Sunday, 18 December 2016 00:00

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቤተ-መፃህፍት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ-መፅሀፍት ኤጀንሲ፤ የንባብ ባህልን ለማዳበርና ለውጥ እንዲመጣ በማሰብ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ተንቀሳቃሽ ቤተ መፅሀፍትን ለመክፈት ባቀደው መሰረት  ከአንድ ወር በፊት በአምስት የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመጀመሪያዎቹ ቤተ መፅሀፍቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ቤተ-መፅሀፍቱን እንዴት ተቀበሉት ምን አይነት መፅኀፍትን አካትቷል፣ እነማን ናቸው እየተጠቀሙት ያሉት፣ አገልግሎት አሰጣጡስ ምን ይመስላል በሚሉትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ባልደራስ ኮንድምኒየም አካባቢ ከሚገኘው የካ ሳይት 1 ተገኝታ ከሳይቱ ህብረት ስራ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ
ከሻምበል ዮሴፍ ሂሌሎ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡

       ተንቀሳቃሽ ቤተ-መፅሀፉ መቼ ነው የተከፈተው? እንዴትስ ተከፈተ?
ቤተ መፅሀፉ ከመከፈቱ በፊት እኛ የተናጋገርነው ከብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ ጋር ነበርን፡፡ በንግግራችን ኤጀንሲው ቤተ-መፅሐፍቱን ለምን ዓላማ መክፈት እንዳሰበ በደንብ አስረዳን፣ ደስም አለን፡፡ ከዚያም እድሉን ካገኙ አምስት የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል የኛ ሳይት አንዱ ሆኖ ባለፈው ጥቅምት 28  ተከፈተ፡፡ እኛም ሰራተኛ ቀጥረን አገልግሎት ጀመርን ጀምረናል፡፡
በቤተ መፅሀፍቱ ምን ያህል መፅሀፍት ይገኛሉ?ሰ አይነታቸውስ?
በውስጡ 158 ዓይነት መፅሀፍት ይገኛሉ። የሰጠን ኤጀንሲው ነው፡፡ የታሪክ፣ የልብወለድ፣ የፖለቲካ፣ የትምህርት መረጃና ማጣቀሻ፣ የግጥምና በርካታ አይነት መፅሀፍት ይገኛሉ፡፡ ከመፅሐፍት ውጭ ጋዜጦ መፅሄቶች በየሳምንቱ ከኤጀንሲው ይላክልናል፡፡
ተጠቃሚ በምን መልኩ ነው አገልግሎት የሚያገኘው?
ማንኛውም ወደ ቤተ-መፅሀፍቱ የሚመጣ ሰው፤ መታወቂያውን ለቤተ መፅሀፍቱ ሰራተኛ ካሰረከበ በኋላ የፈለገውን መፅሀፍ እዚያው በተከለለው ቦታ ቁጭ ብሎ ያነብና ይመልሳል፡፡ ለጊዜው ያሉን መፅሀፍ አነስተኛ በመሆናቸው ማዋስ አልጀመርንም። ምክንያቱም አንዱን መፅሀፍ አንድ ሰው ወደ ቤቱ ይዞ ከሄደ ሌላ የሚመጣ ሰው የሚያነበው ያጣል፡፡ አገልግሎቱ በነፃ ነው የሚሰጠው፡፡ ተገልጋይ ምንም የሚከፍለው ነገር የለም፡፡
በአሁን ሰዓት የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው በደንብ እየተጠቀመ ያለው?
በአሁን ወቅት በጣም እየተጠቀሙ ያሉት ህፃናትና ተማሪዎች ናቸው፤ አዋቂዎች በአብዛኛው ስራ ውለው ደክሟቸው ስለሚመለሱ አይጠቀሙም። አዋቂዎች አልፎ አልፎ ብቻ ነው እያነበቡ የሚሄዱት፡፡
በእናንተ ሳይት ውስጥ ምን ያህል ሰው ነው የሚገኘው?
በዚህ ግቢ ውስጥ ዘጠኝ ብሎኮች ሲኖሩ፡፡ 251 አባወራ ይገኝበታል፡፡ እንግዲህ እያንዳንዱ አባወራ በስሩ ምን ያህል ሰው አለ የሚለውን ለማወቅ ገና መቁጠር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ታዲያ አንድ ተንቀሳቃሽ ቤተ- መፅሀፍትን ለ251 አባወራ በቂ ነው ይላሉ?
ከምንም በጣም ይሻላል፡፡ ምንም የሌላቸው አሉ እኮ፡፡ ወደፊት ኤጀንሲውም ውጤታማነቱን እያየ የሚጨምር ይመስለኛል፡፡ እስካሁን ሰው መጥቶ መፅሀፍ አንሶ ወይም ቦታ ጠቦት የተመለሰ የለም፡፡
ብዙ ጊዜ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በግርግርና በጩኸት የተሞሉ ናቸው ይባላል፡፡ ቤተመፅሀፍቱ መተላለፊያ መንገድ ላይ እንደመሆኑና የተከለለ ባለመሆኑ ንባብ አይረብሽም?
በሌሎች አካባቢዎች ያለውን እርግጠኛ ባልሆንም በእኛ ግቢ የፀጥታ ችግር እስካሁን አላጋጠመም፡፡ በአብዛኛው በራሱ ቤት የሚኖር፣ ጠዋት ወጥቶ ማታ ከስራው የሚመለስ ነዋሪ ነው ያለው፡፡ በጥበቃም በኩል የተጠናከረ አሰራር ነው ያለን፡፡ መኪኖች የነዋሪው ካልሆነ በስተቀር ሲገቡም ሲወጡም ይፈተሻሉ፡፡
በአጠቃላይ ግቢው ፀጥታ የሰፈነበት፣ በአረንጓዴ ዕፅዋት የተሞላና ነፋሻማ በመሆኑ ለንባብ ይጋብዛል። አልተከለለም ለተባለው ትክክል ነው፤ ወደፊት ቦታው ሰፋ አድርገን የመከለል ሀሳብ አለን፡፡ አሁን ስለ ቤተ-መፅሀፍቱ ለሰዎች  ግንዛቤ እየፈጠርን ስለሆነ፣ የግቢው ነዋሪዎች መፅሀፍት እየለገሱን ነው፡፡ ሌላዋ የግቢያችን ነዋሪ፤ አሁን ህፃናቱ የሚቀመጡባቸውን 15 የፕላስቲክ ወንበሮችና ክብ ጠረጴዛ ገዝተው ለግሰውናል፡፡ በአጠቃላይ የግቢውም የቤተመፅሀፍቱም አካባቢ ከረብሻና ከሁከት የፀዳና ሰላማዊ ነው ሰዎችም ላይብረሪውን ለማበረታት ነው እየለገሱን ያሉት፡፡
ከሳይቱ ነዋሪ ውጭ ሰዎች መጥተው መጠቀም ይችላሉ?
በትክክል! ማኝኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው፤ መታወቂውን እያስያዘ፣ መፅሀፍትን አንብቦ መሄድ ይችላል፡፡ እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቢኖሩም ኤጀንሲው ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገው በአምስት ሳይቶች ላይ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባልደራስ አለ፣ የካ ሳይት ሁለት አለ፡፡ በርካታ ነዋሪ በአካባቢያችን ስለሚኖር ማንኛውም ሰው መጠቀም ይችላል፡፡
በቀጣይ ምን ያሰባችሁት ነገር አለ?
እንግዲህ ሰው በብዛት እየመጣ ማንበብ ቢጀምር ምን ማድረግ አለብን የሚለውን አስበናል። በቀጣይ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ፈልገን፣ ገንዘብ ካገኘን ቦታውንም ቤተ-መፅሀፍቱንም የማስፋት እቅድ አለን፡፡ አሁን አሁን ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ አንድ ግለሰብ የማተምያ ማሽን ሲለግሰን፣ አንዲት የግቢው ነዋሪ 60 መፅሀፍትን ሰጥታናለች፡፡ ሌላው ደግሞ የህፃናት ወንበሮችና ጠረጴዛ እንደለገሰችን ገልጨልሻለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን በርካታ መፅሀፍትን ካገኘን፣ መፅሀፍት በማከራየትና የራሱን ገቢ እንዲፈጥር የማድረግ እቅድ አለን፡፡
እንዲህ አይት ቤተ-መፅሀፍት መከፈታቸው ለውጥ ያመጣል ብለው ያስባሉ?
በጣም ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት አለን፡፡ ምክንያቱም ኤጀንሲውም የንባብ ባህልን ለማዳበር ነው ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ ያደረገው፡፡ በሌላ በኩል፤ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንይውሉ ያደርጋል፡፡ ብዙዎች እንዲህ አይነት ጠቃሚ ቦታዎችን በማጣት ወደ ወንጀለኝት፣ ወደ ሱሰኝነትና ወደ አላስፈላጊ ተግባራት ይሰማራሉ፡፡ እንዲህ አይነት አማራጮች መኖራቸው የንባብ ባህልን ከማዳበር ባለፈ ወጣቶችን ከአጉል ባህሪያት ይታደጋል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ትልቅ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ። አሁንም ወጣቶች የታሪክ፣ ልብ ወለድና እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ መፅሀፍቶችን ማንበብ ጀምረዋል፤ ይሄ የለውጡ መጀመሪያ ነው፡፡
ኤጀንሲው ቤተ-መፅሀፍቱን ካቋቋመ በኋላ፤ የቁጥጥር ስራዎችን እየመጣ ይሰራል ወይስ…?
እስካሁን ከእናንተ ውጭ የመጣ የለም፡፡ በእርግጥ ከኤጀንሲው ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን የምንፈልገውን በስልክ እንጠይቃለን፡፡ እነሱም በየሳምንቱ የሚወጡ የህትመት ውጤቶችና አዳዲስ መፅሀፍትን ይልካሉ፡፡
ሳይልኩ ሲቀሩ እንጠይቃለን እንዲህ እንዲህ ገጥሞን ነው፤ በቀጣይ እንልካለን ይላሉ ባሉት ጊዜም ይልካሉ፡፡ እስካሁን በተደረገልን ቀና ትብብር ኤጀንሲውን እናመሰግናለን፡፡

Read 1649 times