Sunday, 18 December 2016 00:00

ዓለማቀፍ የካቶሊክ ቤ/ክ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ከ300 በላይ የዓለም ጳጳሳት ይሳተፉበታል
   ከ300 በላይ የካቶሊክ ጳጳሳትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና የምዕመናን ተወካዮች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀውን 19ኛውን የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መመረጧ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ፅ/ቤት ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ ሀገሪቱ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ ስትመረጥ የአሁኑ የመጀመሪያዋ ሲሆን ጉባኤው በመጪው ዓመት ሐምሌ 2010 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማላዊና  ዛምቢያ ሙሉ አባል እንዲሁም ጅቡቲና ሶማሊያ ተባባሪ አባላት የሆኑበት የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት፤ በቅርቡ በማላዊ ባካሄደው 18ኛው ጉባኤ ቀጣዩን የህብረቱን ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ ከመምረጡ በተጨማሪ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳስ ዘካቶሊካውያን ህብረቱን ለ4 ዓመታት በሊቀመንበርነት እንዲመሩ መርጧቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው አለማቀፍ ጉባኤ፤ በልዩ ልዩ አለማቀፍ የካቶሊክ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን የሚያገኝ ሲሆን የሃገሪቱን ገፅታ ለማስተዋወቅ ጠቃሚ አጋጣሚ ነው ተብሏል።
‹‹ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲዘጋጅ ኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ክርስቲያን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ያላትን የሰላምና የመከባበር ባህል ለማስተዋወቅ ትሰራለች›› ያለው መግለጫው፤ የጉባኤው ዝግጅትም ከዛሬ ታህሳስ 8 ቀን አንስቶ መደረግ ይጀምራል፡፡

Read 4462 times