Sunday, 18 December 2016 00:00

“ዛሬስ ከእነሚስቱ ሊናፍቀኝ ነው ወይ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ሀኪሙን…
“ዶክተር አሞኛል፣ እባክህ ነርሷን ላክልኝ…” ይለዋል፡፡
ዶክተሩም… “ልልክልህ አልችልም፣ ኩፍኝ ይዟታል”  
ሰውየውም ደንገጥ ብሎ… “አትለኝም፣ የሚገርመው ነገር እሷን ሴትዮ ስሜያታለሁ። በዚህ አይነት እኔንም ኩፍኝ ይይዘኛል ማለት ነው?” ይላል።
ዶክተሩም፣ “እሱን ካልክማ እኔም ስሜያታለሁ፣” ይላል፡፡
ሰውየውም፣ “ዶክተር እንደዛ ከሆነማ አንተንም ይይዝሀል” ይላል፡፡ “ከሁሉም የሚያሳዝነው ነገር ግን እኔ ነርሷን ከሳምኩ በኋላ ቤት ስገባ ሚስቴንም ስሜያታለሁ፡፡”
ይሄኔ የሁለቱን ንግግር ዝም ብሎ ያዳምጥ የነበረ የሰውየው ጓደኛ ደንገጥ ይልና ምን ቢል ጥሩ ነው… “እንደዛ ከሆነማ እኔንም ኩፍኝ ይይዘኛል” ብሎ አረፈው፡፡ አሪፍ አይደል፡፡ እናማ ኩፍኝ የያዘው ባል ካለ፣ ማን ማንን እንደሳመ ማጣራቱ ጥሩ ነው። ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አይደለም ከአገር ውጪ መሄድ ሰፈር ሲለውጡ እንኳን የሚናፍቅ ነገር መአት ነው፡፡ እናማ ባህር አቋርጠው የሚሄዱ ሰዎቻችን የማይናፍቁት ነገር የለም፡፡ ልጄ…እዚህ ‘እንጠየፈው’ የነበረው ነገር ሁሉ ራቅ ብለው ሲሄዱ፣ “ምነው ያኔ አፌን በቆረጠው…” ምናምን ያሰኛል ይባላል…ወዳጆቻችን እንደሚነግሩን፡፡
እናላችሁ… እዚህ ሳለ እንጀራ ሲቀርብለት፣ “ይሄ እኮ ምግብ አይደለም፡፡ ሰው ዕድሜ ልኩን  ሰጋቱራ ይበላል!” እያለ ሲሸልል የነበረው ሁሉ ‘ኤይቲንዝ ስትሪት’ (ቂ…ቂ...ቂ…) በደረሰ በአራተኛ ቀኑ …
“የእንጀራ ናፍቆት ሊገድለኝ ነው…”
“አንድ ጭልፋ ምስር ወጥ በልቼ ከፈለገ ለምን የዓለም መጨረሻ አይሆንም…”
“ድርቆሽ ፍርፍር በዓይኔ ሲዞር አደረ…” ምናምን ማለት ይጀምራል፡፡
ታዲያላችሁ …ዘንድሮ እንጀራውም፣ ቆጭቆጫውም… ምኑም በገፍ እየሄደ ስለሆነ ምናልባት የምናለሽ ተራ ፓስቴ ካልሆነ፣ የሚናፈቅ ‘ሎካል’ ምግብ ብዙም ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ለመኖር መናፈቅ አለብን!  ልክ ነዋ… ቢያንስ፣ ቢያንስ ጊዜውም ያልፋል፡፡ እዚች የዓለም ክፍልም ብዙዎቻችን ጊዜው እንዲያልፍልን አይደለም ያየነውን፣ ያላየውን ስንትና ስንት ነገር እየናፈቅን ነው፡፡
ሲብስ እኮ… “ዛሬስ ከእነሚስቱ ሊናፍቀኝ ነው ወይ…” ያሰኛል፡፡
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን ታስባለህ በሉኝ፡፡ እንግዲህ የመብራት መጥፋትና የውሀ መቋረጥ፣ አሁን ለምደነው ‘መነጫነጭም’ ቀንሰን የለ…ይሄ ነገር ባዕድ አገር ስንሄድ ----- ቢናፍቀን ምን ይውጠናል! ልክ ነዋ…ብዙ ጊዜ የሚናፈቀው እኮ የተለመደ ነው፡፡
እናላችሁ…አማሪካን’ በገባ በሁለተኛ ወሩ… አለ አይደል… “የመብራት መቋረጥ ናፈቀኝ…” ማለት ቢጀምር ምን ማድረግ ይችላል!
ስሙኝማ…እንዲህ ግራ የገባው ሰው ሊጽፍ የሚችለው ደብዳቤ ይታየኛል፡፡
ለሚመለከተው ሁሉ
ጉዳዩ የአገር ናፍቆትን ይመለከታል
ክቡር ጌታዬ፤ እዚህ አገር ከገባሁ ሁለት ወር ከአሥር ቀን ሆኖኛል፡፡ በእውነቱ ባየሁት ስልጣኔ ተደንቄያለሁ፡፡ ሆኖም ብዙ አገሬ ትቻቸው የመጣኋቸው ነገሮች ከአሁኑ ይናፍቁኝ ጀምረዋል፡፡ ስለሆነም ክቡርነትዎን የምለምነው በናፍቆት የተነሳ አንድ ነገር ሆኜ ለእናንተም ስም ከምሆንባችሁ ቢያንስ በሁለት ቀን አንዴ መብራት ለተወሰነ ሰዓት እንዲቋረጥ እንዲያደርጉልኝ ነው፡፡
በተጨማሪ ደግሞ ውሀ ለአንዲት ደቂቃ እንኳ የማይቋረጥበት ምክንያት አይገባኝም፡፡ የእግዜሩ ዝናብ እንኳን በመዝነቢያው ወራት ሙልጭ ብሎ ይጠፋ የለም እንዴ! በመሆኑም ውሀ ለሀያ አራት ሰዓት መፍሰሱ ከአገሬ ጋር ስለሚያቆራርጠኝ ይህነኑ ተገንዝበው ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ለተወሰነ ሰዓት ውሀዋ ለአመል ያህል እንኳን እንድትጠፋ እንዲያደርጉልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
የመብራት መጥፋትና የውሀ መቋረጥ የናፈቀው የሰው አገር ሰው
አሪፍ አይደል!
ሲብስ እኮ… “ዛሬስ ከእነሚስቱ ሊናፍቀኝ ነው ወይ…” ያሰኛል፡፡
ክፋቱ ለቱሪዝም አይሆንም እንጂ ቢሆን ኖሮ… ‘ተደጋጋሚ የመብራት መቋረጥ የሚፈጥረውን የተደበላለቀ ስሜት መረዳት ከፈለጋችሁ…ከጦቢያ የተሻለ አገር አታገኙም’… ምናምን የሚል መፈክር በኢንተርኔት እናጦፈው ነበር፡ ሊገባ የሚችለውን ‘ዶላሬ’ አስቡትማ!
አንድ ጊዜ አውሮፓ ሁለት አስርት ምናምን ቆይቶ የመጣ ሰው… “ከሄድክ መብራት ምን ያህል ጊዜ ተቋርጦ ያውቃል!” ብለው ሳቀ… (እንደውም መባል ያለበት ‘ሳቀ ሳይሆን ‘ሳቀብኝ’ ነው፡፡)
እናላችሁ እዚህ ‘የለመድናቸው’ ነገሮች ሰው አገር ስንሄድ እየናፈቁ ሰላም እንዳይነሱን አማሪካንም ሆነ ምናምን ስንፈልግ የምንኖርበት አካባቢ ---- መብራት ድርግም የምናደርግበት፣ የውሀ ቧንቧውን የምናደርቅበት ቴክኖሎጂ ይፈልሰፍልንማ!
እናማ…ከመብራትና ከውሀ ሌላ ሰው አገር ስንዘልቅ ሊናፍቁን የሚችሉ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ስሙኝማ…ለምሳሌ የከባድ የጭነት መኪና ጥሩምባ እያምባረቀ የሚሄድ ሚኒባስ ታክሲ ስንት አገር ውስጥ ልናገኝ እንደምንችል አይገርማችሁም…አንዳንድ ታክሲዎችማ ከአምቡላንስና ከፖሊስ ‘ሳይረን’ ጋር የሚቀራረብ ድምጽ ያለው ጡሩምባ ሲያጮሁ… አለ አይደል… “ይቻላል እንዴ!” ብላችሁ ትገረማላችሁ፡፡ እናማ… እንዲህ አይነት ሚኒባስ ታክሲዎች ‘ናፍቆት’ ምን ሊያደርገን እንደሚችል አስቡትማ፡፡ አሀ…ፊልም ላይ ሁሉ ላናገኛቸው እንችላለና!
‘ሀያ አራት ሰዓት አገልግሎት’ ተብሎ ገና አንድ ሰዓት ተኩል እንኳን ሳይሞላ አይደለም ሠራተኞቹ… የጥበቃ ሠራተኛው እንኳን ተጠቅልሎ የሚተኛበት ተቋም… አለ አይደል…በሰው አገር “ናፈቀኝ…” ብትሉ…
“እናንተ አገር ሀያ አራት የሚሞላው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ነው ወይ?” ተብላችሁ ልትጠየቁ ትችላላችሁ፡፡
ሲብስ እኮ… “ዛሬስ ከእነሚስቱ ሊናፍቀኝ ነው ወይ…” ያሰኛል፡፡
ደግሞላችሁ…አለ አይደል…ሰው አገር ከሄዳችሁ በኋላ “ምን እንደምትሆን አያለሁ!” አይነት እንደፈለገው የሚቆጣ፣ ከፍ ዝቅ አድርጎ የሚዘልፍ  ‘ቦስ’ ነገር ባለስልጣን “ናፈቀኝ…” ብትሉ… አለ አይደል… “እንደፈለገ የሚቆጣ ቦስ ማለት ምን ማለት ነው?” ተብላችሁ ልትጠየቁ ትችላላችሁ!
ስሙኝማ…አሁን ለምሳሌ በሰው አገር ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ቢናፍቋችሁ ምን ልትሆኑ እንደምትችሉ አስቡትማ! (እኔ የምለው… ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’’ የራሳቸውን የአየር ሰዓት የማይገዙሳ! አሀ…ፉክክሩ ከበድ ብሏላ!)
“የመብራት መጥፋትና የውሀ መቋረጥ ከሚናፈቅበት አገር ይሰውራችሁ” አይባልም እንጂ…ቢባል ኖሮ በትልልቅ ፊደል እንጽፈው ነበር።
ሲብስ እኮ… “ዛሬስ ከእነሚስቱ ሊናፍቀኝ ነው ወይ…” ያሰኛል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5706 times Last modified on Monday, 26 December 2016 09:55