Sunday, 18 December 2016 00:00

ራሷ ሰቅላው ራቀ፣ ራሷ ጋግራው ሊጥ ሆነ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ገጣሚ ደበበ ሰይፉ የሚከተለውን ፅፎ ነበር፡፡ መነሻው ተረት ነበርና አመቻችተን እንደ ተረት ተጠቅመንበታል፡፡
በተረት ላሰላስል
መሬትና ጥንቸል ማኅበር ገቡና
ጽዋ ተጣጡና፤ …
ያጋጣሚ አይደለም፤
የተፈጥሮ ባህል፣ የታሪክ ዘይቤ፣ አለው አንድ ቋንቋ፣
አለው አንድ መላ
አንተና ልደትህን፣ አንተና አገርህን
በማይረግብ ገመድ፣ ባንድ ላይ የቋጨ፣ ከአፀደ ዘመን?
ከቦታ ከለላ
በደም ቃልኪዳኑ ባንድ ያስተሳሰረ፣ በማይታይ እጆች
ባልተሰማ መሀላ፡፡
… እና፣
መሬትና ጥንቸል ማኅበር ገቡና
ጽዋ ተጣጡና፣ …
መሬት የፈንታዋን ስትከፍል በጽሞና፤ …
እብስ አለች ጥንቸል፣ መክፈል ጠላችና
እና፣
… በስንት ትላንትና፣ ዘንቦ ወይ ፀህይቶ
በቁር ተኮራምቶ፣ በዋዕይ ገርጥቶ
የበቀለ ዛሬ፣
ትውልድም ነውና፣ ያያት የቅድመ - አያት
የእንዝላ የእንጅላት  
የመሰረት ፍሬ፣
በሺ እግሮች ተራምዶ፣ ዛሬን የደረሰ፣ ለእሱ እሱነቱ
በወቅቱ ለወቅቱ
ይኖር ወይ ደካማ፣ የትውልድ እንክርዳድ
አደገኛ አዝመራ ከዚህ ከወጣቱ?
ማነው ይህ መጢቃ፣ የፀደይ ቀን ዘመድ
ወጪቱን እሚሰብር፣ ዕዳውን እሚክድ
ከወገኑ እማይቆም፣ ከወገኑ እማይነድ?
የጫጨ መንፈሱ፣ የሸፈተ አሳቡ፣ የከነፈ ልቡ
ራሱ መነሻው፣ ደሞ ራሱ ግቡ?
እና፤ …
መሬትና ጥንቸል፣ ማኅበር ገቡና፣ ፅዋ ተጣጡና
መሬት የበኩሏን ስትከፍል በጽሞና
እብስ አለች ጥንቸል፣ መክፈል ጠላችና፣ …
ግና ምን ይሆናል?
ብትሮጠው ብትሮጠው፣ ጋራውን ተሻግራ፣
ሜዳውን አቋርጣ
አልቻለችም ከቶ፣ ከዕዳዋ ልትድን፣
ከመሬት አምልጣ፡፡
(1974)
*      *     *
የመሬትን ዕዳ ሳንከፍል አናመልጥም፡፡ መሬት የአገር ነው፡፡ ብዙ ጥንቸሎች ከመሬት ጥቅም አጋብሰዋል። የአገር ዕዳ አለባቸው፡፡ የትም ቢሮጡ አያመልጡም፡፡ አገር በዐይነ ቁራኛ ታያቸዋለች፡፡ እጃቸው ንፁህ አይደለምና ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ነው!
ክፈሉ ስንባል የማንከፍለውን ጥዋ አለመጠጣት አስተዋይነት ነው፡፡ አቅም ይፈቅዳል የምንለውን እንጂ ግብረ አበራችንን ዝቅ አድርገን የምንሄደበት መንገድ፣ የኋላ ኋላ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ “የሸክላ ድስትና የብረት ድስት ወዳጅነት” ከባድ የመንኮታኮት ውጤት እንደሚኖረው ደራሲ ከበደ ሚካኤል ገና በተማሪነት ዕድሜያችን አስገንዝበውናል፡፡ ያም ሆኖ ትንሽ፤ ትልቅ ለመሆን አይጣጣር ማለት አይደለም፡፡ አድጌ እዚህ እደርሳለሁ የማይል፣ የግቤ መጨረሻ ይሄ ነው የማይል፣ ተስፋ መቁረጥ ነው ውጤቱ! ያልነቃ መንፈስ፣ ያልነቃ ድርጅታዊ መሪ፣ ያልነቃ ተቋማዊ አስተዳዳሪ፣ ያልነቃ ዜጋ፤ ለዕድገት ደካማ ጎን ነው! መንቃት ሲባል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ዕውቀታችንን የማዳበር ጉዳይ ነው፡፡ ሳናውቅ ያወቅን እንዳይመስለን፣ ደግ ሳንሆን ደግ ነን እንዳንል፣ ዲሞክራሲ ሰፈር ሳንደርስ ዲሞክራሲያዊ ነን ብለን ጉራ እንዳንነዛ፣ ከወገናዊነት ሳንላቀቅ ስለ ፍትሐዊ አካሄድ በየደረስንበት እንዳናወጋ፤ ጠቃሚው መላ በንባብ፣ በውይይት፣ በተግባር ልምድ በማበልፀግ፣ ከስህተት በመማር፣ ራሳችንን ማረቅ፣ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለትን መተው ነው፡፡
በሀገራችን እጅግ ጠቃሚ ፋይዳ ያለውና ሳናደርገው የቆየን አንድ ታላቅ አላባ (element) መልካም የሰራን ዋጋ የመስጠት፣ የማድነቅ፣ ጮክ ብለን አዎንታዊ ሙገሳን ለማሰማት የመድፈር ባህል፤ አለማዳበራችን ነው፡፡
“ሌላ ባላውቅ የራሴን ዋጋ አቃለሁ” ይላል እያጎ፡፡ ሼክስፒር፣ መሠሪውን እያጎን እንኳ የራስ ዋጋን ስለማወቅ ሰባኪ አድርጎታል፡፡ ምነው ቢሉ፣ ለማንም ቢሆን ለማን፣ የራሱ መለኪያ አለው! የራስን ዋጋ ማወቅ፣ ራስን ከማወቅ የሚመነጭ ነው! ሁኔታውን እንደ መንግስት ስናሰላው፤ ከየት መጣሁ፣ ለምን መጣሁ፣ ወደየት እሄዳለሁ፣ ምን ዕቅድ አቅጃለሁ? በምን እተገብረዋለሁ? በዚህ ዕቅዴ ተግባራዊነት አነማን አጋሮች አሉኝ? ምን ያህልስ ዝግጁ ናቸው? ብሎ መጠየቅ ዓይነተኛ ግንዛቤ መጨበጥን የሚያሳይ ማፀሕያ ነው! ራስን ለመገምገም መነሻው ይሄ ነው፡፡ ማቀድ፣ መተንተን፣ ተግባራዊነቱን መቆጣጠር፣ ፍፃሜውን መከታተልና ውጤቱን መገምገም… የማናቸውንም ስራ ሂደት ፍሬ ነገር መጠቅለያ ነው!
ማናቸውም አዲስ ሹም፤ የራሱን ብቃትና ህልውና ለማረጋገጥ፤ ከሱ ቀደም የነበረውን ሹም ጥፋትና ድክመት በመጥቀስ እወደዳለሁ፣ ክህሎቴንም አረጋግጣለሁ ብሎ ባያስብ መልካም ነው! ይሄ ባህል፣ ማለትም ጥፋትን ሁሉ በቀደሙት ሹማምንት ላይ ማላከክ የቀደሙትን ማውገዝ እጅግ የተሳሳተ መርህ ነው! ህዝብም ይሄን ዘዴ ተረድቶ በመንገኝነት መንገድ ውስጥ ለመጓዝ፣ ለመንገድ መዘጋጀት የለበትም! ይልቁንም ስላለፉት ሹማምንት ውግዘት ከማዳመጥ፣ የራስህን ብቃት አረጋግጥ ማለትን ዋና ጥያቄው ማድረግ አለበት፡፡ መፍጠር ያለብን ጠያቂ ማህበረሰብ (Inquisitive Society) ነው፡፡ ህብረተሰብ፤ ከወጣው መመሪያ፣ አዋጅ፣ መርሀ ግብር ጋር ራሱን አዋህዶ ያይ ዘንድ የማወቅ መብቱን መጠቀም፣ ለምን? እንዴት? ማለት፤ ካልጣመውም እምቢ ማለትን መልመድና መቀበል አለበት፡፡ ግልፅነትና ተጠያቂነት ከዚህ ሂደት የሚመነጩ ናቸው፡፡ የምንሾማቸውን ባለስልጣናት በጥንቃቄና በሚዛናዊ ብስለት መሾም ኋላ ከሚመጣ ስህተትና ፀፀት ያድነናል። ከዚህ ቀደም የፈፀምነው የማመዛዘን፣ ስህተት ኖሮ ከሆነም፣ ከዚያ መማር ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ራሷ ሰቅላው ራቀ፣ ራሷ ጋግራው ሊጥ ሆነ… የሚለው ተረት ዕውን ይሆናል፡፡

Read 6021 times