Sunday, 18 December 2016 00:00

የጋምቢያው መሪ “ምርጫው ይደገም፤ የ22 አመት ስልጣኔን አለቅም” ብለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጃሜህ በይፋ ያደነቁትን ምርጫ በይፋ ሲክዱት፣ ፓርቲያቸው ለፍ/ ቤት አቤት ብሏል
     ላለፉት 22 አመታት ጋምቢያን አንቀጥቅጠው የገዙት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜህ፣ ከሰሞኑ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያልጠበቁት ዱብ እዳ ይዞባቸው መጣ - በተፎካካሪያቸው አዳማ ባሮው የመሸነፋቸውን መርዶ አስደመጣቸው፡፡
የምርጫው ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ከሁለት አስርት አመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆዩት ጃሜህ፤ ስልጣን እንደጣመው አፍሪካዊ መሪነታቸው ውጤቱን አልቀበልም ብለው እምቧ ከረዩ ይላሉ ብለው ብዙዎች ጠብቀው ነበር፡፡ ጃሜህ ግን፣ ባልተጠበቀ መልኩ የምርጫውን ውጤት እንደሚቀበሉ ተናገሩና፣ አገራቸውንም ዓለምንም አስገረሙ፡፡
“ምርጫው ፍትሃዊ ነበር!...” ሲሉም በአደባባይ አወጁ፡፡
በምርጫው በለስ ለቀናቸው ተፎካካሪያቸው ኣዳማ ባሮው ስልክ ደውለው፣ “ቀጣዩ የጋምቢያ መሪ በመሆንህ እንኳን ደስ አለህ!... መልካሙ ሁሉ እንዲገጥምህ እመኝልሃለሁ!... “ ሲሉ የደስታ መግለጫ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉም፣ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ለህዝብ ታዩ፡፡
የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽንም “ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ነበር” ሲል አስታወቀ፡፡
የኋላ ኋላ ግን...
ጃሜህ ነገሩን በጥሞና አጤኑት፡፡ ለቀናት ደጋግመው አሰቡበት፡፡ ጊዜ ወስደው መላልሰው አሰላሰሉት፡፡
በዚህ መሃል፣ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን፣ የጃሜህን ተሸናፊነት ባይቀይርም፣ በውጤቱ ላይ መጠነኛ የሆነ ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ጃሜህ ይህን ሲሰሙ፣ አሪፍ ማፋረሻ ሰበብ አገኙ፡፡
“እየቀለዳችሁ ነው እንዴ!?... የምን ምርጫ ነው የምታወሩት!?... የምን ስልጣን መልቀቅ ነው!?...” ሲሉ ከአንድ ሳምንት በፊት በይፋ ያመኑትን ውጤት፣ መልሰው በይፋ ካዱ፡፡ ለ22 አመታት የተቀመጡበትን መንበረ ስልጣን፣ አሳልፈው ለማንም እንደማይሰጡትም፣ በመንግስት ቴሌቪዥን መስኮት ከኮስታራ ፊት ጋር ብቅ ብለው አስታወቁ፡፡የምርጫ ውጤቱ አሸናፊነታቸውን ያወጀላቸው ባሮው በበኩላቸው፤ ጃሜህ ውጤቱን ላይቀበሉ ቢችሉም፣ እንዲሰረዝና ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ የመጠየቅ ህገ መንግስታዊ ስልጣንም ተቀባይነትም የላቸውም ሲሉ ተናገሩ፡፡
“ወታደሩም ቢሆን ከጎኔ እንደሚቆም ተስፋ አለኝ!...” ሲሉም ስጋት የወለደው አረፍተ ነገር ጣል አደረጉ፡፡
አለም ወደ ጋምቢያ እያየ በሽሙጥ ሳቀ፡፡
አለም ያሽሟጥ እንጂ፣ ጋምቢያና ህዝቦቿ ግን በውጥረት ተያዙ፡፡ ጃሜህ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለታቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ውጥረት ተከሰተ፡፡ ይህ ውጥረት ያሳሰባቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎችም፣ ጃሜህን መክረው ዘክረው የምርጫ ውጤቱን እንዲቀበሉ ለማግባባት ባለፈው ማክሰኞ ወደ ጋምቢያ አቀኑ፡፡
ያም ሆኖ ግን ያሰቡት አልሰመረላቸውም፡፡
“ወይ ፍንክች የአባ ቢለዋ ልጅ!...” አሉ ጃሜህ፡፡
ይባስ ብሎም፣ ጃሜህ የሚመሩት የጋምቢያው ገዢ ፓርቲ ኤፒአርሲ፣ ምርጫው ተዓማኒነት የጎደለው መሆኑን በመጥቀስ፣ ውጤቱ እንዲሰረዝና ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ የሚጠይቅ ማመልከቻ አርቅቆ፣ በዚያው ዕለት ለአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስገባ፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካና ሌሎች አገራት እንዲሁም ተቋማት፣ ጃሜህን “እባክዎት ይለመኑን!... ስለ ሰላም ብለው ስልጣንዎትን ይልቀቁ” እያሉ በመማጸን ላይ ናቸው፡፡
“ፕሬዚዳንት ጃሜህ ስልጣናቸውን ለአሸናፊው ባሮው ማስረከብ አለባቸው!” ብሏል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፡፡ የአፍሪካ ህብረትም የጃሜህን እምቢተኝነት፣ “ተቀባይነት የሌለው” ሲል በይፋ ውድቅ አድርጎታል፡፡
ጋምቢያ አሁንም ውጥረት ውስጥ ናት፡፡ ዜጎቿ ብጥብጥ ይፈጠራል በሚል ስጋት ተውጠዋል፡፡ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ የአገሪቱ ወታደሮችም፣ ከተሸናፊው ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜህ የተላለፈላቸውን ቀጭን ትዕዛዝ በመቀበል፣ የመዲናዋን ባንጁ ጎዳናዎች ወርረው በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡ የመንግስቱ ታማኝ ወታደሮችም፣ ባለፈው ማክሰኞ በመዲናዋ የሚገኘውን የምርጫ ኮሚሽ ቢሮ በጥብቅ ዙሪያውን ከብበዋል፡፡
የአገሪቱ ጦር ሰራዊት ለሁለት ይከፈላል፣ አገሪቱም ወደ ከፋ ብጥብጥ ልትገባ ትችላለች የሚለው ስጋት አይሏል፡፡ ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣ ጃሜህ መሸነፋቸውን በጸጋ የተቀበሉ ሰሞን የአገሪቱ የጦር ሃይል አዛዥ ኡስማን ባጄ ከተመራጩ ኣዳማ ቦሮ ጋር ተገናኝተው፣ ጦሩ ለእሳቸው እንደሚታመን ቃል ገብተውላቸው ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን፣ ጃሜህ ቃላቸውን አጥፈው ውጤቱን አልቀበልም ማለታቸውን ተከትሎ፣ የጦር አዛዡ ፊታቸውን ወደ ጃሜህ አዙረው ትዕዛዝ መቀበል መጀመራቸውን አስተዛዛቢና አደገኛ አካሄድ ብሎታል- ዘገባው፡፡ ጃሜህ ስልጣናቸውን ለማስረከብ የቀራቸው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ብቻ መሆኑን የጠቆመው ቢቢሲ፤ ገዢው ፓርቲ ምርጫው እንዲሰረዝና ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ ለፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ በአጭር ጊዜ ምላሽ የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ግጭት ሊያስከትል እንደሚችል ዘግቧል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት ክልላዊ ተቋም ኢኮዋስ ከፍተኛ ባለስልጣንም፣ ጃሜህ ስልጣኔን አለቅቅም በሚለው አቋማቸው የሚጸኑ ከሆነ፣ ተቋሙ የውጭ ወታደራዊ ሃይል የማስገባት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሆነው ሆኖ...
የአህጉሩ ትንሷ አገር ጋምቢያ፣ ትልቅ ስጋት ውስጥ ወድቃለች፡፡ የጋምቢያና የህዝቧ መጻእይ ዕጣ ፈንታ፣ አሁንም በ51 አመቱ ጃሜህ እና ጃሜህ እጅ ላይ ነው- ይላል ቢቢሲ፡፡

Read 1507 times