Sunday, 18 December 2016 00:00

ትራምፕን ለመግደል የሞከረው እንግሊዛዊ 1 አመት ተፈረደበት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የኢራን መከላከያ ሚ/ር፤ አለም በትራምፕ አገዛዝ ወደ ጦርነት ልትገባ ትችላለች አሉ
     ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባለፈው ሰኔ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ፕሮግራም ላይ፣ የአንድን ፖሊስ ጠመንጃ በመንጠቅ ትራምፕን ለመግደል ሞክሯል የተባለው እንግሊዛዊ ወጣት የአንድ አመት እስራት እንደተፈረደበት ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ማይክል ሳንፎርድ የተባለው የ20 አመት ወጣት፣ ለመርማሪዎች በሰጠው ቃል፤ የሪፐብሊካኑን ዕጩ ዶናልድ ትራምፕን ተኩሶ ለመግደል በማሰብ፣ ከካሊፎርኒያ በመነሳት በወቅቱ ቅስቀሳ ያደርጉበት ወደነበረው ላስቬጋስ ማምራቱን አምኗል፡፡ ወጣቱ በምርጫ ቅስቀሳው ላይ በጥበቃ ስራ ተሰማርቶ የነበረን ፖሊስ ጠመንጃ በመንጠቅ ትራምፕን ተኩሶ ለመግደል የያዘው ዕቅድ ባይሳካለትም፣ የጦር መሳሪያ በመያዝና ስራን በማስተጓጎል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ፣ በላስቬጋስ የፌዴራል ፍርድ ቤት የ1 አመት እስር እንደተጣለበት ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ተከሳሹ ሳንፎርድ የአእምሮ ችግር እንዳለበት በመጥቀስ ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ ያስገቡት የቅጣት ማቅለያ በምርመራ ተጨባጭ ሆኖ መገኘቱ በመረጋገጡ ቅጣቱን እንዳቀለለለትም ታውቋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የኢራን የመከላከያ ሚኒስትር ሁሴን ዴጋን፣ የትራምፕ ስልጣን መያዝ አለማችንን ወደ ጦርነት ሊያስገባት ፣ እስራኤልንም ለጥፋት ሊዳርጋት ይችላል ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ “ትራምፕ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ የኖረ ሰው ነው፤ አማካሪዎቹና ረዳቶቹ በተለይም በባህረ ሰላጤው አገራት ላይ ቀውስ ወደሚፈጥር እንዲሁም እስራኤልን ወደሚያጠፋና አካባቢውን አተራምሶ፣ አዲስ የአለም ጦርነት ወደሚቀሰቅስ አደገኛ አቅጣጫ ሊመሩት ይችላሉ” ብለዋል- ሚኒስትሩ፡፡

Read 4260 times