Sunday, 18 December 2016 00:00

የእግር ኳስ አካዳሚዎች፤ የታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ እና በዓለም ዙርያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ተቋማት፤ አካዳሚዎች እንዲሁም የታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች ስፖርቱን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ዋንኛ መሰረቶች ናቸው። በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች አገርን ለሚወክሉ ብሄራዊ ቡድኖች ዘላቂ ውጤታማነት ያስፈልጋሉ። ከስፖርቱ የሚገኘውን ገቢ በመጨመርም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በተለይ  ክለቦች በአካዳሚዎቻቸው፤ በታዳጊ እና ወጣት ፕሮጀክቶቻቸው በትኩረት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች ቡድኖችን በመመስረት መወዳደራቸው ለህልውናቸው ዋስተና  ይሆናል።  በተጨዋቾች የዝውውር ገበያና  ደሞዝ የሚገጥማቸውን የናረ ወጭ መቆጣጠር ይችላሉ፤ በየጊዜው ተተኪ ተጨዋቾችን ያፈሩባቸዋል፤ ዋና ቡድኖቻቸውን  በየጊዜው ለማጠናከር አይቸገሩም። የሚያፈሯቸውን ተጨዋቾች በዝውውር ገበያዎች በማቅረብ ትርፋማ እና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድልም ይፈጥርላቸዋል፡፡  በሌላ በኩል ከክለቦች ባሻገር ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በኢንቨስትመንት ሊሰሩበት ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ተቋማት አካዳሚዎች የታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች በቅንጅት መንቀሳቀሳቸውም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ፌደሬሽን፤ ክለቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚያከናወኑአቸው ተግባራት በፋይናንስ አቅማቸው የተጠናከሩ፤ መሆን አለባቸው፡፡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እና የማሰልጠኛ ቁሳቁሶች አሟልተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ አሰልጣኞች እና ሌሎች ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች በመቅጠር ማሰራታቸውም ተገቢ ነው፡፡ በወቅታዊ የስልጠና ማኑዋሎች ፤ ሳይንሳዊ ዘዴዎች የጋራ መመርያ፣ ራዕይና ግብ በመንደፍ ቢንቀሳቀሱም ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ የእግር ኳስ አካዳሚዎች፤ የታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ የሚገኙበትን ደረጃ በመጠኑ ይዳሰሳል፡፡  በአፍሪካ እና በዓለም ዙርያ ያሉ ተመክሮዎችን በመጠቃቀስ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም ጅምር አቅጣጫዎችን ለማነቃቃት የተዘጋጀ ነው፡፡
የፌደሬሽኑ እቅድ…
ከሁለት ሳምንት በፊት በ9ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽ ተተኪዎችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2010 ይተገበራል ባለው የአምስት አመት እቅድ መነሻነት ለ2009 በጀት አመት የተዘጋጀው ዝርዝር እቅድ በሙሉ ድምፅ አፅድቀውታል፡፡  እቅዱ የፌዴሬሽኑን ራእይ፣ ግቦች፣ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት እና የሚጠበቁ ውጤቶችን ይዟል። በትምህርት ተቋማት፣ በማሰልጠኛ ማዕከላትና ክለቦች የህፃናት፣ የታዳጊዎችና የወጣቶች ሥልጠናን በማስፋፋት ተተኪዎችን ለማፍራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦበታል፡፡
በተመረጡ ሞዴል ትምህርት ቤቶች እና ከትምህርት ቤቶች ውጪ ባሉ የስልጠና ጣቢያዎች 1260/ 585 ሴቶችና 675 ወንዶች/ ፤ ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተመረጡ 200 ጣቢያዎች /200 የሴቶችና 200 የወንዶች፤ በትምህርት ቤቶች 5600 /2800 ሴቶችና 2800 ወንዶች/ ፤በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 120 /60 ሴቶችና 60 ወንዶች/፤ በጥሩነሽ ዲባባ የስልጠና ማዕከል 120/60 ሴቶችና 60 ወንዶች/  እንዲሁም በአምቦ ስልጠና ማዕከል 60 /30ሴቶችና 30 ወንዶች ታዳጊና ወጣቶች በ2009 በትብብር እንዲሰለጥኑ ታቅዷል፡፡
በየደረጃው በሚገኙ የታዳጊ ወጣቶች፣ የከፍተኛ ሊግ፣ የብሄራዊ ሊግ እና የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች 2500 ተተኪ ስፖርተኞች በስልጠና መርሀ ግብሮቹ የሚታቀፉ ይሆናል።  በትምህርት ቤቶችና ከትምህርት ቤቶች ውጭ በሚካሄዱ የህፃናት፣ የታዳጊና ወጣቶች እግር ኳስ ስልጠና ጣቢያዎች ለሚካሄዱ ስልጠናዎች የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ በየደረጃው ፌደሬሽኑ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ቤቶች ውጪ  በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ በጥሩነሽ ዲባባ፣ በአምቦ ስልጠና ማዕከል፣ በኘሪሚየርና ብሔራዊ ሊግ ክለቦችና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስልጠና ማዕከል በድምሩ 350 ምርጥ የታዳጊና ወጣቶች ቡድኖች መካከል በዕድሜ የተከፋፈሉ ዓመታዊ ውድድሮችን እንደሚያካሂድም ገልጿል፡፡በ18 ክለቦች መካከል የሚደረጉት የU17 እና የU-20 ውድድር ሳይቆራረጥ የሚካሄድም ይሆናል። በ22 የሴትና የወንድ ቡድኖች የሚሳተፉበት የኮፓ ኮካኮላ ከ15 ዓመት በታች ውድድርም ይኖራል፡፡
የክለቦች ድርሻ..ሌሎች አካዳሚዎች
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የእግር ኳስ ውድድሮች ለመሳተፍ አስገዳጅ በሚሆነው ደንብ የብሄራዊ የክለብ ፈቃድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት ነው፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ከሚገመገሙባቸው መስፈርቶች ዋንኛውና የመጀመርያው ከወጣቶች ልማት አንፃር የተቀመጠው ነው፡፡ ክለቦች የፀደቀ የወጣቶች የእግር ኳስ ልማት ፕሮግራም መቅረፅ አለባቸው፡፡ የወጣቶች እግር ኳስ ልማት ዓላማና የወጣቶች የእግር ኳስ ልማት ፍልስፍና፤ የልማት ፕሮግራሙ አደረጃጀት፤ የሰው ኃይል መዋቅር፤ ከክለቡ ጋር ያለው ግልፅ ግንኙነት፤ ተገቢ የትምህርት ዝግጅት ያለው የሰው ሃይል፤ የእግር ኳስ ወይም የስፖርት ባለሙያ፤ የህክምና ባለሙያ፤ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፤ የውድድርና የመለማመጃ ስፍራ፤ ግልፅ የፋይናንስ አቅም፤ የእግር ኳስ ትምህርት፤ ስልጠናና ህጎች ፕሮግራም፤ የህክምና  ፕሮግራምና የመደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ዝግጅነት መኖራቸው ይፈተሻል፡፡ በሌላ በኩል የወጣት ቡድን አደረጃጀትን በተመለከተ ክለቦች ከ15 እስከ 21 ዓመት እንዲሁም ከ10 እስከ 14 ዓመት እድሜ ያላቸውን ቡድኖች በየደረጃ ስለመያዛቸው ይገመገማሉ፡፡
ዘንድሮ በአህጉራዊ ውድድሮች ተሳታፊ የሚሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ በዚህ አቅጣጫ የተደረገላቸውን ግምገማ አልፈዋል። ሰርተፍኬቱን ማግኘታቸው በታዳጊዎች እና ወጣቶች ባላቸው አደረጃጀት በመልካም ደረጃ ላይ መገኘታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ የሌሎች ክለቦችም ግምገማ እንደቀጠለ ነው፡፡ በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በታህሳስ ወር የሚያስመርቀው  የወጣቶች ማሰልጠኛ አካዳሚ  ለአፍሪካ ሞዴል ሊሆን ይችላል የተባለ ነው፡፡ ይህም ክለቡን ለመላው የአገሪቱ ክለቦች በተምሳሌትነት ያስጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት 3 እና አራት ዓመታት በታዳጊዎች እና የወጣቶች ፕሮጀክቶች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደአበረታች ጅምር መውሰድም ይቻላል፡፡ በተለይ ከፌደሬሽኑ፤ ከክለቦችና ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ባሻገር የግል እግር ኳስ አካዳሚዎች   በቀድሞ የእግር ኳስ ተጨዋቾች፤ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና ሌሎች ባለድርሻአካላት እየተመሰረቱ በመስራት ናቸው። ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባታቸው ተስፋ ይሰጣል፡፡ የሰውነት ቢሻው የእግር ኳስ አካዳሚ፤ በአሰግድ ተስፋዬ የሚካሄደው አካዳሚ ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡
የአገሪቱ ክለቦች ፌዴሬሽኑ፣ መንግስታዊ የስፖርት ተቋማት እንዲሁም ድጋፍ ሰጭ ስፖንሰሮች በቅንጅት ወደሚሰሩበት አቅጣጫ መገባት አለበት። በጋና እና በሌሎች የምእራብ አፍሪካ አገራት እንደሚስተዋለው የታዳጊና ወጣት ተጨዋቾች ምልመላና ስልጠና ሙሉ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡
የምእራብ አፍሪካ አገራትና አካዳሚዎቻቸው
በአፍሪካ የእግር ኳስ አካዳሚዎች እንቅስቃሴ በተለይ የምእራብ አፍሪካ አገራት ተጠናክረዋል። በዚሁ የአህጉሪቱ ዞን በሺዎች በሚቆጠሩ አካዳሚዎች በመስራት ተሳክቶላቸዋል፡፡ የምእራብ አፍሪካ አገራት የእግር ኳስ አካዳሚዎች እና ማሰልጠኛዎች በማንቀሳቀስ እና በአውሮፓ እግር ኳስ ተፈላጊ የሆኑ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን በማፍራት ከ15 ዓመት በላይ ይሆናቸዋል፡፡ እነ ጆርጅ ዊሃ፤ ኑዋንኩ ካኑ፣ ዲዴዬር ድሮግባ፣ ኢማኑዌል አደባዬር፣ ያያ ቱሬ… ሌሎች ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን በማውጣት በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛ ለውጥ መፍጠር ችለዋል። በተለይ የጋምቢያው ጄስፖ እና የናይጄርያው ኩዋራ እግር ኳስ አካዳሚዎች ባላቸው ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠቀሱ ይሆናሉ፡፡ በ2005 እኤአ ላይ የተመሰረተው የናይጄሪያው ኩዋራ የእግር ኳስ አካዳሚ ከ2011 እኤአ ጀምሮ በፊፋ ከፍተኛ ድጋፍ እና እውቅና አግኝቶ የሚሰራ ነው፡፡ በእንግሊዝ የእግር ኳስ አካዳሚዎች የተቀረፀው ይህ አካዳሚ ዘመናዊ ሜዳዎች፤ ጅምናዚዬም፤ የህክምና ማዕከል አሟልቶ ይንቀሳቀሳል፡፡ ታዳጊ ተጨዋቾችን ለናይጄርያ ሀ 17 ቡድን ቋሚነት እያቀረበ ሲሆን በላቲቪያ፣ በፖላንድ እና በእንግሊዝ ክለቦች በየጊዜው እያስመለመለ ይገኛል፡፡ በምእራብ አፍሪካ ተምሳሌት ሆነው የሚነሱ ሌሎች አካዳሚዎችም አሉ፡፡
አዜክ ሚሞሳ አካዳሚ በኮትዲቯር የሚገኝ ነው። በ1948 እኤአ ላይ ተመስርቷል፡፡ ባንድ ወቅት የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ስዊድናዊው ሰቨን ጎራን ኤሪክሰን የዓለም ምርጥ ብለውታል፡፡ ያያ ቱሬ፣ ጀርቪንሆ፣ ሰለሞን ካሉ፣ ኤቡዌ፣ ዛኮራ እና ሌሎች ተጨዋቾችን ለማፍራት የበቃ ነው፡፡ ከሆላንዱ ክለብ ፌዬነሮድ ሮተርዳም ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡
ፔፕሲ አካዳሚ በናይጄርያ የሚገኝ ነው፡፡ በፔፕሲ ኩባንያ ስፖንሰርነት የሚንቀሳቀስና በ1992 እኤአ የተመሰረተ ነው፡፡ ሚኬል ኦቢን የመሰለ ተጫዋች የተገኘበት ነው፡፡ በመላው ናይጄርያ 14 ቅርንጫፎች ከፍቶ እስከ 3ሺ ታዳጊዎችን የሚያሰለጥን ነው፡፡ በናይጄርያ ሀ 17፣ ሀ 20እና ሀ 23 ቡድኖች ቋሚ ተሰላፊዎች የሚሆኑ ተተኪዎች እያፈራ ሲሆን በዚህ አገሪቱ በአህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ውድድሮች ስኬታማ ሆናበታለች፡፡
በጋና ደግሞ ከ1998 እኤአ ጀምሮ ከሆላንዱ ክለብ ፌዬኖርድ ሮተርዳም ጋር በአጋርነት የሚንቀሳቀስ አካዳሚ አለ፡፡ የአካዳሚው ውጤቶች ከሆላንድ ባሻገር፤ በቤልጅዬም እና በግሪክ ክለቦች በየጊዜው ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ሄዷል፡፡
ዲያሞብራስ በሴኔጋል የሚገኝና ከአካዳሚም ላቅ በማለት በኢንስቲትዩት ደረጃ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ በ2003 እኤአ ላይ ተመስርቷል፡፡ በታዋቂው የቀድሞ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድንና የአርሰናል ክለብ ተጨዋች ፓትሪክ ቪዬራ ሊቀመንበርነት የሚመራ ነው፡፡ በአዲዳስ ኩባንያ ስፖንሰር የሆነው የዚህ ኢንስቲትዩት ታዳጊ ተጨዋቾች በፈረንሳይ፤ በሩስያ እና ቤልጅዬም ክለቦች የሚፈለጉ ናቸው፡፡
በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች
በዓለም አቀፍ ደረጃ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች እንዲሁም ስኬታማ ታሪክ ያላቸው ታላላቅ ክለቦች
በታዳጊ እና ወጣት  የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች፤ በአካዳሚዎቻቸው በመስራት ስኬታማ ናቸው። CIES የተባለው ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ተከታታይ እና ጥናት አድራጊ ተቋም ከዓመት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በ39 የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ያለውን እንቅስቃሴ በጥልቀት ዳስሶታል፡፡ ክለቦች እድሜያቸው ከ16 እስከ 21 የሚሆናቸውን ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በማፍራት ያገኙትን ስኬት የተመለከተ ሲሆን ባለፉት 3 ዓመታት ከአካዳሚዎቻቸው በርካታ  ተጨዋቾችን በማፍራት የተሳካላቸው ክለቦች በደረጃ አስቀምጧል፡፡
በአንደኛ ደረጃ የተጠቀሰው የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ሲሆን ያፈራቸው ታዳጊ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ብዛታቸው 57 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ሌላው የስፔን ክለብ ሪያል ማድሪድ ከአካዳሚው ፍሬዎች ቢያንስ ሁለት ተጨዋቾችን ከጋላክቲኮቹ ስብስብ በመቀላቀል መስራቱን ሪፖርቱ በአድናቆት የጠቀሰው ነው። 47  በማፍራት ሁለተኛ ደረጃ አሰጥቶታል፤ ካሪም ቤንዜማን ያፈራው የፈረንሳዩ ክለብ ሊዮን 39፤ እነ ዳኒ ዌልቤክ፤ ቶም ክሌቨርሊና ሌሎች የመጡበት የእንግሊዙ ማንዩናይትድ 39 እንዲሁም የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንትዠርመን 35 ታዳጊና ወጣት ፕሮፌሽናሎችን በአካዳሚዎቻቸው በመፍጠር እስከ 5 ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በየአካዳሚዎቻቸው ስኬታማ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚጠቀሱት ሌሎች የአውሮፓ ክለቦችም አሉ፡፡ የእንግሊዙ ሳውዝ ሃምፕተን እነ አዳም ላላና፣ ጋሬዝ ቤልና ቲዮ ዋልኮትን፤ የሆላንዱ አያክስ ሮተርዳም ቀደምቶቹን እነ ክሩፍ፤ ራይካርድ፤ በርግካምፕ እንዲሁም በቅርብ ዓመታት እነ ሽናይደር፣ ቫንደርቫትና ቬርማሊንን፤ የፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን በዓለም ኮከብ ተጨዋችነት 4 የወርቅ ኳስ ሽልማት ያሸነፈውን ሮናልዶን ጨምሮ እነ ናኒ፣ ኳሬስማንን፤ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ሽዋንስታይገር፣ ላሃም፣ ሙለር፣ ክሮስ እና ሌሎችን የፈጠሩ ናቸው፡፡
 የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ሲቲም መጠቀስ ያለበት ነው፡፡  በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ የተለያዩ አገራት  ፕሮፌሽናሎችን በከፍተኛ ሂሳብ በመቅጠር ወጭው የተጋነነ ክለብ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአካዳሚው በመስራት ተዋጥቶለታል፡፡ የማንችስተር ሲቲ አካዳሚ እነሸዋን ራይትፊሊፕስ፤ ዲከሰን ኡቱሁ፣ ስቴፈን አየረንላንድ እና ሌሎች ተጨዋቾችን ያፈራ ነው፡፡ ዌስትሃም ዩናይትድ እነ ፖል ኢንስ፣ ሪዮ ፈርዲናንድ፣ ማክል ካሪክ፣ ፍራንክ ላምፓርድ፣ ጆ ኮል፣ ጀርመን ዴፎና እና ሌሎችን ያስገኘ ነው፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች የየራሳቸውን አካዳሚ በማቋቋም ሲሰሩ ከ20 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ ከ20ዎቹ ክለቦች መካከል ብዙዎቹ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በአውሮፓ 31 የክለብ ሊጎች በወጣቶችእና ታዳጊዎች ፕሮጀክቶቻቸው በየአካዳሚዎቻቸው የሚያፈሯቸው ተጨዋቾች ዙርያ በዋና ቡድኖች በሚሰጡት የመሰለፍ እድል ደረጃ የወጣበት ጥናት በCIES ተሰርቷል፡፡ የአካዳሚ ውጤቶች በቡድን ስብስባቸው የሚያካሂዱት ምርጫ በአማካይ 19.7 በመቶ ድርሻ አለው።  በአካዳሚዎቻቸው የሚያፈሯቸውን ታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች በዋና ቡድኖቻቸው በማካተት ግንባር ቀደም የሆኑት 23.7 በመቶ በአማካይ የሚያካትቱት የስፔኑ ላሊጋ ክለቦች ሲሆኑ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች 13.7 በመቶ፤ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች 11.75 በመቶ እንዲሁም የጣሊያን ሴሪኤ ክለቦች 8.6 በመቶ አማካይ ተሳትፎ በመስጠት ተከታታይ ደረጃ ይኖራቸዋል፡፡
የባርሴሎናው ላ ሜስያ
ከዓለማችን የእግር ኳስ አካዳሚዎች ግንባር ቀደም ተምሳሌት ሆኖ የሚጠቀሰው ላ ሜስያ በ1979 እኤአ ላይ በሆላንዳዊው ዮሃን ክሩፍ ሃሳብ አመንጪነት ተመስርቷል፡፡ በ9 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ማዕከል አለው፡፡ በስራ ላይ በቆየባቸው ዓመታት ለዓለም እግር ኳስ ከ200 በላይ ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን አውጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ2000 በላይ ሰልጣኞቹን በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች በማቀፍ ይሰራል፡፡ በዓመት እስከ 11 ሚሊዮን ዶላር በጀት አለው፡፡
ወደ ላ ሜስያ የሚገቡ ታዳጊዎች በየዓመቱ ይመለመላሉ፡፡ ከ6 እስከ 8 ዓመት እድሜ ያላቸው ታዳጊዎች ናቸው፡፡ በላ ሜስያ ቅጥር መልማዮች አማካኝነት ነው፡፡  15 ክለቡ በሚገኝበት የካተሎና ግዛት፣ 15 በመላው የስፔን ግዛቶች እንዲሁም 10 በመላው ዓለም በመሰማራት 1000 ያህል ህፃናት መልምለው ምዝገባ ያከናናሉ፡፡   ከዚያም በአካዳሚው መስፈርት የተመረጡ 200 ታዳጊዎች ይቀላቀላሉ፡፡ ላ ሜስያ በ24 ምርጥ አሰልጣኞች አካዳሚውን ያንቀሳቅሳል ፡፡ በህክምና፣ በስነልቦና፣ በስነምግብ እና በፊዚዮሎጂስትነት  ከ50 በላይ ሌሎች ባለሙያዎችንም ቀጥሮ የሚሰራ ነው፡፡
የጀርመን ፌደሬሽና የቦንደስ ሊጋ ክለቦች ስኬታማ  የ10 ዓመታት ስትራቴጂ
በፌደሬሽን ደረጃ በሚካሄድ እንቅስቃሴ በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችለው የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን ይሆናል፡፡ በአገሪቱ እግር ኳስ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ያመጣውን እንቅስቃሴ በማከናወን ነው፡፡ በ1990 በዓለም ዋንጫ እንዲሁም በ1994 በአውሮፓ ዋንጫ በእድሜያቸው አንጋፋ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የገጠመው ቀውስ ለለውጡ መነሻው ነበር፡፡
በወቅቱ ፌደሬሽኑን ይመሩ የነበሩት ፕሬዝዳንት የአገሪቱ እግር ኳስ በታዳጊዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው ወሰኑ፡፡ ይሄው ስትራቴጂ በስርነቀል መንገድ እንዲከናወን መሰረት የጣለ አቋም ነበር፡፡ በ2000 እኤአ በአውሮፓ ዋንጫ ላይ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ደካማ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ ተግባራዊ መሆን ጀመረ፡፡ በመላ አገሪቱ 350 የእግር ኳስ ማዕከላት በ1000 ብቁ እና ፕሮፌሽናል አሰልጣኞች ስራ እንዲጀምሩ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ተንቀሳቀሰ፡፡ በዋናው ቦንደስ ሊጋ እና በሁለተኛው ቦንደስ ሊጋ ላይ ተወዳዳሪ የሆኑ ክለቦች በሙሉ የታዳጊ ማሰልጠኛ አካዳሚዎች እንዲኖራቸው ፤ ከ2002 - 2003 የውድድር ዘመን ጀምሮ አስገዳጅ መመርያ ሆኖ ፀደቀ፡፡ ሁሉም የዋናው ቦንደስ ሊጋ እና የሁለተኛው ቦንደስ ሊጋ ክለቦች የሀ 13 እና የሀ 19 ቡድኖች እንዲያቋቁሙ የሚያስገድድ መመርያ  ነው፡፡ ለእነዚህ ቡድኖቻቸው በሚገነቧቸው አካዳሚዎች 3 የሳር ሜዳዎች ሁለቱ ፓውዛ ያላቸው፤ ጂም እና ሌሎች መሰረት ልማቶች ካሟሉ ብቻ በየሊጎቹ መወዳደር ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ በቀጣይ በሁለቱም የሊግ ደረጃዎች ያሉ ክለቦች ከአካዳሚዎቻቸው እና ከሌሎች የአገሪቱ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ተቋማት ቢያንስ 8 ታዳጊዎችን በተጨዋች ስብስባቸው ማስመዝገብ እንዳለባቸው፤ ከመካከላቸው ም4 ተጨዋቾችን በየዋና ቡድኖቻቸው ማሰለፍ እንደሚኖርባቸው በማስገደድ ተሰራ፡፡  ይህ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስትራቴጂ ከ10 ዓመታት በኋላ ከፍተኛ ለውጥ ሊመዘገብበት ችሏል፡፡ በጀርመን የክለብ እግር ኳስ ከሀ 12 እስከ 23 ባሉት የእድሜ ደረጃዎች መጫወት የሚችሉ ታዳጊዎች ብዛታቸው ከ5000 በላይ ሆነ። ከሀ 18 በታች ያሉ ቡድኖች ከ1000 በላይ ሆነው ከ2 ሚሊዮን በላይ ታዳጊዎችን በስራቸው በማቀፍ የሚንቀሳቀሱ ሆኑ፡፡ የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን ከላይ ለተዘረዘሩት እንቅስቀሴዎች በ10 ዓመታት ከ700 ሚሊዮን ዶላር ወጭ አድርጓል፡፡ ዛሬ የቦንደስ ሊጋ ክለቦች እያንዳንዳቸው በዓመት በአማካይ እስከ  90 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት እየተንቀሳቀሱበት ነው፡፡
ኤቨርግራንዴ፤ ግዙፉ የእግር ኳስ ትምህርት ቤት በቻይና
 በአካዳሚ እንቅስቃሴ በቻይና ስርነቀል የእግር ኳስ አብዮት በመፍጠር ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የቻይና መንግስት በ2009 እኤአ በጀመረው አገር አቀፍ የእግር ኳስ ፕሮጀክት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። በቻይና ሱፕርሊግ በሚወዳደረው ጉዋንዙ ክለብ ከአጋርነት የሚንቀሳቀሰው ኤቨርግራንዴ  የእግር ኳስ ትምህርት ቤት በ10 ወራት ውስጥ በ200 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ነው፡፡
ኤቨርግራንዴ የእግር ኳስ አካዳሚ ያለው የመሰረተ ልማት አቅም እጅግ በጣም የሚያስገርም ነው፡፡ 2800 ታዳጊ ተጨዋቾችን ይዟል፡፡ 50 ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ ሜዳዎች፤  ከ25 በላይ ምርጥ ስፔናዊ አሰልጣኞች፤  ጂምናዚዬሞች፤ ምግብ ቤቶች፤ ማረፊያዎች፤ ሲኒማ ቤት እና የሌሎች ስፖርቶች ሜዳዎችን ያቀፈ ነው፡፡ የእግር ኳስ ትምህርት ቤቱ በደቡብ ቻይና የሚገኝ ሲሆን በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ እግር ኳስን መደበኛ ትምህርት አድርጎታል፡፡ ከ20 እና 30 ዓመታት ቻይና የዓለም ዋንጫን እንድታሸንፍ ተስፋ ተደርጎበታል፡፡ የሰልጣኞቹን ብዛት በቀጣይ ዓመታት እስከ 10ሺ የሚያሳድግበት አቅም አለው፡፡

Read 1091 times