Sunday, 18 December 2016 00:00

የንጉስ አገዛዝ ታሪክ ሲፈተሸ

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(2 votes)

   “የካዎ አለማየሁ አርሼ ዜና እረፍት”
                          
       ትላንትና አርባ ምንጭ ወንድሜ፤ ሻምበል ሐብተ ገብርኤል ጫቦ፤ ጋ ደውዬ ነበር።” አሴ ነብይ ነህ !” አለኝ። “ምነው?” ብለው ትላንት ይሁን ከትላንትና ወዲያ ጋንታ ወጥቶ የካዎ አለማየህ አርሼ ቀብር ሥነስርዓት ላይ ተገኝቶ እንደተመለስ ነገረኝ።
 ካዎ ማለት በጋሞ “ንጉሥ” ማለት ነው። “ንጉሥ” ስንል በተለምዶ ከምናውቀው ከኢትዮጵያ ንጉስ፤ ”ከፈላጭና ቆራጩ” ጋር እንዳናዛምድ ያስፈልጋል። የጋሞ ንጉስ የሕዝቡ የመንፈሳዊና አለማዊ አባት፤ ተጠሪ ማለት ነው። ካዎ ይሁን እንጅ በግሉ የሚወስነው ምንም ነገር የለውም። ነገር ሁሉ የሚወሰነው በአደባባይ (በዱቡሻ) በሕዝብ ተመራጮች ነው።
አለማየሁ አርሼ የጋንታ ንጉስ ነበሩ። ጋንታ ማለት ዛሬ ይህንን አርባ ምንጭ ከተማ ብለን የምንጠራውንም ያጠቃልል ነበር። የእናታችን የማቱኬ አጆ አገር ነው። አሁን ጋንታ ሆኖ የተረፈው አርባ ምንጭን ለምታውቁ፤ ይህ ከሸቻ በላይ ቀጥ ብሎ ወደ ላይ የሚወጣው ተራራ ነው።
የካዎ አለማየሁ የቀብር ሥነ-ስርአት ለየት ያለ ነበር። መጀመሪያ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፍትሀት ተደረገላቸው። ከዚያም የአባታቸው የካዎ አርሼ መካነመቃብር ወደአለበት ሌላ ተራራና ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ ነበር። ፍትሀት ከተፈታ ለምን ካዎ ገብርኤል አልተቀበሩም?  እኔም ጠይቄ ነበር።
ታሪኩ እንዲህ ነው። ካዎ አርሼ፤ የአለማየሁ አባት፤ ገብርኤል ተቀበሩ። ከሶስት አመትበኋላ መቃብራቸው ተቆፍሮ አጽማቸው አሁን የተቀበሩበት የአባቶቻቸውና የካዎ መካነ መቃብር ተውሰደ። ለምን? ካዎ አርሼ በሞት ከተለዩ በኋላ ለሁለት አመት ያክል ድርቅ ገብቶ ጋንታ ተቸገረ። ለዚህ ያደረሰን ኃጢአት ምንድነው ሲባል ጎሜ ነው ተባለ::
ጎሜ ነው ብለው አዋዎች ፈቱ። ሥራቸው ይኸው የሆነ “ዴሙታ” የሚባሉ አሉ። ጎሜ ማለት ኃጢአት ማለት ነው። ኃጢአቱ የካዎ አርሼ ገብርኤል መቀበር ነበር። በሁለተኛው አመት መቃብራቸው ተቆፍሮ አጽማቸው አሁን ያሉበት ተወሰደ። ይህ በሆነ በጥቂት ቀን ውስጥ ዝናብ ወረደ። አገር ጥጋብ በጥጋብ ሆነ። ታሪኩ ይኸው ነው!
“አሴ ነብይ ነህ!” ወደ አለኝ ልመለስ። የዛሬ ሶስት ወር ገደማ ይመስኛል፡፡ ጋንታ ስለአሉት የእናታችን ዘመዶች ስናወጋ፣ የካዎ አለማየሁ ሥም ተነሳ። እንዴት ነው የሚኖሩት ብዬ ስጠይቅ፣ ትንሽ እንደሚቸገሩ ነገረኝ። ለዚያ ያክል የሚሆን ትንሽ መደጎሚያ ላኩኝና  ወንድሜ ሔዶ፤ ሰጥቶ፤ ቀኑን ሁሉ እዚያ ዉሎ ተመለሰ። ምርቃታቸው ሰፊና ረዥምም ነበር። “አንስተን የማናቀውን ሰው አንስተህ መናገር መሰናበታችን ነበር!” አለኝ። ነብይነቱ ይህ ነው።
በዚች ላይ ስለ ጋሞ በተጨማሪ ለማወቅ ፕሮፌሰር ጁዲዝ ኦልምስቲድ  (Judith Olmstead) የጻፈችውን A Women Between Two Worlds  ማንበቡ ጥሩ ይመስለኛል። በኔ አስተያየት ስለ ኢትዮጵያ ከተጻፉት መጽሐፍት ውስጥ ተወዳዳሪ ቢኖረው ጥቂት ነው። ተለይም ዛሬ ለምንገኝበትና ለምንወዛገብበት ዘመን፣ ደቡቡ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያ የሚያሳይ ነው።
ሌላ ትዝ ያለኝ ምንሊክ መጣ፣ ሔደ….. እያልን ወያኔ ድረስ ልንደርስ እንችላለን። በዚህ ዘመን ጋሞ ግብር ገበረ እንጅ መንግስቱን አልገበረም። እንዳለ ነው! ይገርመኛል!
ካዎ አለማየሁ ወንድ ልጅ አልነበራቸውም። በዚያው በ ተቀበሩ ለት የአጎታቸው ልጅ የብር ቀለበቱን አጥልቆ የጋንታ ካዎ ሆነ!
****
በማግስቱ
የሚከተለው Faceboo ላይ ከወጣ በኋላ የካዎ አለማየሁ ጉዳይ የገኘው አዲስ ሕይወት መሆኑ ነው።
አንድ የFacebook ወዳጄ “ንጉሥ” ስንል በተለምዶ ከምናውቀው ከኢትዮጵያ ንጉስ፤ ከፈላጭና ቆራጩ ጋር እንዳናዛምድ ያስፈልጋል” ባልኩት ላይ የሰጠው አስተያየት ይኸውና። ሥሙንመጥቀስ አስፈላጊ አልመስለኝም።
ኢትዮጵያ እኮ ምርጥ መሪዎቿ ንጉሶቿ ማለትም የፊውዳሉ ስርዐት ቁንጮዎቹ ናቸው። አብዮት ካካሄድን 43 ዓመታት በኋላ በኤኮኖሚው፣ በዲሞክራሲያዊ መብት፣ በማሕበራዊ ሕይወት የተሻሉት እጅግ በጣም የተሻሉት አፄ ኃይለሥላሴ ሆኑ እኮ። ሀቁ ይሄ ሆኖ ከንጉሶቹ የተሻለ ነገር የፈጠርን ይመስል “ፈላጭ ቆራጭ ንጉሶች” ብለን ንጉሶቹን ለመዝለፍ የሞራል ብቃት አለን ወይ? በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ሲሯሯጡ ጉድጓድ እየገቡ የሞቱትን ጨምረን በየሰልፉ “እገሌ ለምን ለምን ሞተ በኃይል በትግል ነው ነፃነት የሚገኘው” እያልን ኩዴታ ሞክሮ፣ ብዙ ሰው ገድሎ፣ በፍርድ የተገደለውን ሁሉ ጨምረን በጣታችን እንቆጥራቸው አልነበረምን? ደርግ የገደላቸውን ለመቁጠር ስንት ወር ይፈጅብሀል? ኧረ እየተስተዋለ!
የኔ መልስ  ደግሞ እነሆ:-
እዚህ ጥያቄው የሞራል ጥያቄ አልመሰለኝም። የታሪክ ጥያቄ ነው! የሞራል ጥያቄ ሆኖ ለመቅረብም ከተሞከረ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረውን ህጸጽ ለመናገር የሞራል ብቃት ያለኝ ይመስለኛል። ዋናው መሠረቱ የፈጠራ፤የጥላቻ ወይንም ታሪክን አለማወቅ ወይም ለማዛባት እንዳይሆን መንጠንቀቁ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ነገሥታት ፈላጭ ቆራጭ ነበሩ። አንዳንዶቹስ የበለጠ ፈላጭ የበለጠ ቆራጭ ነበሩ። ቁጥራቸው ጥቂት ደህናዎቹም ነበሩ። ለዚህ ሁለት ምሳሌ ለመስጠት የአጼ ናኦድን እንውሰድ። በላዩ-ላይ ጨው ነስነሰውበት፤ ጉድጓድ አስቆፍረው፤ ሰው ከእነነፍሱ አስቀበረው ከብት አስነድተዋል። ይህን የሚሉት ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ ናቸው። ዐጤ ምንሊክ የሚለውን መጽሐፋቸውን ማንበብ ነው። አጼ ቴዎድሮስ ምን ምን ሰሩ ለሚለው፤ ባለታሪካዊነታቸው አንደተጠበቀ ሁኖ የ Rubinson Acta Ethiopica ማንበብ ነው። በሌላ በኩል የጋሞ ካዎ ንጉስ የመፍለጥ የመቁረጥ ስልጣን የለውም። ያ ነገር በባህሉም ውስጥ የለም። አገር የሚተዳደረው ሕዝብ በመረጠው ኃላቃና ሁዱጋ በሚባሉ ነው። ዛሬም! እነዚህም ተመራጮች በየአመቱ መስከረም ላይ ይለወጣሉ። መስከረም የጋሞ አዲስ አመት ነው። ካው በዚህ በዘመኑ አነጋገር ሕገመንግስታዊ ንጉስ (Constitutional Monarch) ልንለው እንችላለን። ወደ ኃይለ ሥላሴ ዘመን እንመለስ የሚሉ እዚህ አሜሪካ መጽሐፍ የጻፉም አሉ። ንጉስ እፈልጋለሁ፤ ለዚያውም ኃይለሥላሴን የመስለ አይገኝም ማለት የፖለቲካ እምነት ነው። እዚያ ውስጥ አልገባም። ለያንዳንዱ እንደ ምርጫው! ለኔ ማንም ቢሆን ኃይለሥላሴ ጥሩ ነበሩ ብሎ ሊነግረኝ አይችልም! የተጻፈውም ታሪክ አይልምና! ቢያንስ የአቶ ተክለጻድቅ መኩሪያንና የፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያትን የቅርብ መጽሐፍት ማንበብ ገላጭ ይመስለኛል። እኒህ ጸሐፊዎች ኃይለ ስላሴን በቅርብ የሚያውቁ፣ አብረው የሰሩ ናቸው። ከዚያም በላይ ኃይለሥላሴ ጥሩ አለመሆናቸውን በአደባባይ፤ፊት- ለፊት ቢሾፍቱ Fairfield ቤተ መንግስት በ1964 እኔው ነግሬአለሁ። በአደባባይ ለቴሌቪዥንም የተቀረጸ ነበር። በወቅቱ ቴሌቪዥን ትከታተል እንደሁ አይተኸው ይሆናል:: ከሬፑብሊክ ወደ ንጉሠ ነገሥት ለመሔድ መፈለግ የግል ምርጫ ነው። እዚያ ውስጥ አልገባም! ምርጫችን ግን ምክንያትና (Rational and Reasonable)ታሪክ የሚደግፈው ቢሆን ደስ ይለኛል። ሁለት ነጥብ! ማንም ንጉስ ጥሩ ነው፤ ኃይለሥላሴ ምን የመሰሉ ነበሩ ብሎ ሊነግረኝ አይችልም! የተሻለ መመኘት እችላለሁና! ሁለተኛው፤ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች አገር ነች። ፈረንጅ አገር ድረስ ለትምህርት መሔድ ከጀመርን ይኸው መቶ አመት አለፈን። እዚያው አገራችን ካለው ከሚያምረው ከሚበጀው ሥረአት ብንማርና ወደ አገር አቀፍ ደረጃ ከፍ ብናደርገው ምን ሙጉት ወስጥ የሚያስገባ ነገር አለው?
ይገርመኛል!!
****
ይኸኛው ደግሞ “ምንሊክ መጣ፣ ሔደ….. እያልን ወያኔ ድረስ ልንደርስ እንችላለን። በዚህ ዘመን ጋሞ ግብር ገበር እንጅ መንግስቱን አልገበረም። እንዳለ ነው! ይገርመኛል! ባልኩትና በተያያዙ “የመንደር ሹም ንጉሥ አይባልም” የሚልና የመሳሰሉ አስተያየቶችን እንዴት እንደ አስተናገድኩት የሚያሳይ የመስለኛል፡፡  
“ለምን ይሆን?” ይህ ጥያቄና አስተያየት የተሰነዘረው ማለቴ አልቀረም:: ግልጹና ፊትለፊት የሚታየኝ ምክንያት የአገራችንን ታሪክ አለማወቃችን ሊሆን ይችላል የሚል ነው። የማናወቀው ማወቅ አንፈልግም ብለን ሳይሆን የሚነገር ባለመኖሩ ይመስለኛል። ሁለተኛው ምክንያት ብዙዎች የሚያውቋቸው፤ ብዙዎች በስም ብቻ የሚያውቋቸው የኢትዮጵያ ንጉሥ፤ ያውም ንጉሠ ነገሥሰት ኃይለሥላሴ ነበሩ። ከ1967 ወዲህ የትላንት ታሪክ ሆኗልና ንጉሥ የሚባል ነገር ሁሉ “የትላንት ታሪክ” መስሏቸው ሊሆንም ይችላል:: አሁን ከስንት አመት በኋላ እኔ “ንጉሥ ሞቱ! መርዶ አውጡ! ስል” ቆይ እስቲ! የምን የማን ንጉስ?” የሚለው ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል። አንድ የአውዱ ተካፋይ “የማንም የመንደር  ሹም ንጉሥ ሊባል አይገባም!” ብሏል። “የጋሞ መንግሥት” ያልኩትን ያነበበ ደግሞ “መንግስት የሚባለውን ጽንሰ ሐሳብ (Concept) እንዴት አቃለህ ለሰፈር ሹም ሁሉ ሰጠህ?” አይነት አስተያየት ሰጥቷል። እውነት አላቸው! እስቲ ከፍተን ለማየት እንሞክር፡፡
ስለብዙ፤ ወይም የየመንደሩ ንጉሥ ጉዳይ እስቲ የኃይለሥላሴን ማዕረግ ከፍተን እንይ። ንጉሠ ነገሥት ይላል! የህ የግዕዝ ቃና ያለው ወደ አማርኛ ብንመልሰው፣ የንጉሦች ንጉሥ ማለት ነው። ይህም ማለት እስከ 1967  ፤ማለትም ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መስከረም  2,1967 በዘውድ መገዛትን በአዋጅ እስከፋቀው ድረስ ኢትዮጵያ የብዙ ነገሥታት አገር ነበረች ማለት ነው። እርግጥ ከላይ አንዱ፡- “እኔ የነዚህ ሁሉ የበላይ ነኝ” የሚል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት፣ የንጉሦች-ንጉሥ እንደነበረን የሚያሳይ ነው። ከፍተው ሲያዩት ግልጽነው። ዋናው ነጥብ ደፍሮ መክፈቱ ላይ ይመስለኛል።
ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ፤ በተለየም ከምንሊክ በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያ የንጉስ ነገር በአደባባይ ያለቀለት ይመስላል። ውስጥ ውስጡን የሚቆዘምበት ይመስለኛልም። ላለፈው አንድ አመት በተቀጣጠለው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ በሰሜን “አማራ”፤ በደቡቡ “ኦሮሞ” ጨምሮ “እንቅስቃሴውን እኔ ነኝ! እኛ ነን! የምንመራው!” የሚሉ፤ አንዳንድዶቹ “የFacebook አርበኞች!” የሚሏቸው፣ “ምሁራን” የሚሉትም ተከታዮቻቸው የሚያሰሙት ጩኸት፤ “የዘመነ መሳፍንት ብሎም የንግሥናና  የንጉስ  ጠረን” ያለው ይመስለኛል። ይህንን፣ ራሱን ችሎ፣ በራሱ ቦታ፣ ሌላ ቀን መመለሴ አይቀርም። ዘውዱን፤ ኃይለ ሥላሴን አወዳሽ፣ የገጠር መሬት አዋጅንና አዋጁን አረቀቁ የተባሉትን ኮናኝና ከሳሽ፣ በተለይም እዚህ አሜሪካ ባሉ “ምሁራን” መጽሐፍ ተጽፏል። እነዚህ “ምሁራን” ትላንትና ኮሚኒስትም ሆነው ስለ” ዓለም አቀፋዊነት፤ የሰውዘር ወንድማማችነትና እህትማማችነት” ሲያስተምሩን የነበሩ ነበሩ። ከአለምአቀፋዊነትእስከ ዘመነ መሣፊፍንት፤ እስከ ትልቁ ራስ አሊ፣ ያለው 150 አመት የመቶ ሜትር ሩጫ አይነት አድርገው ያዩት  መስሎ ታየኝ። የፕሮፌሰር አዱኛ ግጥም፤ ይሁነኝ በላይ የዘፈነው፤ አንዲት ኢትዮጵያዊነት የተሠረገችበት ዘፈን /ግጥም ሥሙ “ሠከን!” ነው። ጎበዝ፤ ሠከንን ማፈላለግ የሚበጅ ይመስለኛል!
የዚህ የዘውድ፤ የንጉሥ፣ ጉዳይ ከአብዮቱ ማግስት በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ተነስቶ ነበር። አንድ በየሳምንቱ በምትደረግ መለስተኛ ስብሰባ ላይ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም፤ የዚያን ጊዜ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ ወንበር ነበርና ያለውን አስታወሰኝ። ራስ ውብነህ፤አሞራው ውብነህ ተብለው የሚጠሩት፤ ጎንደር ሸፍተው ነበር።” የሳቸው መሳይ መሸፈት፣ ለስማችንም ለሥራችንም ጥሩ አይደለምና፤ የአገር ሽማግሌ ቢላክና…” የሚል ወይይት ተነስቶ ነበር። “ምን አድርጉ ነው የምትሉን!? የአገር ሽማግሌ ካንዴም ሁለቴ ላክንኮ! እምቢ አሉ! እሳቸው የሚሉት ባሪያ ነገሠ ነው! በዚህ ላይ ምን አይነት ውይይት መክፈት ይቻላል ጓደች!?” አሉ። በጥሞና! የሻምበል አለማየሁ ኃይሌ፤ የደርጉ ዋና ጸሐፊ የነበረው፤ በያዘው የማስታወሻ ደብተር ፊቱን ሸፍኖ እንባ እስኪወርደው ይስቅ ነበር። በኋላ “ምን እንዲያ ያስቅሀል?” ብለው “አልሳክ እንደሆነ ያንተ ነው የሚገርመኝ !”አለ። አለማየሁ ዩኒቨርስቲ ሆነንም ወዳጄ ነበር።
የዚህ የጋሞ ካዎ፣ “የመንደር ሹም ፣ንጉሥ ሊባል ከቶ አይገባውም!” ለሚባለው፤ ይህማ የፌዴራል አስተዳደር መሠረቱኮ ነው! የውስጥ ጉዳይ ላይ የ አካባቢው መንግስት በውስጥ ጉዳዩ ሙሉ ሥልጣን ይኖረውና  በፌደራሉ ጉዳይ የሚካፈልበትም ይበጃል። ከፍተን ስናየው ይኸው ነው! የተወሳሰበም አይመስለኝም!
“ጋሞ ገበረ እንጅ መንግሥቱ እንደጸና..!” ላልኩት ሁለት ምሳሌ ልስጥ። ጋሞ፤ ዶርዜ ተብሎ የሚታወቀው፣ በሽመና በአብዛኛው ኢትዮጵያ ተሰራጭቷል። አዲስ አበባ በተለየም ሽሮሜዳና ኮልፌ እንደ ማእከል የሚታይ ነው። የትም ይኑር የትም፣ ጋሞ መንግስት መሥሪያ ቤት፤ በተለይም ፍርድ ቤት አይሔድም። በጋሞ እምነት ፍርድ ቤት ነገር ይወስናል እንጅ ከስሩ አይፍቅም (Void)። ጋሞ ከስሩ ፍቆ ማንሳት (Void) የእምነቱ መሠረቱ ነው። ለዚህ “የዶርዜ ማርያም!” ብዬ የጻፍኩት ከአመት ይሁን ሁለት አመት በፊት ድረገጻትም ላይ ሆነ አዲስ አድማስ ላይ ወጥቷልና ቢቻል ያንን ማንበብ ነው። ጋሞ የትም ይኖር የትም የራሱን መንግስት፤ እምነትና ቅራኔ አፈታት በልቡ ቀርጾና ሰንቆ የሚዞር፤ የሚኖር ይመስለኛል።
ሁለተኛው በራሴ የደረሰ ነው። በ1983 ነሐሴ፤ የሽግግር መንግሥት የምክር ቤት አባል ሆኜ ጨንቻ ሔድኩኝ። ለአንድ ጉዳይ ከጨንቻ ወደ ምእራብ ወደ አለችው ዶኮ ማሾ ሔድኩኝ። እኔ ስደርስ ማሾ ገበያው ላይ፤ ታላላቅ ዋርካ ስር ዱቡሻ ተቀምጠው ደረስኩ። የአገር ጉዳይ እያዩ መስለኝ። መኪናየን አቁሜ ተቀመጥኩ። ከሶስት ሰአት ይሁን አራት ሰአት በኋላ የጀመሩትን ሲጨርሱ “አስፋ እንኴን ደህና መጣህ ! እንኳንም ተፈታህ!” አሉኝ “ትላንት ጨንቻ ሰው ልከን ንግግርህን ሰምተናል!”  ብለው መረቁኝ። ይህን ያመጣሁት የመንግሥት፤ የኢትዮጵያ መንግሥስት ባለሥልጣን መሆኔን ያውቃሉ። ሆኖም የዶኮ መንግስትን ሥራ ቅድሚያ ሰጥተውት ሲጨርሱ ወደኔ ተመለሱ ለማለት ኀው። መንግስት የሚለውን ከዚህ፣ ዘመኑ ከጣለብን ጭነት ፈተን ብናየው ለማለት ነው። ሕዝቡ  በፍትህ ራሱን ያስተዳድራል! መንግስት ያንን ለማጥፋት መግቢያ መውጫ ያሳጣዋል!
ለማጠቃለል
የዚህ የጋሞን “የጸብና ግጭት ማስወገድና መፋቅ(Voiding)” ጉዳይ ከተነሳ አንድ ነገር ጨምሬ ልዝጋው። ፕሮፌሰር ጁዲዝ  ኦልምስቲድ (Judith Olmstead)” A Women between Two Worlds” የሚል መጽሐፍ ጽፋለች። አንች የምለው በፈረንጅ አንቱታ ስለሌለ ብቻ ሳይሆን በእድሜም ተቀራራቢ ስለሆንን ነው። ጁድዝ ወደ ጋሞ የመጣችው የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ (Columbia University) ተማሪ እያለች ለዶክተርነትዋ የሚሆን ጥናት ለማድረግ ነበር። መጀመሪያ ዶርዜ የራስዋን ቤት ሠርታ ተቀመጠች። ዶርዜዎቹ “ዶርዜ ሚሽሬ!” ይሏታል። የዶርዜ ወይዘሮ እንደማለት ነው። ቆየት ሲል ከዶርዜ ወደ ምእራብ፤ ዲታ የሚባል አገር ሔደች። መጽሐፉ የሚያውራው የዲታን፤ የጋሞን ባህልና ታሪክ ነው። አርእስቱ የተሰጣቸው ሴት፤የካዎች እናትና አያት ሆነው ከጣሊያን ወዲህ እስከ ደርግ ዲታና ያስተዳደሩ ነበሩ። እኒህ ንግሥት፣ኦሬቴ ኦሎሎ ናቸው።
 ንግሥት፣ ኦሬቴ ኦሎሎን፣ ልጅ ሆኜ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ከቀኛዝማች ኢልታሞ ኢቻ ጋር ቤታቸውም አድረናል። ከአንዱሮ ወደ ወረዳው ከተማ ወደ ጉልታ  ስንሔድ ነበር። ኢልታሞን በትዝታ ፈለግ መጽሐፌ አንስቸዋለሁ። ጉልታ ኦራቴ ኦሎሎ ግብር ለማስግባት መጥተው ረድቻቸው ስለነበር እንደ ልጅ ልጆቻቸው ያዩኝ የነበር ይመስለኛል።
ጁዲዝ ኦልምስቲድ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተመርቃ ቦስተን ዩኒቨርስቲ (Boston University) ፕሮፌሰር ሆነች። ከዚያ ያንን ሥራ ለቃ የራሱን የግጭት አስወጋጅ ኩባኒያ  (Conflict Resolution)ቶኮማ ዋሽንግቶን (Tokoma ,Washington) አቋቋመች። ግጭት የማስወገዱ መንገድና ዘዴ በታወቀው በአሜሪካን  መንገድ አይደለም። ዶርዜ ሚሺረ የመረጠችው የጋሞን መንገድ ነበር። አንድ ጋሞ ከህፃንነቱ ጀምሮ፤ ሴት ወንድ ሳይል የማስታረቅ፣ የማቀራረብ መርህ ተክትሎ፤ ተግባራዊም ያደርጋል! ትላላች።
A Women between Two Worlds ስለ ኢትዮጵያ ከተጻፉ ጥቂት ከማክብራቸው መጽሐፍት ውስጥ እመድበዋለሁ። ቢቻል በየዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያ  ቢሆን የሚመረጥ ይመስለኛል። “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ በምንሊክ ከተወረረ በኋላ ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ያየዋል? ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ምን መስዋእተነት ከፈለ ?” ለሚባለው መሠረታዊ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ይመስለኛል። በተለይም ዛሬ፤ ቀየነት፤ መንደረተኛነት  እንዲህ በተጧጧፈበት ዘመን “እስቲ ሠከን በሉ!” ለማለት የሚያገልግል መጽሐፍ ይመስለኛል::
ንግሥት እለኒ፥ እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ አንጻር ቢታይም ወጥ አንጸባራቂ ከዋክብት(Shining Stars) ነበሩ። የሴት ነጻነት፤ የሴት እኩልነት( Women’s Liberation Movement) እንኳንስ ሊዘመርለት ባልታለመበት ዘመን፣ የሴቶች ነጻነትና እኩለነት መሪዎች የነበሩ ናቸው።
ስለ ንግሥት እለኒ አንድ ፓርቱጋላዊ የአይን ምስክር የጻፈውን መጽሐፍ ወንድሜ፤ እሸቱ ጫቦ፤ ከእንግሊዝ አገር ልኮልኝ ነበረ። ጸሐፊው እለኒን ማክበር ብቻ ሳይሆን ሊያመልካት ይቃጣዋል። አንዱ ሊያነበው ወስዶ ጣለብኝ። ያነበበው አልመሰለኝም! መውሰዱንም አላስታወሰምና! ስለእትጌ ጣይቱ Empress Taytu And Menilek II: Ethiopia, 1883-1910 By Chris Prouty Chris Prouty የጻፉትን ማንበብ ነው። እንደመጣሁ እኒህን ደራሲ ሴት ወይዘሮ  Chris Prouty አግኝቼ፣ አብረን አምሸተናልና ኩራት ይሰማመኛል። ዓለም ፀሐይ ወዳጆ Maryland ,Silver Spring (አገር ማርያም የብር ምንጭ) የጣይቱ ማእከል በሚባል የሚታወቀውን መሰባሰቢያ የሰየምኩት በዚህ መጽሐፍና በኝህ ሴትዮ ምክንያት ነው ብላኛለች::
ለኦራቴ ኦሎሎ እንዳልኩት የዶርዜ እሽሬን  A Women between Two Worlds ማንበብ ነው። ኦርቴ የወጡት ተራራ፤ የወረዱት ገደላገደል ከእሌኒም ከጣይቱም የሚርቅ ይመስለኛል። አጋንኜ ሊሆን ይችላል! አንብቦ መፍረድ ነው!
እሌኒ ሐዲያ ነበሩ። ጣይቱ ኦሮሞ ናቸው፦ ኦርቴ  ጋሞ ናቸው። ኢትዮጵያችን ደግሞ ይህንንም ትመስላለች!
የካዎ አለማየሁ አርሼን ዜና ዕረፍት ለመዘከር መነሻ ምክንያት (Original Reason) ማቱኬ አጆ ነች። የኔ ካዎ ሳይሆኑ የሷ ነበሩ። ማቱኬም ቢሆን የምታውቃቸው አይመስለኝም። ገና ልጅ እያሉ ጨንቻ ገብታ ቀልጣ የቀረች ነበረች። እኔ ከናቴ ወገን የማውቀው አንድ እህቷን፤አሊሴ አጆንና ባሌቤተዋን ላጬ ላካን ብቻ ነበር። ገና ልጅ ሆኜ ጨንቻ መጥተው ነበር። ጥጥ፤ሙዝ፤የበቆሎ እሼት ሌላም የማላስታውሰውን ጭነው ነበር የመጡት። ጨንቻ ደጋ ነውና ይህ ለደገኛ ብርቁ ነበር።
አያቶቼን፤ በሁለቱም ወገን ለማየት አልታደልኩም። ሐብቴ ግን ሁሉንም አይቷቸዋል። ወንድ አያቴ አጆ አሻ አሞ፣ ሴት አያቴ ዶይኬ ዶላ ይባሉ ነበር። በዚህ በተገኘው አጋጣሚ ይህ ለነሱም ከሁሉም በላይ ግን ለማቱኬ መዘከር ይሁንልን።
ቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ፤ ሕግ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበርኩ ጊዜ ግርግዳ ላይ ይሁን የሆነ ቦታ(ተረስቶኛል) ተለጥፎ ያነበብኩት ትዝ የሚለኝ “ኩሎ አመክሩ! ወለዘሠናየ አጽንኡ!” የሚል ነበረ።” ሁሉንም ዳስሱ! የሚያምረውን፤ የሚበጀውን ጨብጡ!” እንደማለትነው
የሚያምረውን፤ የሚያዋጣውን፤ የሚበጀውን  ፈላጊ ያደርገን!

Read 985 times