Sunday, 18 December 2016 00:00

አስሩ ቢሊዬነር ፕሬዚዳንቶችና ንጉሶች!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 * ከ1 ቢሊዮን - $30 ቢሊዮን የሚደርስ ሃብት አላቸው
               * አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከቢሊየነሮቹ አንዱ ናቸው

1. ቢሁሚቦል አዱልያዴጅ እና ቤተሰቡ - $30 ቢሊዮን (የታይላንድ ንጉስ)
ንጉሱ በቅርቡ ቢሞቱም ሀብታቸውን  ቤተሰባቸው ወርሶታል፡፡ በዓለማችን ለረዥም ዘመን በርዕሰ ብሄርነት ያገለገሉ ሲሆን በአገራቸው መልካም ስምና ዝና ያተረፉ ንጉስ ናቸው፡፡ ንጉሱ ጠብመንጃ ይወዱ ነበር፡፡ የጃዝ ሙዚቃ ማድመጥና ጀልባ መቅዘፍ ያስደስታቸዋል፡፡ ፎርብስ፤ የንጉሱን ሀብት ሲገምት ጥቂት በማሳነሱ ታይላንዳውያን ትንሽ በስጨት ብለው ነበር፡፡ (እንዴት ተደፈርን በሚል!)
2. ሃሳናል ቦልክያህ - $20 ቢሊዮን (የብሩኔይ ሱልጣን)
ለሱልጣን ቦልክያህ ከዓለማችን ባለፀጎች አንዱ መሆን እምብዛም የሚከብድ አይደለም፡፡  ለምን? ቢባል፣ በመንግስትና በግል ካዝናቸው መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ሱልጣኑ በዓለም ትልቁ የግል መኖሪያ ቤት ባለቤት ናቸው፡፡ (1ሺ 800 ክፍሎች ያሉት) ምርጥ ሲጋር የሚወዱ ሲሆን የራሳቸውን 747-400 ጀት ያበራሉ፡፡ የተለያዩ ውድና ብርቅ የአውቶሞቢል ስብስቦች አሏቸው፡፡  
3. ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳውድ - $18 ቢሊዮን (የሳኡዲ አረቢያ ንጉስ)
ዕድሜያቸው ወደ 80 ቢገፋም፣ለረዥም ጊዜ ንጉስ ሳይሆኑ ቆይተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወንድማቸው በመሞቱ ነው፡፡ እንደ ሳኡዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ አባልነታቸው፣ የሃብት ምንጫቸው የነዳጅ ዘይት ነው፡፡
4. ካሊፋ ቢን ዛዬድ አል ናህያን - $15 ቢሊዮን (የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ፕሬዚዳንት)
5. ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም - $4 ቢሊዮን (የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጠ/ሚኒስትር)
የነዳጅ ዘይት ገንዘብን በመጠቀም ዱባይን የመካከለኛው ምስራቅ ቬጋስ አድርገዋታል። በእሳቸው ባለቤትነት ተይዘው በነበሩ ሁለት ኩባንያዎች፡- ዱባይ ወርልድ እና ዱባይ ሆልዲንግ አማካይነት በከተማዋ በርካታ ቢዝነሶችና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች የፈጠሩና የገነቡ ሰው ናቸው። ሼክ ሞሃመድ ኢምሬትስ አየር መንገድን ያስጀመሩ ሰው ናቸው፡፡ በተጨማሪም የዱባይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያና የዱባይ ወርልድ ሴንትራል -አል ማክቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ ግንባታን በበላይነት መርተዋል፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ የበረራ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጠውና ባለቤትነቱ የመንግስት ከሆነው ፍላይዱባይ ምስረታ ጀርባም ሼክ ሞሃመድ ነበሩ፡፡  
6. ሃንስ አዳም (ሁለተኛው) - $4 ቢሊዮን (የሊችቴንስቴይን ልኡል)
የአውሮፓ ቢሊዬነር ንጉስ የሆነው ሃንስ አዳም፤ በፋይናንስ ዕውቀቱ በእጅጉ ይታወቃል፡፡  በአሁኑ ጊዜ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን የቤተሰቡን ቢዝነስ ተረክቦ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ንጉሱ ከ1ሺ በላይ ውድና ምርጥ የስዕል ስብስቦች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ከራሱ ጋር የሚቃረን ቢመስልም ዲሞክራሲ ምርጡ የመንግስት ሥርዓት ነው ብሎ ያስባል፡፡
7. ዶናልድ ትራምፕ - $3.8 ቢሊዮን (ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
ቢዝነሳቸውን 7 ጊዜ ያህል ከስሯል ብለው ያመለከቱ ቢሆንም ከወደቁበት በተደጋጋሚ አንሰራርተው ለቢሊዮርነት በቅተዋል፡፡ ፎርብስ፤ የሃብቴን መጠን በእጅጉ አሳንሶታል የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ የሚያሰሙት የሪልእስቴት ከበርቴው ትራምፕ፤ እስከ $10 ቢሊዮን የሚደርስ ሃብት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዋይት ሃውስ የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው መንግስት  የሚከፍላቸውን 400ሺ ዶላር ዓመታዊ ደሞዝ እንደማይቀበሉ ቢሊዬነሩ በተመረጡ ማግስት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ትረምፕ እንደ ቃላቸው ከዘለቁ አሜሪካን ያለ ደሞዝ የሚያገለግሉ ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡      
8. ሞሃመድ Vi - $2.5 ቢሊዮን (የሞሮኮ ንጉስ)
የሞሮኮ ንጉሳውያን ቤተሰቦች በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ ሃብት አላቸው ተብሎ ይታመናል። ዛሬ ንጉስ ሞሃመድ በአገሪቱ ቀዳሚ የመሬትና የግብርና ምርቶች ባለቤት ናቸው፡፡ የንጉሱ ቤተመንግስት በቀን 960 ሺ ዶላር ገደማ ወጪ የተመደበለት ሲሆን፣ አብዛኛው ወጪም ለመኪና ጥገና፣ ለሰራተኞች ክፍያና ለአልባሳት የሚውል ነው፡፡
9. አልበርት (ሁለተኛው)- $1 ቢሊዮን (የሞናኮ ልኡል)
ልኡል አልበርት (ሁለተኛው)፤ በዓለም እጅግ ባለጸጋ ከሆኑ ንጉሳውያን ቤተሰቦች አንዱ ሲሆኑ ሃብታቸው በፈረንሳይና ሞናኮ የሚገኙ መሬቶችን ይጨምራል።  
10. ኑርሱልጣን ናዛርባዬቭ - $1 ቢሊዮን (የካዛኪስታን ፕሬዚዳንት)
የካዛኪስታኑ ፕሬዚዳንት ኑርሱልጣን ናዛርባዬቭ፣ ከዓለማችን ቢሊዬነር ፕሬዚዳንቶች አንዱ ሲሆኑ የሃብት መጠናቸው 1ቢ.ዶላር ይገመታል፡፡ ከታላቋ ሶቭየት ህብረት መበታተን አንስቶ በሥልጣን ላይ ሲሆኑ እንደ አለመታደል ሆኖ ስማቸው ከሙስና ጋር ይነሳል፡፡

Read 2917 times