Sunday, 18 December 2016 00:00

ተሃድሶ፣ ግምገማና የሥልጣን ሹም ሽር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶና ግምገማ እንዲሁም ሹም ሽር ቀጥሏል፡፡ በፊት አውራሪነት የኦሮሚያ፣ከዚያም የአማራ፣በቅርቡ ደግሞ የትግራይ ክልል ሹም ሽር አድርገው አዳዲስ ካቢኔዎች መስርተዋል፡፡ የህዝብ ተቃውሞና ብሶትን መነሻ አድርገው የፌደራሉን ጨምሮ በየክልሉ የተቋቋሙት ካቢኔዎች መለያቸው ምሁራንን በብዛት ማሰባሰባቸው ነው፡፡ በተለይ የትግራይ ክልል፣ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዶክተር ምሁራንን (PHD) በካቢኔው በማካተት ቀዳሚው ሳይሆን አይቀርም፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ጥር ወር አዲስ የካቢኔ ተሹዋሚዎችን ለፓርላማ አቅርበው ባጸደቁበት ወቅት፤ሹመቱ ከወትሮው በተለየ ከፓርቲ ታማኝነት ይልቅ ለትምህርት ዝግጅትና ብቃት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተከናወነ መሆኑን ጠቁመው አዲሶቹ ሚኒስትሮች ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ነበር፡፡ የአገሪቱ ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የስልጣን ሹም ሽሩ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ጋር አይገናኝም ባይ ናቸው፡፡ እንዴት? ለምን?  
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤በኢህአዴግ ተሃድሶ፣ግምገማና ሹም ሽር ዙሪያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን አጠናቅሮታል፡፡  ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡ የተለያዩ ሃሳቦች ማንሸራሸራችንን እንቀጥላለን፡፡  
                     
              “ተሃድሶ ማድረግ ማለት ለህዝብ ውሳኔ መገዛት ነው”
                              አቶ ጥሩነህ ገምታ (የኤፌኮ አመራር)

    ገዥው ፓርቲ ወይም መንግስት ባለስልጣናቱን መቀያየሩ መብቱ ነው፡፡ የራሱ የቤት ስራ ነው፡፡ የውስጠ ፓርቲ ጉዳይ ነው፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም በተመሳሳይ ይቀያይራሉ፡፡ ገዥው ፓርቲም አመራሮቹን ቢቀያይር ምንም ማለት አይደለም። ነገር ግን እስካሁን የህዝብን ጥያቄ አለመመለሱ ወይም ለመመለስ አለመቃረቡ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የህዝብ ጥያቄ የሠብአዊ መብት አከባበር ጥያቄ ነው። የህገ መንግስት መከበር ጥያቄ ነው። የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ጥያቄ ስንል ምርጫ ላይ የህዝብን ድምፅ ማክበር ማለት ነው፡፡
ህዝቡ “እኔ የመረጥኳቸውን መሪዎችና ፓርቲዎች በስልጣን ላይ ልያቸው” ነው ያለው፡፡ ሌላም መሠረታዊ የህዝብ ጥያቄም አለ፡፡ የፓርቲና የመንግስት ጥምርታ ይወገድልኝ ብሏል። ገዥው ፓርቲ በማንኛውም የመንግስት መዋቅር ውስጥ ይገባል፡፡ ለምሳሌ በፍትህ አካላት፤ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ ፍ/ቤቶች ሁሉ ለምን ጣልቃ ይገባል ነው - ጥያቄው። ህዝብ እነዚህ አካላት በሙሉ ነፃ እንዲሆኑለት ይፈልጋል፡፡ ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚው ህግ አስፈፃሚው ተለያይተው፣ ድንበር ኖሯቸው፣ በነፃነት መስራት ይኖርባቸዋል ነው፡፡ ህግ አስፈፃሚው አካል በሁሉም ቦታ ላይ ገብቶ አዛዥ ናዛዥ መሆን የለበትም፡፡ ገዥው ፓርቲ የመንግስት ሰራተኞችን የራሱ ተገዥዎች ማድረግ የለበትም፡፡ የመንግስት አገልግሎቶችን የሚሠጠው አካል በሙሉ ከፓርቲ ተጽዕኖዎች ነፃ መሆን አለበት፡፡ የማንም ፓርቲ ገባር መሆን የለበትም፡፡ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያ ሰራዊት በገለልተኝነት፣ በህዝብ ውግንና ማገልገል አለባቸው። ከፓርቲ ይልቅ የህዝብን መብትና የህግ የበላይነት የሚያስከብሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡
መንግስት አሁን አደረግኩ የሚለው ጥልቅ ተሃድሶ፣ እነዚህን ሶስት የመንግስት አካላት ነፃ ሆነው እንዲሠሩና እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ነው? ጥያቄው ይሄ ነው፡፡ አዲስ ተተኩ የሚባሉት ሰዎችም ቢሆኑ በፊት ከስር ሆነው ይሠሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ወደ ላይ እንዲመጡ ተደረጉ እንጅ የተለወጠ ነገር የለም። ጥልቅ ተሃድሶ፤ በፖሊሲና በመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ላይ እንዴት ያለ ለውጥ ያመጣል የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ እንደኛ እምነት፣ ችግሩ ያለው ስርአቱና ፖሊሲው ላይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት 25 አመታት በርካታ ተሃድሶ አድርጓል፡፡ ለመሆኑ ለምን ያህል ጊዜ ነው ጥልቅ ተሃድሶ የሚያደርገው? ይሄ መልስ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ዛሬም ስለ ሙስና፣ ስለ መልካም አስተዳደር ችግር ነው የሚነገረው፡፡ ተሃድሶ ማድረግ ማለት እንደኔ ለህዝብ ውሳኔ መገዛት ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን አስሮ፣ ጥልቅ ተሃድሶ እያደረኩ ነው ማለት ተገቢ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ “ከተቃዋሚዎች ጋር እንነጋገራለን”የሚለው ከፌዝ ባለፈ የሚተገበር ከሆነ እሠየው ብለን እንቀበላለን፡፡ ለሠላም ሁሌም በቁርጠኝነት እንቆማለን፡፡ የኦፌኮ አመራሮች፣” በአንድ እግራችሁ ከሠላማዊ ትግሉ ጎን፣ በሌላ እግራችሁ ከአሸባሪ ጎን ትቆማላችሁ” በሚል እንወነጀላለን፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ እኛ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ማንኛውንም ፀረ- ዲሞክራሲያዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እንቃወማለን፡፡ አሸባሪነትም ቢሆን የሚፈለፈለው ዲሞክራሲያዊ ባልሆኑ ሃገሮችና መንግስት ስር ነው እንጂ ዲሞክራሲያዊ በሆኑት ሃገሮች ስር እንዳልሆነ የአለምን ተጨባጭ ሁኔታ አይቶ መረዳት ይቻላል፡፡ የኛ ተቃውሞ ግልፅ ነው፤”የኔ ብቻ” ወይም “እኔ ያልኩት ብቻ” የሚለው ያብቃ የሚል ነው፡፡ በተረፈ ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከሌሎች ጋር ለመነጋገር ሁሌም ዝግጁ ነን፡፡

----------------------------------------------

                           ‹‹ተቃዋሚዎች በነፃነት መንቀሳቀስ አለባቸው››
                                 አቶ አበራ (የሠማያዊ ፓርቲ አመራር)

      መንግስት ከህዝቡ የቀረቡ ጥያቄዎችን ለማስተንፈስ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ዘላቂ ውጤት ያመጣሉ የሚል እምነት የለኝም። ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙት ከስር መሠረታቸው የእርማት እርምጃ ሲወሰድባቸው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጥያቄ ያቀረቡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ለእስር መዳረግም መፍትሄ አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ “ኮማንድ ፖስት” ለሚለው መንግስት ለምን የአማርኛ ቃል እንደማይጠቀም አይገባኝም፡፡
በዚህ የራሱን እርምጃ እየወሰደ ባለበት፣ ”ተሃድሶ” እና “ግምገማ” የሚለውም ግራ አጋቢ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ግምገማው ምንድን ነው? ባለስልጣናቱ ስራቸውን በትክክል አልሠሩም? የህዝቡን ጥያቄ አልመለሱም? ህዝቡ ከነሱ የሚጠብቃቸውን ተግባራት አላከናወኑም? ምንድን ነው የሚገመገሙት? ይሄ አይታወቅም። ግምገማው ውጤት ያመጣል ተብሎ ነው ወይስ እንዲወገዱ የሚፈለጉ ሰዎችን ለማስወገድ ብቻ ነው? የሚለውም አጠያያቂ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በዝግ ጨርሰው ነው የሚቀርቡት፡፡ ይሄ የግልጽነት ጥያቄ ያስነሳል። የተተኩት ሰዎችስ እነማን ናቸው? ስንል ደግሞ፣ እዚያው ያሉ የድርጅቱ አባላት የነበሩ ናቸው፡፡ በተለይ የግምገማ መስፈርቶቹ በግልፅና በዝርዝር ለህዝብ አለመገለጻቸው ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ የተዓማኒነት ችግር ይፈጥራል፡፡  
ሌላው የሃገሪቱን ችግር ለመፍታት “ከተቃዋሚዎች ጋር እንነጋገራለን” የተባለው ከልብ የመነጨና ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት ተቃዋሚዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ፣ እንዲጠነክሩ መደረግ አለበት። የሲቪክ ተቋማት በነፃነት መደራጀትና መቋቋም አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ሚዲያውን መጥቀስ ይቻላል። ከተቃዋሚዎች ጋር ከሚደረገው ውይይት በፊት እነዚህ ተግባራት መቅደም አለባቸው፡፡ ተቃዋሚዎች ከተጠናከሩ በኋላ በሰከነ መንገድ መነጋገር ይቻላል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች ባልተፉበት መነጋገር ውጤት አያመጣም፡፡ መቼም መቶ በመቶ የተመረጠ መንግስት በአጭር ጊዜ እንዲህ ያለ ተቃውሞ ያጋጥመዋል ተብሎ አይጠበቅም። ለዚህ ነው የይስሙላ ምርጫ ይቅር የምንለው፡፡ አሁን ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት አድርጎ፣ነፃና ገለልተኛ ተቋማት አቋቁሞ፣ ምርጫዎች በትክክለኛ ህዝባዊ መሰረት ላይ እንዲፀኑ ማድረግ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

------------------------------------------------

                         ‹‹ሁላችንም ለህዝብ ሲባል አገርን ማስቀደም አለብን››
                              አቶ ተሻለ ሠብሮ (የኢሪፓ ፕሬዚዳንት)

      የኢትዮጵያ ህዝብ ባለብዙ ፈርጅ ችግሮቹ ወይም ህጋዊና ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎቹ በርካታ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል መንግስት ያንን ችግርና ጥያቄ ለመፍታት እየወሰዳቸው ያሉት እርምጃዎች በብዙ መልኩ ለየቅል ናቸው፡፡ አልተገናኙም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ “ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ያድርግልን” አይደለም፤ “አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይታወጅም” አላለም፡፡
ከየትኛውም ለውጥ ፈላጊ ህብረተሰብ እኒህ ጥያቄዎች አልተደመጡም፡፡ ከጥያቄዎቹ መረዳት የምንችለው ጥገናዊ ለውጥ መልስ ሊሆን እንደማይችል ነው፡፡ ህዝቡ “ለውጥ! ለውጥ!” እያለ ነው የጮኸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ህገ መንግስቱ ይከበር ነው፡፡ ሠብአዊ መብቶች ይከበሩ፣ ዲሞክራሲ ይስፈን ነው፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የኑሮ ውድነት ብቻ አይደለም፡፡ በዋናነት የጠየቀው ነፃነትና ዲሞክራሲን ነው፡፡ ቢያንስ በህገ መንግስቱ ላይ ያለው መብት ሳይሸራረፍ ይሰጠኝ ነው ያለው። ስለዚህ የኢህአዴግ ተሃድሶ እንዴት ነው ለህዝቡ ጥያቄዎች መልስ የሚሆነው? ተሃድሶ በፊትም ነበር፤አሁን የተጨመረው ‹‹ጥልቅ›› የሚለው ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ጥልቅ ተሃድሶ ለማን? በእነማን? ለምን? የሚለው መመለስ አለበት። መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ነው ከተባለም እስካሁን ምልክቶች መታየት ነበረባቸው፡፡
አዋጁ 3 ወር ሊሆነው ነው፡፡ ግን ምን ውጤት አመጣ? ምን ተስፋ ተገኘ? በተለይ ተቃዋሚዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ፣ ፕሬሶች እንዲያብቡ በማድረግ ረገድ ምን ተከናወነ? የሚሉት መጠየቅ አለባቸው፡፡ እንደኔ ለነዚህ ጉዳዮች ተስፋ ሰጪ ፍንጮች እስካሁን መታየት ነበረባቸው።  የህዝብ ጥያቄና የመንግስት ምላሽ አልተገናኙም የምለው ከዚህ አንፃር ነው፡፡
ስለ ብሄራዊ መግባባት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ብዙ አሳስቧል፡፡ በዚህ ረገድ እስካሁን የሚጨበጥ ተስፋ መታየት የነበረበት ቢሆንም፣ መንግስት ግን ስሙን እንኳን ለመጥራት ሲያፍር እየታዘብን ነው፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚመነዘሩ ሃሳቦችን ለመቀበል አሁንም ዝግጁ አይደለም። ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲባል ሁላችንም የፓርቲ አጥራችንን ትተን ሃገርን ማስቀደም አለብን፡፡ አንዱ ከአንዱ ጋር  በአልባሌ ጉዳይ መነታረኩ ጥቅም የለውም። ከዋናው የህዝብ ጥያቄ ያዘናጋናል፡፡ ገዥው ፓርቲ መድረክ (ሚዲያ) ይስጠን የምንለው ለሌላ አይደለም፤ ለህዝብ ሃሳባችንን በተገቢው መንገድ ለማድረስ ነው፡፡
የመንግስት ሚዲያዎች ለምንድን ነው ለተቃዋሚዎች ክፍት የማይሆኑት? ምርጫ እስኪመጣ ለምን ይጠበቃል? እኛ ለጊዜው መንግስት የመሆን እድሉን ባለማግኘታችን የሰራነው ሥራ ባይኖርም፣ ወደፊት ልንሠራ ያቀድናቸው፣ብዙ ከኢህአዴግ የተሻሉ ፕሮግራሞች አሉን፡፡ እነሱን በየጊዜው ለህዝብ እንድናሳውቅ ዕድል ሊሰጠን ይገባል፡፡ የት ነው ፕሮግራማችንን የምንሸጠው? ፓርቲዎች እርስ በእርስ ለመከራከርና ከኢህአዴግ የሚበልጡበትን በጎ ጎኖች ለማሳየት መች እድሉን አገኙ? ተቃዋሚዎች ሳይታዩና ሳይመዘኑ፣ በደፈናው አይረቡም የሚለው ድምዳሜ  የሚያስኬድ አይደለም፡፡ አንድም ፓርቲ በሃሳቡ ተቀባይነት በህዝብ ዘንድ ነጥሮ እንዳይወጣ መንግስት ሁሉ ነገራችንን አስሮናል፡፡

-------------------------------------

                           “ተቃዋሚዎች ህዝቡን ወክለው መደራደር አይችሉም”
                              አቶ ስለሺ ፈይሳ (ፖለቲከኛ)

      በኦሮሚያና በአማራ ለተነሱ የህዝብ ተቃውሞዎችና ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አንዱ አማራጭ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አሁን ሀገሪቱ በከፊል በኮማንድ ፖስቱ ስር ነች፡፡ ይሄን ያደረጉት ሀገሪቱን ለማረጋጋትና ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ፋታ ለማግኘት ነው ብለዋል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ፣ “ከህዝቡ የተነሳው ጥያቄ ህጋዊ ነው፤ጥፋቱ የራሳችን ነው” የሚል አይነት አስተያየት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይሄን መርምረን እንታደሳለን፤ ለህዝቡ ጥያቄዎችም መልስ እንሰጣለን ብለው ነበር፡፡ አሁን ግን እሳት የማብረድ ስራ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አካላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንንና አክቲቪስቶችን የማሰር እንቅስቃሴዎችን ስንመለከት፣ መንግስት ስልጣኑን የማስጠበቅ እርምጃ ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል፡፡ የህዝቡንም ጥያቄ መጠምዘዝ መስሎ ይሰማኛል፡፡
ለወደፊት ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይደገሙ በሚያደርግ መልኩ፣ ህዝቡን ሊያረካ የሚችል ዘላቂ መልስ የመስጠት ጥረት ወይም ሙከራ እምብዛም አላስተዋልኩም፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተቃዋሚዎችን እንዲያሸማቅቅ ከማድረግ ይልቅ መንግስት ራሱን ለማረምና ለማሻሻል ከሚመለከታቸው የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ጋር ውይይት መጀመር ነበረበት፡፡ አፋኝ የተባሉ አዋጆችንና መመሪያዎችን እንደገና ተመልክቶና ፈትሾ ማሻሻያ ለማድረግ መንቀሳቀስም ይጠበቅበት ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ ከእነ አካቴው ረስቷቸው ሹም ሽረቱ ላይ ነው ያተኮረው። ታዲያ እንዴት ነው በዚህ ሁኔታ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችለው?
በሌላ በኩል መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እወያያለሁ ማለቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በምን አግባብ፣ በምን ጉዳይ ነው የሚወያየው? የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ ሀገሪቱን ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያበቃት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ አይደለም፡፡ የህዝብ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ የህዝብ ጥያቄ ማንም ፖለቲከኛ ኃላፊነት ለመውሰድ አይችልም፡፡ ለኔ የትኛውም ፖለቲከኛ የህዝብን ጥያቄ ወክሎ የሚደራደርበት ሁኔታ አይታየኝም፡፡ ድርድር ካስፈለገ ፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም፤ የተለያዩ ህብረተሰቡን የሚወክሉ ወገኖችም መሳተፍ አለባቸው፡፡

Read 2425 times