Sunday, 18 December 2016 00:00

“ኢዮሃ የገና ኤክስፖ” ዛሬ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይመንትና ኤቨንትስ ያዘጋጀው ‹‹ኢዮሃ የገና ኤክስፖ” ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይከፈታል፡፡ ለ21 ቀናት በሚቆየው በዚህ ኤክስፖ ላይ ከ450 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች እንደሚሳተፉና በቀን ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይመንትና ኤቨንት ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አዩ ዓለሙ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ከ50 በላይ አንጋፋና አዳዲስ ድምፃዊያን እንዲሁም ስድስት ታዋቂ ባንዶች ለቀጣይ 21 ቀናት ኤክስፖውን እንደሚያደምቁ የተገለፀ ሲሆን ዲጄ ሊ፣ ዲጄ ሚኪና ዲጄ ሄኖክም ጎብኚውን በሙዚቃ ያዝናናሉ ተብሏል፡፡ በየቀኑ የዳንስ ውድድር፣ የባለ ዕጣዎች ሽልማትና የሙዚቃ ድግስ በሚካሄድበት በዚህ ኤክስፖ፣ 1ኛ ለሚወጣ የመኪና ለሁለተኛው ባለዕድል ደግሞ የሞተር ሳይክል ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ ዛሬ በሚካሄደው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሶበች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙ ሲሆን ከ8-10 ሰዓት ለሚገቡ ጎብኚዎች የመግቢያ ክፍያ እንደማይጠየቅም ተገልጿል፡፡ ኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይመንትና ኤቨንት ባለፈው ዓመትም የገናንና የፋሲካን ኤክስፖ በ22.5 ሚሊዮን ብር አሽንፎ በተሳካ ሁኔታ ከማካሄዱም በላይ የቀይ መስቀል 80ኛ ዓመት በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን አሸንፎ ማዘጋጀቱ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮም የገናን ኤክስፖ በ17.6 ሚ. ብር፣ የፋሲካን በ13.6 ሚ ብር ያሸነፈ ሲሆን ከፋሲካ ቀጥሎ ሌላ ኤክስፖ ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ መሆኑን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡ የመግቢያ ዋጋ እንደወትሮው 15 ብር መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1181 times