰነዱ የተሻሻለውን መጠን ባይጠቅስም በቂና ማራኪ ደሞዝና ጥቅማጥቅም እንዲኖር ያደርጋል ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሌሎች በየደረጃው ያሉ አመራሮች መኖሪያ ቤትት የተገደበም ቢሆን የቀረጥ ነፃ አገልግሎት፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ያገኛሉ ተብሏል፡፡


Read 6164 times