Sunday, 25 December 2016 00:00

ግለሠቡ በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ በእሳት ተቃጥሎ ሞተ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 በአዲስ አበባ የካ/ክፍለ/ከተማ ወረዳ 7፤ አንድ ለጊዜው ማንነቱ ያልታወቀ ግለሠብ ከትናንት በስቲያ ንጋት ላይ በአካባቢው በሚገኝ የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ በእሳት ተቃጥሎ ህይወቱ ማለፉን፤ የአይን እማኞች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በአካባቢው በሚገኝ ድርጅት በጥበቃ ስራ ላይ እንደተሠማሩ የገለፁልን አቶ ተሾመ የተባሉ የአይን እማኝ፤ ከሳቸው በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ከንጋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው እሳት ሲነድ መመልከታቸውን ጠቁመው ወደ ገንዳው ተጠግተው ሲመለከቱ፤ የሚቃጠለው ሰው መሆኑን መገንዘባቸውንና በእሳት የተቀጣጠለው ሰውነቱን ሲያወራጭ መመልከታቸውን በአካባቢው ከሚገኝ ሌላ ጥበቃ ጋር በመመካከርም ጉዳዩን ለፖሊስ አመልክተው ፓሊሶች በአካባቢው ላይ ፈጥነው በመድረስ፣ እሳቱን በውሃ ቢያጠፉም የግለሰቡ ህይወት ሊተርፍ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
በቆሻሻ ገንዳ ጥበቃና ቁጥጥር ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የገለፁልን ሌላው የአይን እማኝ አቶ ሸበላው ከበደ፤ በጥበቃ ማረፊያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ የሰው ጩኸት በመስማታቸው፤ ፈጥነው ከቤት ወጥተው ሲመለከቱ፤ በቅርባቸው ያለው የቆሻሻ ገንዳ በእሳት ተያይዞ መመልከታቸውንና የሚቃጠለውም ሰው መሆኑን ሲረዱ በድንጋጤ ጉዳዩን ለፖሊስ ማመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡ ገንዳው መጠነኛ ቆሻሻ ያለበት መሆኑን የጠቀሱት የአይን እማኙ ፖሊሶች እሳቱን በውሃ አጥፍተው፣ አስክሬኑን ከገንዳው ቢያወጡትም ማንነቱ መለየት በማይችልበት ሁኔታ መቃጠሉን መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡
አስክሬኑንም ፖሊስ ለምርመራ መውሰዱን እኚሁ የአይን እማኙ አስታውቀዋል፡፡
ግለሰቡ ራሱን በራሱ አቃጥሎ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት እስካሁን የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ የፖሊስ ምንጮች መረጃ ጠቁመዋል፡፡

Read 4309 times