Sunday, 18 December 2016 00:00

በፋይናንስ ዘርፍ ኢትዮጵያ ዝግ ናት ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ዘርፍ ራሷን አግልላና በሯን ዘግታ መቆየቷን የአንደኛው ዓመታዊ የምሥራቅ አፍሪካ ፋይናንስ ሰሚት ተሳታፊዎች አስታወቁ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ‹‹ቢዩልዲንግ ኮምፕቴቲቭ፣ ኮኦፕሬቲቭ ኤንድ ኢኖቬቲቭ ፋይናንስ ሴክተር ኢን ኢስት አፍሪካ፤ ኤንፌሲስ ኦን ኢትዮጵያ›› በሚል ጭብጥ ባዘጋጀውና በኢሲኤ  አዳራሽ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ አስተያየት ሰጪዎች፤ ‹‹የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ከተቀረው ዓለም ራሱን የከለለና የተዘጋ ስለሆነ ይህ ጉባኤ ለእኛ ዓይን መክፈቻ ነው›› ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የሕብረት ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ ዛፉ፤ ‹‹የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ የተዘጋ ነው፤ አሁን ባለንበት የዕድገት ደረጃ ሁሉም ነገር በኢትዮጵያ ድንበር ተከልሎ ነው ያለው፡፡ ዘርፉ ከውጪው ዓለም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ ኩባንያዎቻችን ከሚወዳደሩባቸው ገበያዎች ከመጡ ባለሙያዎች ጋር መወያየታችን ለእኛ ዓይን መክፈቻ ስለሆነ፣ እኔ በጣም ጠቃሚ የውይይት መድረክ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ እንደታሰበው የሚቀጥል ከሆነ ጥሩ ፕሮጀክት ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹ዘመኑ የለውጥና  ግሎላይዜሽን ነው፤ ለውጥ መቆም የማይችል ሂደት ነው፡፡ እኛም በምሥራቅ አፍሪካ የኮሜሳ አባሎች ነን፡፡ በመካከላችን ንግድና ኢንቨስትመንት ማካሄድ፣ እየተካሄደም ከሆነ ማስፋፋት፣ የየአገሮቹ ትልቅ ግብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን ከሌሎቹ አገሮች በፋይናንስና በቴሌኮም ዘርፍ  በጣም ጥብቅ የመከላከል ዝንባሌ (ፕሮቴክቲቭ አቲትዮድ) ነው ያላት፤ የፋይናንስ አቅምና እውቀት እስክናዳብር ድረስ ፕሮቴክት ማድረጉ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በጣም ለብዙ ዘመን ሲቆይ ጥሩ አይደለም፤ ወደ ‹‹ፕሮቴክቲቪዝም›› ይሸጋገራል፡፡ ስለዚህ ከጎረቤት አገሮች ከመጡ ሰዎች ጋር መገናኘትና እነሱ ዘንድ ምን እየሆነ ነው?... ምንድነው የሚያስቡት? የሚለውን ማወቅ እጅግ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ከአቶ ዛፉ በመቀጠል ከአሜሪካና ከጀርመን የመጡ የዘርፉ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በዓለም ያሉ አዳዲስ ሐሳቦችና አዳዲስ ሲስተሞችንም አስተዋውቀውናል፡፡ እዚህ ሆነን ከእነሱ እየተማርንና እነሱም ስለእኛ እያወቁ ነው፡፡ መማማር ማለትኮ ዓይን መግለጥ ማለት ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ፤ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስትቲዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ገመቹ፤ የመጀመሪያው ዓመታዊ የምሥራቅ አፍሪካ ፋይናንስ ሰሚት ሐሳብ አፍላቂና የአዘጋጅ ኮሚቴው  ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ የአንድን አገርና፣ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ማሻሻል፣ ቢዝነሱን ማሳደግ ከፈለግን፣… ዋናውን ሚና የሚጫወተው የፋይናንስ ዘርፉ ነው ይላሉ፡፡
ሊቀመንበሩ፤ ጉባኤውን ለማዘጋጀት ምክንያት የሆናቸውን ሲጠቅሱ፤ ኢትዮጵያ በአካባቢው አገሮች መጫወት የምትፈልገውን ሚና ለመወጣት ከዓለም አቀፉ ደረጃ ጋር ሲነፃፀር፣ የፋይናንስ ዘርፉ በፋይናንሻል ኢኖቬሽን፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል አጠቃቀም፣ ቴክኖሎጂ መግዛት ብቻ ሳይሆን ለተገዛው ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ያለችበት ደረጃ ምን ይመስላል? ሌላው ዓለም ካሽ ወደ ማይጠቀም ማኅበረሰብ ለመፍጠር ሲጥር ኢትዮጵያስ? ከሁሉም በላይ ደግሞ የአዕምሮ ዝግጁነት አለ ወይ? የሚል ጥናት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ የሁሉም ጥናቶች ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን አይኤምኤፍ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያደረጉት  ጥናት ያመለክታል፡፡ የእኛስ ድርሻ ምን መሆን አለበት? በማለት ሲጠይቁ፤ የፋይናንስ ዘርፉ ወሳኝ ሚና ያላቸውን ባለድርሻ አካላት አንድ ላይ ሰብስበው፣ ርዕሶች ቀርፀው ለመወያየት፣ ከዚያም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት የሚመለከተውን ይዞ ይሂድ የሚል ሐሳብ  አይ ካፒታል አመነጨ፡፡ ተባባሪዎቹ የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቢዝነስ ኢንተርፕራይዝ ሐሳቡን ወደዱት፡፡
ዋነኛው ዓላማ በሁሉም የፋይናንስ ዘርፎች ያሉ ፖሊሲ አውጪ፣ የቢዝነስ መሪዎች፣ አማካሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች አንድ ላይ አምጥቶ፣ በጋራ ችግሮቻቸው ላይ እንዲወያዩ ማድረግ ነው፡፡ የመወያያ ጭብጡ፡- ተወዳዳሪ፣ መተባበር የሚችልና የፈጠራ ዝንባሌ ያለው የፋይናንስ ዘርፍ መፍጠርና ማሳደግ እንደሆነ ገልጸዋል- ዶ/ር ገመቹ፤ ሁለተኛው ዓላማ መድረኩ ከተፈጠረ በኋላ ምን ትምህርት ነው ይዘን የምንሄደው? ለፖሊሲ ግብአት የሚሆን ምን እንውሰድ? ለኢንዱስትሪው ደግሞ አሠራራችንን ለማሻሻል የሚረዳን ምንድነው? ዩኒቨርስቲዎችም ለምርምር የሚረዳቸው ምን ይዘው ይሂዱ?... የሚል ነው፡፡
ሦስተኛ ዓላማ፡- ከስብሰባው የተገኙ ትምህርቶችን ወደየመጡበት ተቋም ይዞ ሄደ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ የመጨረሻው ነጥብ፤ በመጪው ዓመት ሲገናኙ የቤት ሥራ ይዘን ሄደን ነበር፡፡ ምን ውጤት ተገኘ? በሚለው ነጥብ ላይ መነጋገር ነው በማለት ዶ/ር ገመቹ አስረድተዋል፡፡

Read 1238 times