Sunday, 18 December 2016 00:00

ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ የካርቶን ምርት ለገበያ አቀረበ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

አምና፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ደረጃ ፋሺን እሆነ የመጣውን አዲስ ዓይነት ሮዝ የወይን ጠጅ ለገበያ አቅርቦ በደንበኞቹ ዘንድ ተወዳጅነት ማግኘቱን የጠቀሰው ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ፣ አሁን ደግሞ አዲስ የአኬሽያ የካርቶን ወይን ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
ወይን ጠጅ ፋብሪካው ከትላንት ወዲያ አዳዲሶቹን ምርቶች በራማዳ አዲስ ሆቴል ባስተዋወቀበት ወቅት የካስቴል የወይን ጠጅ ፋብሪካ የሽያጭና የማርኬቲንግ ኃላፊ ወ/ት ዓለም ፀሐይ በቀለ፣ አዲሶቹ ምርቶች ከአሁን ቀደም ከውጭ አገር ተገዝተው የሚገቡትን የካርቶን ወይን ጠጆች በመተካት የውጭ ምንዛሪ እንደሚያድኑ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የካርቶን ወይኖች ተከፍተው ጥራታቸው ሳይቀንስ ብዙ ጊዜ መቆየትና በብርጭቆ ተቀድተው መቅረብ ስለሚችሉ በሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ተወዳጅ እንደሆኑ የጠቀሱት ወ/ሪት ዓለምፀሐይ፤ አሁን በሁለት ሊትር ተኩል ለገበያ የቀረቡት ነጩና ሮዙ ወይን መሆናቸውን፣ ከሦስት ወር በኋላ ደግሞ ጠንካራውንና (ድራይ) መካከለኛውን (ሚዲየም) ቀይ ወይኖች ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
በሁለት ብራንድ ስሞች፡- አኬሽያ እና ሪፍት ቫሊ 10 ዓይነት የወይን ጠጅ ምርቶች እንደሚያቀርቡት የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ “በአሁኑ ወቅት የአኬሽያ ካርቶንና የጠርሙስ ወይን ይኖረናል፡፡ ወደፊት የገበያውን ፍላጎት አይተን ሪፍት ቫሊዎቹንም በካርቶን ልናቀርብ እንችላለን” ብለዋል፡፡
ካስቴል ወይን ጠጅ፣ በወይን ጠጪ አገራት ተወዳጅነት ማግኘቱንና ኢትዮጵያንም በዓለም የወይን አምራች አገሮች ካርታ ውስጥ እንድትሰፍር ማድረጉን፣ ምርታቸውን ወደ 11 አገራት እንደሚልኩና የገበያ ድርሻቸውም 11 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በ162 ሄክታር መሬት ላይ በ2001 ዓ.ም የወይን እርሻ የጀመረው ካስተል ወይን ጠጅ ፋብሪካ፤ በ2007 ምርት መጀመሩን፤ በአሁኑ ወቅት በ82 ሄክታር መሬት ላይ ማስፋፊያ እየሰራና ዓመታዊ ምርቱ 1.4 ሚሊዮን ጠርሙስ እንደሆነ፣ ለ850 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ወይን፣ ምርትና አቅርቦቱ ብቻ ሳይሆን መስተንግዶውም በትክክል መታወቅ አለበት ያሉት ወ/ሪት ዓለምፀሐይ፤ ወደ አገራችን የሚመጡ ቱሪስቶች ለሚከፍሉት ገንዘብ ተመጣጣኝ መስተንግዶ ስለማያገኙ ደስተኞች አይደሉም፡፡ የአገራችንም ህዝብ ወይን ራሱን የቻለ መስተንግዶ እንዳለው ማወቅ አለበት፡፡ እኛም እንደ አንድ ወይን አምራች ድርጅት ሚናችንን መወጣት አለብን። አስተናጋጆች አንዱ ወይን፣ ከሌላው በምን እንደሚለይ፣ የእያንዳንዱ የወይን ዓይነት የቅዝቃዜ መጠን ምን መሆን እንዳለበት፣ የትኛው የወይን ዓይነት ከሚመገቡት ምግብ ጋር እንደሚስማማ ለደንበኞቻቸው እንዲነግሩ፣ ወይን እንዴት እንደሚከፈት፣ እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸውም … ማወቅ አለባቸው፡፡
እስካሁን ስናደርግ የነበረው ወደ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች እየሄድን ለአስተናጋጆች ስለ ወይን ምንነት ስልጠና ሰጥተናል፣ ከአምስት የመስተንግዶ ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር እየሰራን ነው፡፡ 400 የመስተንግዶ ሰራተኞች ፋብሪካው ወደሚገኝበት ዝዋይ ወስደን የምርት ሂደቱን እንዲከታተሉ አድርገናል፡፡ ይህ ሁሉ በቂ ሆኖ አላገኘነውም። ስለዚህ፣ በስልጠና ያገኙት እውቀት አብሯቸው እንዲቆይናየወይን መስተንግዶን ለማሻሻል ዲቪዲ አዘጋጅተን ለሁሉም አስተናጋጆች ለማከፋፈል ዝግጅት አጠናቅቀናል በማለት አስረድተዋል፡፡

Read 914 times