Sunday, 18 December 2016 00:00

ሃሪ ፖተር በዓመቱ የመጽሐፍት ሽያጭ ቀዳሚ ሆኗል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  መጽሐፉ በህጻናትም፣ በአዋቂዎችም ዘርፍ አንደኛ ደረጃን ይዟል
     የአለማችን ቁጥር አንድ የድረገጽ የሽያጭ ተቋም አማዞን፣ በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2016፣ በብዛት ከተሸጡ ምርጥ 20 መጽሐፍት መካከል የታዋቂዋ ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ ስራ የሆነውና የሃሪ ፖተር ተከታታይ መጽሐፍት የመጨረሻው ክፍል፣ “ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ከርስድ ቻይልድ” ቀዳሚውን ስፍራ መያዙን አስታውቋል፡፡
“ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ከርስድ ቻይልድ” የሚል ርዕስ ያለውና በቲያትር ስክሪፕት መልክ የተዘጋጀው ይህ ተወዳጅ ስራ፣ በአመቱ በአማዞን በኩል በብዛት ከተሸጡት 20 ምርጥ መጽሃፍት መካከል በህጻናትም በአዋቂዎችም ዘርፍ ቁጥር አንድ ስፍራን ይዟል ብሏል - አማዞን፡፡ መጽሃፉ ለገበያ ከመብቃቱ ከወራት በፊት አንስቶ በርካታ የግዢ ትዕዛዝ በመቀበል ክብረወሰን መስበሩን ያስታወሰው አማዞን፤ በቲያትር መልክ ተዘጋጅቶ በለንደን ቲያትር ቤቶች እጅግ በርካታ ቁጥር ባላቸው ተመልካቾች እየታየ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
በአማዞን የአመቱ ምርጥ ሽያጭ ያስመዘገቡ የአዋቂዎች መጽሃፍት ዝርዝር ውስጥ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው በፖል ካላኒቲ የተጻፈው “ዌን ብሪዝ ብካምስ ኤር” የተሰኘ መጽሐፍ ሲሆን  በታዋቂው ደራሲ ጆን ግሪሻም የተጻፈው “ዘ ዊስትለር” ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ በህጻናት መጽሐፍት ዘርፍ ደግሞ “ዲያሪ ኦፍ አ ዊምፒ ኪድ፡ ደብል ዳውን” የተሰኘው የጄፍ ኬኒ መጽሐፍ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ በሪክ ሪዮርዳን የተጻፈው “ዘ ትሪያልስ ኦፍ አፖሎ፣ ቡክ ዋን - ዘ ሂድን ኦራክል” በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

Read 1797 times