Sunday, 18 December 2016 00:00

የአገር ተስፋና አደጋ፣ በቁጥሮች ይታያል! ይደበቃል

Written by  ዮሃንስ . ሰ.
Rate this item
(5 votes)

 1. አገር ተሻሽሎ እንደሆነ ለማወቅ፣ የልጆችን ቁመት መለካት፣ ጥሩ ዘዴ ነው።
  • ከ15 ዓመት በፊት ከነበሩት ልጆች ይልቅ፣ የዛሬዎቹ ልጆች በቁመት ይበልጣሉ?
  • ከመቶ ህፃናት መካከል፣ የ60 ህፃናት ቁመት “ከደረጃ በታች” ይሆን ነበር። ዛሬስ?
2. የዶላርን ምንዛሬ ማስተካከል፣ ለመንግስት እንደ እሬት ይመረዋል። ለምን?
  • የመንግስት የውጭ እዳዎችንና ክፍያዎችን፣ በቁጥር ብናይ፣ ነገሩ ይገባናል።
  • የዶላር ምንዛሬ በ5 ብር ቢስተካከል፣ ለመንግስት የ5 ቢ. ብር ወጪ ይሆንበታል።
3. የኢትዮቴሌኮም የአምስት ዓመት ቁጥሮች፣ ችግርን ያሳያሉ፤ መፍትሄውንም!
  • የሞባይል መስመር በእጥፍ ጨምሯል፤ ከ20 ሚሊዮን ወደ 45 ሚሊዮን።
  • ከውጭ የሚደወል የስልክ ጥሪ ብዛት በግማሽ ቀንሷል፤ ከ200ሚ ወደ 100ሚ።
4. የስራ አጥነት ችግርን የሚደብቁ “የምናብ” ቁጥሮች፣ አገርን ለቀውስ ያጋልጣሉ።
  • በ2002 ዓ.ም፣ በከተሞች የነበረው የስራ እድል 5 ሚ ሰዎችን የሚያስተናግድ ነበር።
  • ከዚያ ወዲህ 12 ሚ. አዲስ የስራ እድል ተፈጥረዋል። ወደ 17 ሚ. አድጓል ማለት ነው?
  • የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ግን፣ ህፃን አዋቂው ሁሉ ተቆጥሮ፣ 14 ሚሊዮን ነው።

      ብሔራዊ ባንክ፣ ሰሞኑን፣ ፈካ ደመቅ የሚያደርጉ የቁጥር መረጃዎችን በዝርዝር አቅርቦልናል - በ116 ገፅ ባዘጋጀው ዓመታዊ ሪፖርቱ። የኢትዮቴሌኮም ገቢ እና ወጪ፣ የነዳጅ ግዢና ዋጋ፣ የገንዘብ ዝውውርና የእህል ምርት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን... በየአመቱ ከዳያስፖራ የሚመጣ የዶላር ብዛት... ብዙ ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ ሪፖርት ነው። ነገር ግን፣ እውነት ሊሆኑ የማይችሉ፣ መረጃዎችንም ያካትታል - በስራ እድል ፈጠራ የተንበሻበሹ የህልም አለም ከተሞችን እንደማስጎብኘት ቁጠሩት።
ታዲያ፣ የልጆችን ቁመት የሚያነፃፅር መረጃ፣ ከብሄራዊ ባንክ ለማግኘት እንዳትጠብቁ። ግን ችግር የለውም። የዛሬዎቹንና የድሮዎቹን ልጆች፣ ቁመትና እጥረታቸውን በንፅፅር ለማየት ከፈለግን፣... የስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣ ከሰሞኑ ያቀረበውን አዲስ የጥናት ሪፖርት መቃኘት እንችላለን።

ኑሮ ሲለካ፣ ቁመት ነው ለካ!
የቁመት ልዩነት፣ በድሮና በዘንድሮ ላይ ብቻ አይደለም። ከቦታ ቦታ፣ ከከተማ ከተማም ይለያያል። ገምታችሁ ይሆናል። የአዲስ አበባ ህፃናት፣ በአመዛኙ... በአብዛኛው... በቁመት ከሌሎች ይበልጣሉ። ግን፣ የአዲስ አበባ ኑሮ ከሌሎች ልቆ ተሻሽሏል ማለት አይደለም። የወሊድ ብዛት ወይም የህፃናት ቁጥር በአዲስ አበባ አነስተኛ መሆኑን እናስታውስ። ሦስት አራት ህፃናትን ከማሳደግ ይልቅ፣ ሁለት ህፃናትን ማሳደግ ቀለል ይላል። በቂ ምግብና እንክብካቤ ደግሞ፣... ከእድገትና ከቁመት ጋር የተያያዘ ነው።
ከመቶ ዓመት በፊት የቻይናዊ ወጣት አማካይ ቁመት፣ 162 ሴንቲሜትር ነበር። የኢትዮጵያዊ ወጣት አማካይ ቁመትም፣ ተመሳሳይ ነበር። የዛሬ ሃምሳ ዓመትም ቁመታቸው ተቀራራቢ ነበር - 168 ሴሜ። ከዚያ ወዲህ ግን፣ ተለያይቷል። ከቻይና ተነጥላ፣ ቶሎ ወደ ብልፅግና የገሰገሰችው ታይዋን ውስጥ፣ ዛሬ የወጣቶች አማካይ ቁመት 175 ሴሜ ነው። ቻይና ውስጥ ደግሞ 172 ሴሜ፤ የኢትዮጵያዊያን ግን አልተሻሻለም። “ኑሮ ሲለካ፣ ቁመት ነው ለካ!” ያስብላል።
ለማንኛውም፣ ሰሞኑን የወጣው የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጤና-ነክ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ ህፃናት ኑሮ፣ ለእድገት አመቺ አይደለም። ከመቶ ህፃናት መካከል፣ የ45ቱ ቁመት ከ‘ደረጃ በታች’ ነው። የእድሜያቸው ያህል በቁመት አይመነደጉም። እንዲያም ሆኖ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።
ከ15 ዓመት በፊት፣ ከመቶ ህፃናት መካከል፣ 60 ያህሉ፣ ለእድሜያቸው የሚመጥን ቁመት ላይ ለመድረስ አይችሉም ነበር።    
 
በስራ እድል የተንበሻበሹ ከተሞች!   
ብሔራዊ ባንክ በየዓመቱ እንደሚያደርገው፣ ዘንድሮም ብዙ የስራ እድል እንደተፈጠረ ገልጿል። በ2008 ዓ.ም ብቻ፣ ለዚያውም በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አማካኝነት ብቻ፣ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ስራ እድል እንደተፈጠረ ብሔራዊ ባንክ ገልጿል - መረጃውን ከከተማ ልማት ሚኒስቴር እንዳገኘ በመጥቀስ። ካቻምና ደግሞ 2.8 ሚሊዮን የስራ እድሎች። ከዚያ በፊትም እንዲሁ ሁለት ሚሊዮን ተኩል የስራ እድሎች።
ምናለፋችሁ? በ2003 ዓ.ም እና ከዚያ ወዲህ ባሉት አመታት፤ 9.5 ሚሊዮን አዳዲስ የስራ እድሎች እንደተከፈቱ፣ በአመታዊ ሪፖርቶቹ ዘርዝሯል። ታዲያ ይሄ እልፍ አእላፍ የስራ እድል፣ በየከተማው የተፈጠረው፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ብቻ እንደሆነ ልብ በሉ። በኢንቨስተሮችና በመንግስት ፕሮጀክቶች አማካኝነት፣ በኢትዮጵያ ከተሞች የተፈጠሩ የስራ እድሎች ሲጨመሩበት፣ ከ12 ሚሊዮን እንደሚበልጥ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ሪፖርቶች ይገልፃሉ።
ከምር፣ ሪፖርቶቹ፣ ልብን ወከክ ያደርጋሉ። ይሄ ሁሉ ሰው፣ አዳዲስ የስራ እድል እያገኘ፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ከዳር ዳር፣ በተስፋ ከመፍካት አልፈው፣ በእድገትና በብልፅግና ጎዳና፣ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሱ እንደሆነ ያሳያሉ - ሪፖርቶቹ ውስጥ የምናያቸው ቁጥሮች። አገር አማን ነው፤ አማን ብቻ አይደለም፤ መትረፍረፍ፣ መንበሽበሽ ነው... ደስታ ነው... ስኬት ነው!
ነገር ግን፣ ደስታው የምናብ ደስታ፣ ከተሞቹም የምናብ ከተሞች ናቸው።
እውነተኛዎቹን ከተሞች በእውን እናውቃቸዋለን። በስራ አጥነትና በኑሮ ቅሬታ፣ አምና ሲታመሱና ሲናጡ የከረሙ ከተሞችን ማለቴ ነው።
የምናብ ከተሞቹ የተፈጠሩት፣ በምናባዊ ቁጥሮች ምክንያት ነው። በየአመቱ በአማካይ 2 ሚሊዮን አዳዲስ የስራ እድል የሚፈጠርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች፣ የምናብ ከተሞች ናቸው። ቁጥሮቹ... የእውነት ቁጥሮች ሊሆኑ አይችሉማ። ነባርና አዳዲስ የስራ እድሎች ሲደማመሩ፣... በቃ የሰራተኛው ቁጥር፣ ከህዝቡ ቁጥር የሚበልጥ ይሆንብናል።
የከተማ ልማት ሚኒስቴር ሪፖርቶች ላይ የተዘረዘሩትን ቁጥሮች ትተን፣  ሌሎች ሪፖርቶችን መመልከት እንችላለን። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ሪፖርቶችን!

እውነተኛዎቹ ከተሞች
በ2002 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ከተሞች የህዝብ ቁጥር፣ 10.4 ሚሊዮን ነበር። በ2008 ዓ.ም፣ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር፣ 14 ሚሊዮን በላይ ሆኗል። በ3 ሚሊዮን ተኩል ጨምሯል ማለት ነው። ግን ሁሉም ነዋሪ፣ ሰራተኛ ወይም ስራ ፈላጊ አይደለም። ገሚሶቹ ገና ህፃናት ናቸው፣ ገሚሶቹ ታዳጊ ተማሪዎች ናቸው። እድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ የሆናቸውና የመስራት ዓቅም ያላቸው ነዋሪዎችን ብቻ እንመልከት።
ለአቅመ ስራ የተደረሱት የከተማ ነዋሪዎች፣ በ2002 ዓ.ም ቁጥራቸው ስንት ነበር? “6 ሚሊዮን ነበር” ብሎ ይመልሳል - የስታትስቲክስ ባለስልጣን። ከእነዚህ መካከልም፣... ደሞዝተኛው፣ ባለሃብቱ፣ ነጋዴው፣ አናጢው፣ የቤት ሰራተኛው፣ ሱቅ ውስጥ እየተላላከ ያለደሞዝ ቤተሰቦቹን የሚረዳ ወጣት... ይሄ ሁሉ ተቆጥሮ፣ 5 ሚሊዮን ያህሉ ነዋሪ፣ “ሰራተኛ ነው” ተብሎ ተቆጥሯል።
እሺ፣ ወደ 2008 ዓ.ም ተሸጋገር ደግሞ እንይ። ህፃናትን ትተን፣ ለዓቅመ ስራ የደረሱት የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር፣ ስንት ደረሰ? 9 ሚሊዮን ገደማ ሆኗል። ከእነዚህ መካከልም፣ 7.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች፣ ተለቀም አነሰም፣ ከባድም ይሁን መናኛ፣ ስራ አላቸው ይላል - የስታትስቲክስ ባለስልጣን ሪፖርት።
በ2002 ዓ.ም በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ከነበረው 5 ሚሊዮን የስራ እድል ጋር ስናነፃፅረው፣ በ2.5 ሚሊዮን ይበልጣል። በቃ፣ ባለፉት ስድስት አመታት የፈጠረ የተጣራ የስራ እድል፣ 2.5 ሚሊዮን ነው።
የከተማ ልማት ሚኒስቴር እንደሚለው፣ በስድስት ዓመት ውስጥ፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የስራ እድሎች ቢፈጠሩ ኖሮ፣ ከነባሮች የስራ እድሎች ጋር ሲዳመር፣ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰራተኞች ያስፈልጉ ነበር። በከተሞቹ ውስጥ ያለው የነዋሪዎች ቁጥር ግን፣ ህፃን አዋቂው ሁሉ ተቆጥሮ 14 ሚሊዮን ብቻ ነው። ህፃናቱን ስንቀንሳቸውና፣ የመስራት አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ብቻ ሲቆጠሩ ደግሞ፣ 9 ሚሊዮን ብቻ ናቸው። በከተሞቹ ውስጥ ያለውና የተፈጠረው የስራ እድል ግን 17 ሚሊዮን?
ቁጥሮች፣ እውነታን ለመለካት ሳይሆን፣ ምናባዊ አለምን ለማሳመር የምንጠቀምባቸው ከሆን፣ ያው... ከእውነት ጋር ያራርቀናል፣ ከእውነት ጋር አጣልቶ ያጋጨናል። ምናባዊዎቹ ከተሞች በምናባዊ ቁጥሮች ተምበሽብሸው ሲንቆጠቆጡ እያየን ራሳችንን የምናታልል ከሆነ፣ ከዚህ ቅዠት ለመባነን ድፍረት ካጣን፣ ፈጠነም ዘገየም፣ ድንገት ከድንዛዜ መንጭቆ የሚያወጣና እያንገራገጨ ከእውነታ ጋር የሚያጋጭ ቀውስ አያጠራጥርም። በኑሮ ቅሬታና በስራ አጥነት ሳቢያ የተቃወሱ የአገራችን ከተሞች ባለፈው አመት አገሪቱን ምንኛ እንዳንገራገጯት አይተን የለ!
የቴሌኮም ቁጥሮችና ፈተናዎች
ስራ ላይ የዋሉ የሞባይል ስልክ መስመሮች፣ በአምስት አመታት ከእጥፍ በላይ እንደጨመሩና 45 ሚሊዮን እንደደረሱ ይገልፃል - የብሄራዊ ባንክ ሪፖርት። የአገር ውስጥ የሞባይል ጥሪዎችም ተበራክተዋል። በየእለቱ የሚስተናገዱት የሞባይል ጥሪዎች፣ 35 ሚሊዮን ነበር - ከአምስት አመት በፊት። ዛሬ 75 ሚሊዮን ደርሷል። በአመት 27 ቢሊዮን ጥሪ።
ለኢትዮቴሌኮም፣... ገበያ ደርቶለታል ማለት ነው። ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነለት ከመሰለን ግን ተሳስተናል። ሌሎች ቁጥሮችን ተመልከቱ። በተለይ ደግሞ፣ ዋና የገቢ ምንጭ የሆኑት የውጭ ጥሪዎችን።
ከሁለት ዓመት በፊት፣ 45 ሚሊዮን ወደ ውጭ የተደወሉ ጥሪዎችን አስተናግዷል። አምና ግን፣ 37 ሚሊዮን ጥሪዎች ብቻ ነው ያስተናገደው። ዋናው ግን ይሄ አይደለም።
ከውጭ የሚደወሉ ጥሪዎች መቀነሳቸው ነው፣ ለቴሌ የራስ ምታት የሚሆንበት። የዛሬን አያድርገውና፣ በ2005 ዓ.ም ኢትዮቴሌኮም፣ ከውጭ የተደወሉ 210 ሚሊዮን ጥሪዎችን አስተናግዷል። አምናስ? የጥሪዎቹ ቁጥር በግማሽ ገደማ ቀንሰዋል - ወደ 110 ሚሊዮን። ያው፣ የቴሌ ገበያ የሚለካው፣ በጥሪዎች ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በደቂቃው ብዛትም አይደል? በ2005 ዓ.ም ከውጭ በተደወሉት ጥሪዎች፣ የ800 ሚሊዮን ደቂቃ ገበያ አስገኝተውለት ነበር። የአምናው ሲታይ ግን ከ400 ሚሊዮን ደቂቃ በታች ሆኖበታል።
የቴሌኮም ቴክኖሎጂና ቢዝነስ፣ ምንኛ በፍጥነት እየተለዋወጠ እንደሆነ፣ ከቁጥሮቹ መመልከት ይቻላል። ከድሮው የሞባይል ጥሪ ይልቅ፣ በፌስቡክ መልእክት የሚለዋወጥ እንዲሁም እንደ ቫይበር በመሳሰሉ የኢንተርኔት የስልክ ጥሪዎች እየተገናኘ የሚያወራ ተበራክቷል። ይሄ ለኢትዮቴሌኮም ከባድ ፈተና ነው። ቁጥሮቹ ይመሰክራሉ።
የቁጥሮች አገልግሎት የዚህን ያህል ትልቅ ነው። ምናባዊ አለምን ለመፍጠር ሳይሆን፣ እውኑን አለም ለማሳየትና ለማገናዘብ ከተጠቀምንባቸው፣ ችግሮችን በጊዜ አውቆ መፍትሄ ለማፈላለግ ይረዳሉ - እውነተኛ ቁጥሮች። እንግዲህ፣ ኢትዮቴሌኮምም፣ ካሁን በፊት የውጭ የማኔጅመንት በኮንትራት በማስመጣት ችግሮችን ለመፍታት ሞክሮ የለ? ዛሬም ተጨማሪ ሙከራዎችና ጥረቶች እንደሚያስፈልጉ ከቁጥሮቹ በማየት፣ መፍትሄዎችን ማፈላለግ ይጠበቅበታል - በተለይ ደግሞ፣ የቴሌኮም ቢዝነስን ወደ ግል ኩባንያዎች የማስተላለፍ መፍትሄ!   

እድገት በኤክስፖርትና በውጭ እዳ?
ኤክስፖርት፣ በ2000 ዓ.ም እና በተከታዩ ዓመት፣ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ነበር። በ2002 ግን ማደግ ጀመረ። በ2004 ዓ.ም ወደ 3 ቢሊዮን ደርሷል። ከዚያ ወዲህ ግን አላደገም። እንዲያውም ቀንሷል - በ100ሚሊዮን ዶላር።
ለምን? የአለም የሸቀጦች ገበያና ዋጋ አንዱ ምክንያት ቢሆንም፣ የዶላር የምንዛሬ ቁጥጥር ዋናው መንስኤ ነው። ከፍተኛ የምንዛሬ ማሻሻያ የተደረገው በ2002 ዓ.ም ነው። 13 ብር ይመነዘር የነበረው አንድ ዶላር፣ 16 ብር እንዲሆን ተደረገ። ኤክስፖርተሮች፣ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሸቀጥ ኤክስፖርት ያደረገ ነጋዴ፣ በ13 ሚሊዮን ብር እንዲመነዝር ይገደድ ነበር። በ16 ሚሊዮን ብር እንዲመነዝር ተፈቀደለት። በዚህም፣ ብዙ አምራቾችና ነጋዴዎች፣ ኤክስፖርት ለማሳደግ ቢነሳሱ ምን ይገርማል? ግን ብዙም አልዘለቀም።
በየአመቱ በገንዘብ ህትመት ሳቢያ፣ የብር ዋጋ በፍጥነት እየረከሰ መጥቷል። ነገር ግን፣ ይህንን የሚያካክስ በቂ የምንዛሬ ማስተካከያ አልተደረገም። የአለም ባንክ እና የአለም ገንዘብ ድርጅት በተደጋጋሚ እንደሚገልፁት፣ የዶላር ምንዛሬ ከአራት ብር እስከ ሰባት ብር የሚደርስ ማስተካከያ ያስፈልገዋል። ግን፣ መንግስት፣ እንዲህ አይነት ከፍተኛ የምንዛሬ ማስተካከያ እንዲደረግ ፈቃደኛ አይደለም። ለምን? “የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር እሰጋለሁ” የሚል ምክንያት ሊሰጥ ይችላል።
ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነው። አብዛኛው የውጭ ምንዛሬ፣ ወደ መንግስት እጅ እንደሚገባ አንሳ። ቢያንስ ቢያንስ፣ በየአመቱ የውጭ እዳ ለመክፈል ብቻ፣ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል። ለዚህም፣ አሁን ባለው ምንዛሬ፣ ኤክስፖርተሮች አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት፣ 22 ቢሊዮን ብር ያወጣል። ምንዛሬው በአምስት ብር ቢሻሻል ግን፣ የመንግስት ወጪ ወደ 27 ቢሊዮን ብር ያሻቅባል። 5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ማለት ነው! ይህንን ወጪ ለማስቀረት፣ ምን ይደረግ? የዶላር ምንዛሬ፣ በአግባቡ እንዳይስተካከል መገደብ ነዋ! ኪሳራው የኤክስፖርተሮችና የአምራቾች ይሆናል።
ችግሩ ምንድነው? ኤክስፖርተሮችና አምራቾች ይዳከማሉ። በሌላ አነጋገር፣ የዶላር ምንዛሬ በአግባቡ ካልተሻሻለ፣ የኤክስፖርት ምርት ማደግ አይችልም። ላለፉት አራት አመታት እንዳየነው፣ እዚያው ባለበት እየረገጠ የድንዛዜ አዙሪት ውስጥ ይገባል። የዶላር ምንጭ ይደርቃል።         

Read 2597 times