Sunday, 18 December 2016 00:00

የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደርሷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በመላው ዓለም 259 ጋዜጠኞች በእስር ላይ ይገኛሉ
     በተለያዩ የአለማችን አገራት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2016 ላይ  259 መድረሱን ያስታወቀው ሲፒጄ የተባለው አለማቀፍ የፕሬስ ተሟጋች ቡድን፣ የጋዜጠኞችን እስር በማጥናት ይፋ ማድረግ ከጀመረበት ከ1990 ወዲህ ከፍተኛው በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር መሆኑንም ገልጧል፡፡
ቁጥሩ ከፍተኛው ደረጃ ላይ ለመድረሱ ምክንያት የሆነው፣ የቱርክ መንግስት ባለፈው ሃምሌ ወር የተቃጣበትን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከትሎ በጋዜጠኞች ላይ የወሰደው ከፍተኛ የእስር እርምጃ መሆኑን የጠቆመው ቡድኑ፤ በተገባደደው የፈረንጆች አመት ከአለም አገራት በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ቱርክ ቀዳሚነቱን መያዟን ጠቅሶ፣ የአገሪቱ መንግስት በአመቱ ከ81 በላይ ጋዜጠኞችን ወህኒ መወርወሩን አስታውቋል፡፡
በአመቱ ከቱርክ ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የታሰሩባት ሁለተኛዋ የአለማችን አገር ቻይና መሆኗን የጠቆመው የቡድኑ አመታዊ ሪፖርት፤ በአገሪቱ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር 38 መድረሱን አመልክቶ፣ ሶስተኛ ደረጃን በያዘቺው ግብጽ ደግሞ 25 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ጠቅሷል፡፡ በመላው አለም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው 199 ዘንድሮ ወደ 259 ከፍ ማለቱን ሪፖርቱ ገልጾ፣ በእስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞች መካከል ሶስት አራተኛ ያህሉ ጸረ-መንግስት ተግባር ፈጽመዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው መሆናቸውንና ከታሰሩት 259 ጋዜጠኞች መካከል 20 ዎቹ ሴቶች እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡
በኤርትራ 17፣ በኢትዮጵያ 16 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙም ቡድኑ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

Read 1276 times