Saturday, 17 December 2016 12:54

የአቶ አሰፋ ጎሳዬ የ12ኛ ዓመት መታሰቢያ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መስራች
የአቶ አሰፋ ጎሳዬ ገዳ የ12ኛ ዓመት መታሰቢያ ታህሳስ
6 ቀን 2009 ዓ.ም በቅዱስ ካቴድራል አማኑኤል
ቤተክርስቲያን በፀሎት ታስቦ ውሏል፡፡
አሴዋ ሁሌም እናስብሃለን ቤተሰቦችህ


አንድ ደርዘን ዕድሜ

አሴ!
ከቶም አንድ ደርዘን ዕድሜ፣ አለፈና ዘመን ሆነ
አዋቂውን እያከሳ፣ ድንቁርና እያደነደነ
የነበረው እንዳለ አለ
እንደ አፋር ጫማ ፊት ኋላውን፣ አቅጣጫው አልለይ እንዳለ፡፡
ያልተዘመረለት ነህ፣ ብዬህ ነበር ገና ያኔ
አሁንም ወሮናል አሴ፣ የዕውቀትና ብስለት - ጠኔ
ዛሬም ያልተዘመረለት፣ እንደገባ ነው ምናኔ!
“… አዎ አለ አንዳንድ ሰው
ጉቶ የሸፈነው የአገር ግዙፍ ዋርካ
መስፈሪያ የሌለው፣ ልቡ እማይለካ
… ያልተዘመረለት፣ እሱ ኖሯል ለካ!”
ያልኩህ ትዝ ይበልህ አሴ፣ ዛሬም ያው ጮካ ለጮካ
ኑሮ ሆኗላ እንካ በእንካ!
ዘመኔ መቀነቻ አጥቶ፣ ይሸነጋገላል ሰው ሁሉ
የአፉ ከሆዱ ተጣልቶ፣ ጠፍቶበታል ዕትብት ውሉ፡፡
ሰው ሲጠፋን ስለሰው፣ ማሰብ የማይቀር ዕውነት ነው
ያጎደሏትን አገር፣ መሙላት ጭንቁ መቶ አምሳ ነው
ቅጣቱ ራስን ማጉደል ነው!
አላዋቂው ከላይ ሰፍሮ
አዋቂ ታች ተቀርቅሮ
ዱሮ እንዳየኸው ነው ህይወት፣ ያው የግርምቢጡ ኑሮ!
ሰው ራሱን ለማየት ዛሬም ዐይኑ ጠፍቶበታል
እንንገርህ ብንል ደግሞ፣ ቀድ ጆሮውን ይዘጋል
ደምም መቅመስ አልሆነለት፣ ፍጥረቱ ለጣ’ም ጣም የለው
ስድስተኛ ስሜት አለው፣ ብለን ጥንት የጠረጠርነው
ከነአምስቱም ጠፍቶበታል፣ መደናበር ነው የያዘው!
አሴ እንዳልኩህ ጉቶው በዛ፣ ዋርካ እሚሆን ሰው ጠፋና
በግምገማ ብቻ ቀረን፣ ጧት ማታ እያወራን መና!
አሴ! ፈገግ በል እባክህ፣ ምንም አላጣህምና!
የምንፈልገውን ሳናውቅ፣ የምናውቀውን ሳንፈልግ
የሚሄደውን መራገም፣ ለመጣ ሁሉ ማደግደግ
ይህ ሆኗል የህሊና ሕግ!
አዲስ መውለድ ሲያቅተን፣ ያረጥነውን መናፈቅ
እርግማን ነው የቤት ጣጣ፣ ዘልቆ አገርን የማያዘልቅ
አሴ!
ትውልዱም እንዳስቀመጥከው
ዴሞክራሲም ያው እዚያው ነው
ንግዱ በጭንቅ፣ ኑሮው በጭንቅ፣ ባለቤት
የሌለው እልፍኝ
ከቶም ያልተግባብቶም አገር፣ የሆድ ያንጀት
እማያስገኝ
ወይ ከታሪኩ ያልሆነ፣ ወይ ልባም ታሪክ ያልሰራ
እንደው ሸርተት ሸተት ብቻ፣ የአንድ ደርዘን ዕድሜ ጎራ
ነውና አሴ አልቀረብህም፣ እዚያው ፈገግ ብለህ ኩራ!
ያ ፈገግታ ነው የናፈቀን፣ አሴ ሳቅልን አደራ!!
ከቶም ላልተዘመረለት፣ እንዘምርለት ያልነው
ከቶም ላልተነገረለት እንናገርለት ያልነው
ዛሬም ሀቁ እንደዚያው ነው
አስራ ሁለት ዓመት ሆነ፣ ደርዘን ፈገግታህ ይፍካ
ሁሌም እናስብሃለን፣ በቅን ፍቅራችን ተመካ!
ወደፊት እንሂድ እንጂ፣ ወደኋላ ማሰብ አይቀር
አለህ እውስጣችን አሴ፣ ስምህ የትም አይቀበር
ህዝቡ ይወቅ ብለሃል፣ ዕውቀት የፈራ ያቀርቅር
በዚህ ነው አንተ እምትኖር!
“መርሳት ለዘላለም ይኑር፣” የሚሉ እንዳሉ አቃለሁ
እኔ ግን በልብ ዕምነቴ፣ መርሳት ይሙት እላለሁ!!
(ለአሰፋ ጎሳዬ 12ኛ ሙት ዓመት
እና ለማንረሳቸው ሁሉ መታሰቢያ)
ነቢይ መኮንን

Read 6845 times Last modified on Saturday, 17 December 2016 14:59