Sunday, 18 December 2016 00:00

ማነህ ባለሳምንት? የ“መሪ” ወርተራ

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(2 votes)

 እንደ መግቢያ
የኦርቶዶክሶች ማህበር ቤት ወርተረኛውን ለመመደብ ዳቦ ከተቆረሰና መውጫ ሲቃረብ  ሙሴው ይነሳና:
ማነህ ባለሳምንት?
ያስጠምድህ ባስራ ስምንት
እኔ ነኝ የምትል የቅዱስ ገብርኤል ወዳጅ ይላል።
ገብርኤሉ እንደ ማኅበራቸው ታቦት ሥም ይቀያየራል። ተራኛው ይቆምን የሚባለውን ብሎ ጽዋውን ይረከባል። ይህ እውደት በየወሩ ቋሚና ቀጣይ ነው። ከልጅነቴ ያስታወስኩት ነው። እዚህም
ማነህ ባለሳምንት?
እኔ ነኝ የምትል  ሴራ ወዳጅ ማለት የሚቻል ይመስለኛል።
ማኅበሩ ወርሐዊ ነውና በየወሩ ተረኛው ደጋሽ ቤት ይሔዳል። በፓርቲዎች ውስጥ ያለው ሹም ሽር የዚህ አይነት ባሕርይ የሚያጣ አይመስለኝም። ግቡ፤ መንፈሳዊነቱና፣ አለማዊነቱ፣ ሰላማዊነቱና ሴራነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው።
የምጽፈውን የምጽፈው ብልጭ ሲልብኝ ወይም  ሲልልኝ ነው። አብዛኛው! እንጅ ይህንን እጽፋለሁ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ እጽፋለሁ የሚል እቅድ ኖሮኝ የሚያውቅ አይመስለኝም። ግብታዊነት የሚሉት ሥር የምመደብ ይመስለኛል። ይህም የተጻፈው በዚሁ አይነት ነው።
ማህበራዊ  ገጽታዎች በተለይም  Facebook ትልቅ ትምህርት ቤት ሆኖኛል። አገር ተሰብስቦ ሲያወጋ የሚያድረውንና የሚውለውን ማዳመጥ፣ አንዳንዴም በወጉ ውስጥ ወጣ-ገባ ይመጣል። Facebook  ከገባሁ ሁለት አመት ሆኖኛልና  አንድ ቀን “እንኳን ደስ ያለህ!” የሚል መልዕክት ከFacebook አግኝቼ ሳቅኩኝ። እኔ የማላስታውሰውን አስታውሶ የሚነግረኝ “ወዳጅ”ም አለኝ ማለት ነው።
አገር ተሰብስቦ ያወጋል ብያለሁ። አገር ደግሞ ሰፊ ነውና ብዙ ነገር ያቅፋል።ከዚህ ውስጥ ጥሩ፤ መጥፎ፤ አስጸያፊም አለ። ፈረንጅ The Good,The Bad, and The Ugly እንዲል! “ሆድ ከአገር ይሰፋል!” ብሎ መጓዝ ነው። ወይ እንደ ፈረንጆቹ “ልዩነታችን ለዘለዓለም ይኑር!” (Vive la difference!) ብሎ መቀጠል! ነው።
እንግዲህ “የሀሳብ ልዩነት” ሲባል “ጤናማ ልዩነት!” ማለቴ እንጅ አጸያፊውም “ለዘለአለም ይኑር!” ማለት አይመስለኝም! እንደኔ እንደኔ አስጸያፊው አንድም ቀን አይደር! የFacebook ነገር ጥሩ ነው። አስጸያፊው ተመክሮ ተዘክሮ የማይመለስ ከሆነ ለማሰናበት 30 ሴኮንድ  በቂ ነው። “ከዚች ሴኮንድ ጀምሮ  ‘ወዳጄ’ አይደለሽም፤ አይደለህም!”  ማለት ይቻላል። “Unfriend!” ይለዋል። “ተፋቱ!” ማለት ነው። በዚሁ መሠረት መክሬ - ዘክሬ እምቢ ያሉኝን ጥቂት “ፈትቼ” የለቀቅኳቸው አሉ።
የአሁኑ ጉዳይ
Facebook ከገጠምኩ ሁለት አመት ሆኖኛል ብያለሁ። ትምህርት ቤትም ሆኖኛል ብያለሁ። ከልቤ ነው! 5,000 ወዳጆች(Friends) አሉኝ! ብዙዎች ወዳጅ ሊሆኑ ጠይቀውኝ በFacebook “ያለህ ይበቃል!” ስለተባልኩ አልጨመርኳቸውምና በዚህ አጋጣሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ወዳጆቼ በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው።በአብዛኛው ያሰኘኝ እንደነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያሉ አዛውንቶችም ስለአሉበት ነው።
የዚህ የኔ “ወጣት ወዳጆቼ” ነገር ይገርመኛል። ሁሉም ማለት ይቻላል “አንተና ጋሼ አሰፋ!” ነው የሚሉኝ። ልጆቼ አድርጌ ነው የምቆጥራቸው! ልጆቼም የልጅ-ልጆቼም “አንተ” ስለሚሉኝ! እነሱ “አሴ!” ነው የሚሉኝ። እዚህም አሴ የሚሉኝ ጥቂት አሉ። አንድ አገር ሙሉ፤ አለም ሙሉ ቤተሰብ ያለኝ መስሎ ይሰማኛል! ደስ ደስም ይለኛል! ጥያቄ ይጠይቁኛል። መልስም እሰጣለሁ። “ይህን አድርግ/ አታድርግ”ም  ይመክሩኛል። አንዳንዴ ውይይታቸውም ጫወታቸውም ውስጥ እገባለሁ። ሰሞኑን በተለየም ልደቱ አያሌውን ባንድ በኩል፣  ሰማያዊ ፓርቲን በሌላው አድርገው ሲወያዩ ገባሁና አስተያየት ሰጠሁ፡፡
የመጀመሪያው አስተያየት ይኸውና፡-
እኔ ከብዛታቸውም ይሁን የሚሉት በደንብ ስለማይገባኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ላይ ምንም ከማለት ተቆጥቤ ኖርኩ። የዛሬ ሁለት ይሁን ሶስት ወር በፊት ዶክተር መረራ ጉዲናና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር እዚህ አሜሪካ መሆናቸውን ሰማሁና ለሁለቱም ደወልኩላቸው። መረራን አውቀዋለሁ። ይልቃልን አላውቀውም። ሁለቴ መሰለኝ ያነጋገርኩት። ማነጋገር ከማለት ያዳመጥኩት ማለት ይሻላል። ብስለቱ፤ ጥልቀቱና እርጋታው በጣም ገርሞኝ በርታ! ተባረክ! አልኩት። ለሰላምታና በርቱ ለማለት ብቻ ነበር የደወልኩት። ወዲያውኑ ወረደ፤ ይበሉ ተሻረ ወይም ተባረረ የሚል ሰምቼ “አይ የኛ ነገር!” ብዬ አዘንኩ።
አሁን  ከኢዴፓ ጋር የሚባለው በሙሉ አይገባኝም። ዝርዝር መረጃ ስለሌለኝና ምናልባትም እንዳይ ኖረኝ ስለፈለኩም ሊሆን ይችላል። የማይሆን ነገር በሰማሁ ቁጥር ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ያመኛል።ውስጤን! ኢደፓ ልደቱ ያለበት ከሆነ ባለፈው አንድ ስብሰባ ላይ ልደቱ ሲናገር የሰማሁት የመንግስት ወኪል ወይ ቃል አቀባይ የሚመስል ጠረን ነበረው ልበል? እኔ ምን አውቃለሁ!
ሁለተኛም አስተያየት ሰጥቻለሁ። በሁለተኛው እኔን በግልም የሚነካ ተነስቶ ስለነበረ ነው። ይኸውና፡-
በዚህ ዙሪያ የሚደረገውን ውይይት፤ በተለየም የጋላታ ጋሞና የኤደን መኮንን ተስማምቶኛል! “የሠለጠነ ውይይት ወይም የሀሳብ መለዋዋጥ” Civilized Discourse) መስሎ ታይቶኛል። ከዚያ በፊት ግን ስለ እኔ መጀመሪያ ከደርግ ጋር  የነበረው ግንኙነት!  እኔ የነበረኝ ግንኙነት፣ ያ “የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ነው!” ብዬ ሙሉ ለሙሉ አምኜበት ነው። ነውም!! የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዘመናት ባርነት ነጻ አውጥቷል። ኢትዮጵያን ሬፑብሊክ አድርጓል። ከዚያ በኋላ በዋናነት በአመራር፤ በተለይም በመንግስቱ ምክንያት አሰቃቂና አሳዛኝ በደል በኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይም በወጣቱ ላይ ተፈጽሟል። ለዚያም ተጠያቂና ናቸው የተባሉት ዋጋውን በእስራት ከፍለዋል። ፋይሉ አንድ ቀን አንድ ቦታ መዘጋት ያለበት ይመስለኛል። ያለበለዚያ ሁሌ ሙሾ ያወረድን እንደሁ የአሁኑን ያስተናል ብዬ እፈራለሁ።
በተለየ እኔን በሚመለከት! ከተወሰነ ቀን በኋላ ድጋፌን አቆምኩ። ይህንኑ “የኢትዮጵያ አብዮት ከየት ወዴት? ትላንት፤ ዛሬና ነገ!” የሚል ወደ 30 ገጽ የሚደርስ ጽፌ አሰራጨሁ። “ነጻነት” ቅጽ 1 ቁጥር 1! ለዚያም ወደ 11 አመት ታሰርኩ። ያ ፋይሉን የሚዘጋልን መሰለኝ።
ልደቱን በሚመለከት በ97 ምርጫ ሰበብ በሚደረገው ሁካታ ምክንያት email ሁሉ ተለዋውጫለሁ። እስቲ ለምትከሱቱ ማስረጃ አቅርቡ? ብዬም የጻፍኩ ይመስለኛል። ስለዚህ የልደቱን ጉዳይ የማየው በጅምላ መልክ አይደለም ለማለት ነው። ያኛውን ወይም ይህኛውን ድርጅት ለምን አትደግፍም? ለተባለው ሲመች “አንተም ተው! አንቺም ተይ!” የሚል ሽማግሌ ያስፈልጋል በሚል ምክንያት ይመስለኛል።
ይህ “የሰለጠነ ውይይት” ጥሩ ነው፣ አድማሱን ሰፋ ብታደርጉት ጥሩ ይመስለኛል። ሰፋ ማድረግ ማለት ይህ እርስ-በርስ  መባላት በ97 ምርጫ ጊዜም ሆነ በደርግ ዘመን ያደረገውን አይቶ ዘለቄታው ምን ይመስላል? የሚል አንጻር መጨመር ማለት ነው። ስለ ልደቱ አሁን የሰጠሁት አስተያየት በውይይቱ ላይ የተሰጠውን አስተያየት ጠረኑን ስለ አልወደድኩት ነው። “መስሎ መታየት” ሌላ ትርጉም መስጠቱ ያለ ነውና! Pereception is Reality የሚሉት!
እዚህ ከላይ በለጠፍኩት “..እኔ ከብዛታቸውም ይሁን የሚሉት በደንብ ስለማይገባኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ላይ ምንም ከማለት ተቆጥቤ ኖርኩ። የዛሬ ሁለት ይሁን ሶስት ወር በፊት ዶክተር መረራ ጉዲናና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር እዚህ አሜሪካ መሆናቸውን ሰማሁና ለሁለቱም ደወልኩላቸው። መረራን አውቀዋለሁ።ይልቃልን አላውቀውም…” በሚለው ልጀምር መሰለኝ፡፡
ልወቅ እንኳ ብል ለማወቅ የሚያስቸግር ይመስለኛል። “ዘጠና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል ይሁን ተፈልፍለዋል” የሚል ነገር ያነበብኩ ይመስለኛል። በጥንቃቄ ነው የማነበው! ጥንቃቄው  ለአገሬ ብቻ አይመስለኝም። ለጤንነቴም ጭምር ይመስለኛል። ጠለቅ  ብዬ ለማወቅ ብፈልግ፤ የሚጠለቅበት ጥልቀት አለው ብለን ብንገምት እንኳ፤ መንፈሴን የሚረብሸው ይመስለኛል።
ለመሆኑ ምኑ ነው መንፈስ የሚረብሸው? ወይም ሊረብሸው የሚችለው? ጥሩ ጥያቄ ነው! ዘጠና  ፓርቲዎች ተመሠረቱ ተባለ። ለዘጠና ፓርቲ የሚሆን የፖለቲካ ጽንሰ-ሐሳብ (Theory)ከየት ሊመጣ ነው? ሁሌም፤ አሁንም ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ  የቀኝ ፖለቲካ፤ የመሀል ፖለቲካና የግራ ፖለቲካ ነው። እርግጥ “ጽንፈኞች” (Extrimists) የሚባሉ  የግራም የቀኝም አሉ። ጽንፈኞች ቁጥራቸውም ተሰሚነታቸውም ከቁጥር የማይገባ ስለሆነ  “ጤና-ያጡ ግለሰቦች መሰባሰቢያ” ተደርጎ ይወሰድና የሚያተኮርበት የለም። የሚተኮርበትም አይደለም። እርግጥ ዛሬ ያለፈ በደል ክምር ገንፍሎ፤ የሐይማኖት ሽፋን ሁሉ ወስዶ አስፈሪ ሆኗል። ያም ቢሆን ያው ጽንፈኛ ናቸው። አሁን በፈነዳው የሕዝብ ቁጣ ሳቢያ ዛሬ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ “ጽንፍና መሀል” ለመለየት አጉልቶ የሚያሳይ መነጽር ሳያስፈልግ የሚቀር አይመስለኝም። አንዱ ይህ ይመስለኛል ገሸሽ እንድል ያደረገኝ። “ዘጠና ድርጅቶች” የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም’ኮ! የለም’ኮ! አይገባም’ኮ! “በአንድ አፍ ተነጋገሩ ወይም መነጋገር ትችላላችሁ!” ብሎ፤ መክሮ፤ ገስጾ፤ ተማጽኖ ማቅረብ ለኔም ሆነ  እንደኔ ላለው ተራ ተርታ ሰው (The average person) ከባድ የቤት ሥራ ይመስለኛል።
ሌላው የታየኝ ችግር “እሽ ዘጠና ሁኑ! ለመሆኑ ልታሳፍሩን የምትፈልጉት አህያ፤ በቅሎ፤ ፈረስ፤ ጋሪ፤ ታክሲ፤ አውቶቡስ፤ ባቡር፤ አውሮፕላን ወይም መርከብ የትና ወዴት ሊወስደን፣ ሊያደርሰን ነው?” የሚለው ጥያቄ ግልጽ አይደለም። ለኔ አይደለም! አላማችን፤ ግባችን፤ አድማሳችን የማያሻማ የተማረ የተመራመረውም ሆነ ከተሜው፤ ገጠሬው ወጣት ሽማግሌ አስተርጓሚ ሳይፈልግ መረዳት የሚገባው መሆን አለበት። መልእክቴ ግልጽ ካልሆነ የሰሚው፤ የአድማጩ ችግር አይመስለኝም። የተናጋሪው፣ የአቅራቢው እንጅ።
ሌላው ድፍን አገር የሚያውቀው ላይ ከሚገባው በላይ ትኩረት የሚሰጠው ይመስለኛል። ወያኔ በሉት ኢሕአዴግ እቡይ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ዛሬ ሳይሆን ሕዝቡ ከግንቦት 1983 ጀምሮ የሚያውቀው ነው። እዚያ ላይ ብርቱ ጊዜ የሚባክን ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ጋር አብሮ የሚሔደው ክስና ወቀሳ፤ ዛሬም ያልተቋጨው “ይኸኛውወያኔ ሰርጎና አሰርጎ ያስገባው ግለሰብ ነው፤ ድርጀት ነው” የሚለው ጣት መቀሰር ነው። የአስርጎ ማስገባት ነገር አለም አቀፋዊ መሆኑን ባላውቅም በየአገሩ የነበረ፣ ያለ፤ የሚኖር ነው። እዚህ አሜሪካም አለ። በቅርቡ እንግሊዝ አገር በዚሁ ጉዳይ የሌበርና የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ይሁን ሌላ ሲካሰሱ ነበር። ይልቅስ የሚደንቀው ወያኔ ሰርጎ ወይም አሰርጎ ባያስገባ ነው። “ወያኔ እንዲህ አድርጎ እንዲህ ሆንን” ማለት ወያኔ በፖለቲካ ጥበብ፤ ቴክኒክና ታክቲክ ይበልጠናል፤ በልጦናል ብሎ እንደማመን ይመስለኛል። ቡሐቃዋን በቅጡ ሳትከድን  ሁሌ በድመቷ ወይም ውሻው ላይ እንደምታማርረው የቤት እመቤት የሚመስል ነገር ያለው ይመስለኛል። በሩን ሊዘጋ የሚችለውን ያክል መዝጋት ነው። ካልተቻለ በዚያም ይሁን በዚያ ለዚህ የጨዋታ ሜዳ ብቁ ሆኖ አለመገኘትንም የሚጦቁም ይመስለኛል። “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው!” ንም አውቃለሁ፡፡
ሴራው
የ1997 አገር አቀፍ ምርጫ ውጤትና ያንን ተከትሎ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉት ያደረጉት አልገባኝም። ሊገባኝ የሚችልም አይመስለኝም። ያንን በሚመለከት በወቅቱ ተዋናይ ከነበሩት አንዱን የተቃዋሚ ድርጅት መሪ በስልክ ለማነጋገር ሞክሬ መልስ አላገኘሁም። የሚመስል መልስ አላገኘሁም ማለት የሚሻል ይመስለኛል። ምርጫውን አሸነፉኮ! በአገር አቀፍ ደረጃ ከ200 በላይ መቀመጫ ያገኙ ይመስለኛል። ያም ይቅር አዲስ አበባን፤ የኢትዮጵያን ዋና ከተማ፤ የአፍሪቃን ዋና ከተማ፤ የተባበሩት መንግስታትን ዋና ከተማን ሙሉ ለሙሉ አሸነፉኮ! ገቢናው መሪው፣ ሹፌሩ (The Driver’s Seat) ያለውኮ አዲስ አበባ ከተማ ነው! ለኔ ማመን የተሳነኝ ድል  ነበር።
ከምርጫ በኋላ በአብዛኛው አወዛጋቢ ጥያቄ ይነሳል። የትም ሁሌም ያለ ጥያቄ ነው። ውዝግቡን ለመፍታትም የታወቀና የተረጋገጠ የሌሎች አገሮች ተመክሮም አለ። የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያንን የተጠራቀመ ልምድ አልተጠቀሙበትም። ሊጠቀሙ አልፈለጉም ወይም ከነአካቴው አያውቁትም ማለትም የሚያስችል ይመስላል። የሚያማርሩበት ነገር እንኳቢኖር፤ በኔ አስተያየት፣ ይህን ያክል የሚያማርር ነጥብ የነበረ አልመሰለኝም፤ ዝነኛው “ብልጥ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል!” የሚለው መመሪያ እንደ ሀ ሁ መታወቅ የነበረበት ይመስለኛል። የወሰዱት አማራጭ ትላንትና የመረጣቸውን  ሕዝብ “እስቲ ፓርላማ እንግባ አንግባ!?  ምን ይመስላችኋል!?” ብለን እንጠይቅ የሚል ነበር። ውጤቱ  “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች!” ሆነ። በብዙ መቶ የሚቆጠር  ሕዝብ ለሞት ተዳረገ። መሪዎቹ የተባሉት ከርቼሌ ወረዱ። “አስታራቂ ሽማግሌ!” የሚባሉ ከመለስ ዜናዊ ፋብሪካ ተፈለፈሉ። መሪዎቹ መለስ ዜናዊን ይቅርታ ጠይቀው ተፈቱ። ያ የኢትዮጵያ ሕዝብ  ያንን ሁሉ ጥይትና ዱላ ችሎ፣ ተአምር በሚመስል መንገድ ያገኘው ድል  ከንቱ ሆነ። ለዚህ አይነት  ክህደት እንኳን ባይባል አላዋቂ ሥራ ተጠያቂ፤ ተጠያቂው(ዎች) ማነው? እነማናቸው? የሚለው መልስ ያገኘ አይመስልም። ከሆነም እኔ አልሰማሁም። አንድ እርግጠኛ ነገር አለ። ወያኔ፣ ”ይህችን ስህተት አንደግማትም!” የሚል ዘላቂ ትምህርት አግኝቶ ተግባራዊ አድርጓል። የምርጫውን በር ዘግቶ ቁልፉን ወረወረው! የተቀረነው የተማርንበት አይመስለኝም።
ሌላ ተያያዥ ጥያቄ መጠየቅም የምንችል ይመስለኛል። ወያኔ የተማረበት የሚመስለውን ዞር ብለው ሲያዩት ጊዜያዊ ይመስላል። ባሰበት እንጅ አልተማረበትም። ዛሬ የውስጥ አዋቂዎች ነን የሚሉ እንደሚነግሩኝ (ለነገሩ የማናውቀው ውስጥ ያለ ይመስል) “ብትፈልግ ወያኔ፤ ብትፈልግ ኢሕአዴግ በለው የሚባል ነገር የለም። ተከስክሷል! ጥላው ነው ያለ የሚያስመስለው። እያንዳንዱ የኢሕአዴግ አካል አምሳል ነኝ ተብዬው ውስጡ ሶስት ወይም አራት ቦታ ተፈረካክሶ ያለ መልሕቅ ይዋዥቃል” ነው የሚሉኝ። በእርግጠኝነት ያላቸው ነገር ቢኖር አፈሙዙ ነው። ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚባሉት ያው የዛሬ ስንትስ አመት ሲሰሩት የነበረውን ያንን የውስጥ አድማ እንበለው ሴራ ቀጥለዉበታል። ትላንትን ዛሬ አድርገውታል። ይህ፤ ለዚህ መነሻ የሆነኝ የሰማያዊ ፓርቲ በአደባባይ መናቆር ትላንት፣ አሁንም ትላንት ሳይሆን ዛሬ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።
እንዳልኩት እኔ የአሁኑን ድርጅቶችም ሆነ መሪዎቻቸውን አብዛኞቹን አላውቃቸውም። ዶክተር መረራ ጉዲናን አውቀዋለሁ። ቢያስሩት “አረ እባካችሁ ፍቱት!” ብዬም ጽፍያለሁ። ዶክተር በየነ ጴጥሮስን ትንሽ የማውቀው፣ በአብዛኛው  የማላውቀው ይመስለኛል። የዶክተር በየነ ስም ሲነሳ ሱዘን ሳረንደንን (Susan Sarndon 1995) ያስታውሰኛል። የዛሬ ስንትስ አመት (1995)Dead Man Walking  የሚል ፊልም ውስጥ ዋናዋ ተዋናይ ነበረች። “በቁሙ የሞተ!” እንደማለት ነው። በቁሙ ሞቶም ሙቱ ሰውም ግና ነፍሱ አልወጣችምና ፊልሙ ውስጥ ይታያል። እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ፊልም ነበር። ዶክተር በየነን የሚመሳሰልብኝ ያንን ሁሉ ድርጀት፤ በተለይም የደቡብን ሕብረት ቀብሮ፤ አባላቱን አሳዶ ዛሬም እዚያው መኖሩ ነው። ልጅ ሆኜ ጨንቻ መሰለኝ፣ የሰማሁትን የልጆች ዘፈንም አስታወሰኝ። “እዚያ ነሽ ዛሬም እዚያው ነሽ? አስሮ የሚገርፍሽ ዘመድም የለሽ፣ ዛሬም እዚያ ነሽ!” ይሉ ነበር። ከዚህ ሌላ ኢንጂነር ይልቃልን በስልክ ሁለቴ አነጋግሬአለሁ። ብርቱካን ሚደቅሳን አሁንም አነጋግራታለሁ። በጥሞና እንደ ተሳታፊ፤ እንደ ህግ ባለሙያም ያኔ የሆነውን፣ ለእስራትና ለስደት ያበቃትን ከሁለት ዓመት በፊት አውግታኛለች። ከልጆቼ እንደ አንዱ አያታለሁ። ልደቱን በአካል አላውቀውም። የዛሬ ስንት አመት (March 8,2006) ምርጫው ውስጥና ውጭ ስለሆነው ነገር የጻፈውን መጽሐፍ አንብቤ፤ ወድጄው፤ Email አድርግጌለት መልስም (03/27/2006) ሰጥቶኛል። እውቄቴ ይህችው ነች!
የአሁኑ ውዝግብ ዘመነ ደርግን ያስታውሰኛል። በየቀኑም ባይሆን በየሳምንቱ አዲስ ድርጀት ወይም ስንጣቂ ተመሥርቶ ወረቀት ይበትንና ያንን አገኘው ነበር። የሚደራጅ ሳይሆን የሚፈለፈሉ ይመስል ነበርና “ማለቂያ የለውም እንዴ!” የሚያሰኝ ነገር ነበረው። እንዳያልቅ የለምና እንዳይሆን ሆኖ አለቀ። ከዚያ ዘመን  ዛሬም ቢሆን፣ አልፎ አልፎ፣ “አለና!” የሚሉና ሙሾ የሚያወርዱ “በቁም የሞቱ!” አያለሁ፤ እሰማለሁም። እኔ የማስታውሰው የመጨረሻው “የስንጥቅ” ድርጅት መሥራች ዶክተር አለሙ አበበ መስለኝ። “ቀይ ባንዲራ!” ነው ያለው? የመኢሶን ግንባር ተዋናይ ነበርና፣ መኢሶን ላይ ጀንበር ሲያዘቀዝቅ አይቶ መሰለኝ ቀይ ባንዲራ ያነሳው። ለሱም አልበጀውምና ከርቸሌ ወረደ።
ለምናውቀውም ለማናወቀውም ዝርዝሩ ብዙ ነውና አልገባበትም። ብፈልግም የምችል አይመስለኝም። አልበርት አይንስታይን (Albert Eienstein) ብሏል ያሉትን እደግመዋለሁ፡- “ያንኑ እየመላለሰ ግን ከቅድሙ የተለየ ወጤት አገኛለሁ ብሎ የሚያምን እብድ ብቻ ነው!” የኛም ሰው ይህንኑ ይላል። “አብዷል እንዴ!  አብዳለች እንዴ!”  ይህንን የሚሉት ተመክሮም ተዘክሮም የማይመለስ ሰው ሲያገኙ ነው። አሁኑ ያሉት ድርጅቶች ከሌላው አለም ተመክሮ አለመማመር ብቻ ሳይሆን ባለፈው 50 አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሆነውም አልተማሩም። ከሌላው ስህተት አለመማር ብቻ ሳይሆን ትላንት ጥዋት ራሳቸው ከሰሩትም የተማሩ አልመሰለኝም። አንድ ሌላ ነገር፤ ከወጣንበት፤ ከመጣንበት፣ የተሻለ ቀንም እናመጣልሀለን ከምንለው ከኢትዮጵያ ሕዝብ የአኗኗርና የአደረጃጀት ታሪክም የምንማር አልመሰለኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ ያክል እቁብና እድርን እንውሰድ። የአንድ እቁብ ወይም እድር ዳኛ፤ “እባክችሁ ደክሞኛልና ሌላ ዳኛ እንፈልግ!” ብሎ  ለምኖ ነው ከዳኝነቱ የሚነሳው። ከሥልጣኑ ማለት ነው!! ከዚህ የምንማረው ቢኖር ጀማው፤ የእድሩ ወይም የእቁቡ አባላት በዳኛቸው ላይ ሙሉ እምነት አላቸው ማለት ነው። ይህንን ማለት ደግሞ መጀመሪያውኑ የሚሆናቸውን፤ የሚያዘልቃቸውን ሰው አይተውና፤ ለይተው መርጠው ነበር ማለት ነው።
ይህ በየሳምንቱ የፖለቲካ ድርጅት መሪ መለዋወጥ የሚያመጣው ሌላም ችግር ያለው ይመስለኛል። የድርጅቱን ተቀባይነት ያሳጣል። አንድ የሕዝብ ስብሰባ ላይ ባለፈው ሰኞ አሰፋ መሪ ነኝ ብሎ መጥቶ፣ የአሁኑ ሰኞ ከበደ መሪ ነኝ ብሎ ቢመጣ ሕዝቡ ግራ የሚጋባ ይመስለኛል። “ስምህን ማን አልከኝ? ያ አሰፋ የተባለው ሰውዬ አልነበር አለቃችሁ?” የሚልና የመሳሰለ ጥያቄ ያስነሳል። የመሪና የድርጅት ስም አብሮ አጣምሮ ማየትና ማወቅ አለ:: Name Recoginition የሚሉት ነው። ይህ በተለዋወጠ ቁጥር ሕዝቡ፤ደጋፊ የሆነውም ያልሆነውም ይህንን ነገር “የልጅ ጫወታ አደረጉት እንዴ?” ማለቱ የማይቀር ነው። እኔም እላለሁና!
የኦርቶዶክሱ ካሕን ሲያሳርግ በሚለው ልቋጭ መሰለኝ፡- “ዘሀለፈ ሥርየት ወለዘይመጽእ እቅበት!” ይላል። “ላለፈው ምህረትን ለመጪው መቆጠብን ይስጣችሁ!” ማለት ነው። መቆጠብ ማለት ደግሞ ያንኑ አለመደጋገም ማለት ነው፡፡ ካህናቱ “ገዝቻለሁ!” የሚሉትም አላቸው። ይህ የሚሆነው ተመክሮ ተዘክሮ አልመለስ ያለውን ዳግም እዚያች ቦታ/ ድርጊት ድርሽ እንዳትል ብሎ ቁልፍ መቆለፍ ማለት ነው። መጽሐፉ ውስጥ “ያሰራችሁት የታሰረ የፈታችሁት የተፈታ ይሁን” የሚል ሥልጣን ተሰጥቷቸዋልና ነው።
አወይ ያ ሥልጣን ቢኖረኝ!

Read 2334 times