Sunday, 18 December 2016 00:00

‹‹ማይ ባብ›› እና የቻይናው “ክሎው” ቆጣሪና የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ለመምራት ተስማሙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  የጁፒተር ትሬዲንግ እህት ኩባንያ “ማይ ባብ ኤሌክትሮኒክስ” እና የቻይናው “ክሎው” ኩባንያ በአገራችን የመብራት ቆጣሪና የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ለማምረት ከትላንት በስቲያ ካዛንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ስምምነት ተፈራርመዋል። ሳህሊተ ምህረት አካባቢ በተሰጣቸው 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ለሚገነባው ፋብሪካ 4 ሚሊዮን ዶላር መመደቡ የተገለፀ ሲሆን የቻይናው “ክሎው” 30 በመቶ፣ “ማይ ባብ ኤሌክትሮኒክስ 70 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ተናግሯል፡፡
ፋብሪካው በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት፣ ለ100 ሰራተኞች የስራ እድል በመፍጠር፣ 300 ሺህ የመብራት ቆጣሪዎችን ለማምረት ማቀዱ የተገለፀ ሲሆን፣ በቀጣይ ሁለት ዓመታት የሰራተኞቹን ቁጥር ወደ 250 በማሳደግ፣ በሶስት ፈረቃ ለመስራትና የማምረት አቅሙን ወደ 900 ሺህ ከፍ ለማድረግ ማቀዱን የኩባንያው ሀላፊዎች ገልፀዋል፡፡
የቆጣሪዎቹ በአገር ውስጥ መመረት ከከተማ ቤቶች ግንባታ መስፋፋት ጋር እያደገ የመጣውን የኤሌትሪክ ሀይል አቅርቦት ለማገዝና ለቆጣሪ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማዳኑም በላይ ለውጭ ገበያም በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ለመሳብ ያለመ እንደሆነ የ“ማይ ባብ” ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የቻይናው “ክሎው ከሌሎቹ” ኩባንያዎች የተመረጠበትን መስፈርት አቶ መላኩ ሲያስረዱ፤ “ክሎው” ቻይና ውስጥ ከሚገኙ ሶስት ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች አንዱ በመሆኑ፣ ኩባንያው ምርቶቹን ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ እስያና አፍሪካ በመላክ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ በመሆኑና ከቻይና ውጭ (በጋና፣ ናይጄሪያ፣ በግብፅ፣ በባንግላዲሽ፣ በኢንዶኔዢያ ፋብሪካዎችን ከፍቶ በጥራት ከማምረቱም ባሻገር ከ“ማይባብ ጋር ለመስራት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል፡፡
ኩባንያዎቹ የመብራት ቆጣሪዎቹን በጥራትና በብዛት ከማምረትም ባሻገር የአገሪቱን የታክስ አሰባሰብ ስርዓት ለማገዝ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም ማሰባቸውንና ለዚህም 1.5 ሚ ዶላር መመደቡን አስታውቀዋል፡፡
ኩባንያዎቹ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ለውጭ አገራት ገበያ ቆጣሪዎችንና የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖችን በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከአገር ውስጥ ገበያ ዋና ደንበኛቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን መሆኑን የገለፁት አቶ መላኩ፤ ሁለቱም ምርቶች አገራዊ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ እንደሆነና ለዜጎች በርካታ የስራ እድል መፍጠራቸውንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

Read 523 times