Sunday, 18 December 2016 00:00

ሩት ነጋ፤ ለጎልደን ግሎብ በምርጥ ተዋናይት ታጭታለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የ2017 የጎልደን ግሎብ ሽልማት ዕጩዎች ይፋ ተደረጉ
      ለ2017 የጎልደን ግሎብ ሽልማት በዕጩነት የቀረቡ ፊልሞች፣ የፊልም ተዋንያን፣ ዳይሬክተሮች፣ ፕሮዲዩሰሮች፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና አከፋፋይ ኩባንያዎች ዝርዝር ባለፈው ሰኞ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ “ላቪንግ” በተሰኘው ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የሰራቺው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የፊልም ተዋናይት ሩት ነጋ፣ በምርጥ ሴት የድራማ ፊልም ተዋናይ ዘርፍ ለሽልማት ታጭታለች፡፡
ኢትዮ-አይሪሽ ዜግነት ያላት ሩት፣ በጄፍ ኒኮላስ ዳይሬክት በተደረገው “ላቪንግ” የተሰኘ የድራማ ዘውግ ያለው የፍቅር ፊልም ላይ ባሳየቺው የትወና ብቃት ለጎልደን ግሎብ የታጨች ስትሆን ለሽልማቱ መታጨቷ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባት  መግለጧን አይሪሽ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ በዘንድሮው የጎልደን ግሎብ ሽልማት፣ “ላ ላ ላንድ” የተሰኘው ፊልም ምርጥ ዳይሬክተር፣ ምርጥ ወንድ ተዋናይና ምርጥ ሴት ተዋናይን ጨምሮ፣ በተለያዩ ሰባት ዘርፎች ለሽልማት መታጨቱን ያስታወቀው የሆሊውድ ፎሪን ፕሬስ አሶሴሽን፤ “ሙንላይት” በስድስት ዘርፎች፣ “ማንችስተር ባይ ዘ ሲ” በአምስት ዘርፎች መታጨታቸውንም ገልጧል፡፡  
ለ74ኛው የጎልደን ግሎብ ሽልማት በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ ከታጩት ቶም ፎርድና ኬኔዝ ሎኔርጋን “ጌም ኦፍ ትሮንስ”፣ “ዌስትዎርልድ”፣ “ዘ ናይት ኦፍ” እና “ኢንሴኪዩር” እያንዳንዳቸው 14 ጊዜ በመታጨት ቀዳሚነቱን መያዛቸው የተነገረ ሲሆን  በፊልም አከፋፋይ ኩባንያዎች ዘርፍ “ሰሚት ኢንተርቴንመንት” 10 ጊዜ በመታጨት ቀዳሚነቱን ሲይዝ፣ “ኤ24” 9 ጊዜ፣ “ፓራማውንት ፒክቸርስ” ደግሞ ለ8 ጊዜ በመታጨት ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልሞች ዘርፍ “ዘ ፒዩፕል ቨርሰስ ኦ ጄ ሲምሰን” ለ5 ጊዜ በመታጨት በአንደኛነት ሲቀመጥ፣ “ዘ ናይት ማናጀር” ለ4 ጊዜ፣ “ብላኪሽ” ደግሞ ለ3 ጊዜ በመታጨት ይከተላሉ፡፡ የ2017 የጎልደን ግሎብ ሽልማት ስነስርዓት በመጪው ጥር መጀመሪያ፣ በቤቨርሊ ሂልተን ሆቴል የሚከናወን ሲሆን በኤንቢሲ ቴሌቪዥን በኩል በቀጥታ ለተመልካቾች እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

Read 1173 times