Sunday, 25 December 2016 00:00

የአትሌት ዋሚ ቢራቱ 100ኛ ዓመት የልደት በዓል ይከበራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በሱሉልታ ከተማ ጥር 11 ቀን 1909 ዓ.ም የተወለዱትና ለ64 ዓመታት በሩጫ አንፀባራቂ ድሎችን የተጎናፀፉት ታላቁ አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ፤ የተወለዱበት 100ኛ ዓመትና ሩጫ የጀመሩበት 64ኛ ዓመት ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አዘጋጁ “ኢጂጂ ኤቨንት ኦርጋናይዘር” አስታወቀ፡፡
ትላንት ዕለት በሸራተን አዲስ ሰሜን አዳራሽ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ የአንጋፋው አትሌት የ100ኛ አመት ልደትና ሩጫ የጀመሩበት 64ኛ ዓመት በዓል በዶክሜንተሪ ፊልም፣ በስእል አውደ ርዕይ በስማቸው አደባባይና መንገድ በመሰየምና ወደ ትውልድ ከተማቸው በመሄድ ይከበራል፡፡
አትሌት ዋሚ ቢራቱ ሩጫን የተቀላቀሉት በውትድርና አገራቸውን እንዲያገለግሉ ተመድበው አስመራ በነበሩበት በ1945 ዓ.ም እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ከዚያን ዘመን አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት ለአገራቸው ድልን በማስመዝገብ እንደ አበበ ቢቂላ ላሉ ብርቅዬ አትሌቶች አርአያ ቢሆኑም የሰሩትን ያህል አለመከበራቸውን አዘጋጆቹ ገልፀው፤ ይህንን ቁጭት ለመወጣት፣ አትሌቱን ለመደገፍና የጥንካሬያቸውን ምስጢር ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ ፕሮግራሞቹ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 30 በተለያዩ ቦታዎችና ዝግጅቶች የሚከበሩ ሲሆን ጥር 30 ቀን 2009 በኦሮሞ የባህል ማዕከል የመዝጊያ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡

Read 2689 times